ምዕራፍ 12

እግዚአብሔርም ናታንን ወደ ዳዊት ላከ፥ ወደ እርሱም መጥቶ አለው። በአንድ ከተማ አንዱ ባለጠጋ አንዱም ድሀ የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ።
2 ፤ ባለጠጋውም እጅግ ብዙ በግና ላም ነበረው።
3 ፤ ለድሀው ግን ከገዛት አንዲት ታናሽ በግ በቀር አንዳች አልነበረውም፤ አሳደጋትም፥ ከልጆቹም ጋር በእርሱ ዘንድ አደገች፤ እንጀራውንም ትበላ፥ ከዋንጫውም ትጠጣ፥ በብብቱም ትተኛ ነበር፥ እንደ ልጁም ነበረች።
4 ፤ ወደ ባለጠጋውም እንግዳ በመጣ ጊዜ ከበጉና ከላሙ ወስዶ ለዚያ ወደ እርሱ ለመጣው እንግዳ ያዘጋጅለት ዘንድ ሳሳ፤ የዚያንም የድሀውን ሰው በግ ወስዶ ለዚያ ለመጣው ሰው አዘጋጀ።
5 ፤ ዳዊትም በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቈጥቶ ናታንን። ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ያደረገ ሰው የሞት ልጅ ነው።
6 ፤ ይህን አድርጎአልና፥ አላዘነምና ስለ አንዲቱ በግ አራት ይመልስ አለው።
7 ፤ ናታንም ዳዊትን አለው። ያ ሰው አንተ ነህ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእስራኤል ላይ ንጉሥ ልትሆን ቀባሁህ፥ ከሳኦልም እጅ አዳንሁህ፤
8 ፤ የጌታህንም ቤት ሰጠሁህ፥ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ ጣልሁልህ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ፤ ይህም አንሶ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ እጨምርልህ ነበር።
9 ፤ አሁንስ በፊቱ ክፉ ትሠራ ዘንድ የእግዚአብሔርን ነገር ለምን አቃለልህ? ኬጢያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መትተሃል፥ ሚስቱንም ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃል፤ እርሱንም በአሞን ልጆች ሰይፍ ገድለሃል።
10 ፤ ስለዚህም አቃልለኸኛልና፥ የኬጢያዊውንም የኦርዮን ሚስት ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃልና ለዘላለም ከቤትህ ሰይፍ አይርቅም።
11 ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ከቤትህ ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ፤ ሚስቶችህንም በዓይንህ ፊት እወስዳለሁ፥ ለዘመድህም እሰጣቸዋለሁ፥ በዚህችም ፀሐይ ዓይን ፊት ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል።
12 ፤ አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል፤ እኔ ግን ይህን በእስራኤል ሁሉ ፊትና በፀሐይ ፊት አደርገዋለሁ።
13 ፤ ዳዊትም ናታንን። እግዚአብሔርን በድያለሁ አለው። ናታንም ዳዊትን። እግዚአብሔር ደግሞ ኃጢአትህን አርቆልሃል፤ አትሞትም።
14 ፤ ነገር ግን በዚህ ነገር ለእግዚአብሔር ጠላቶች ታላቅ የስድብ ምክንያት አድርገሃልና ስለዚህ ደግሞ የተወለደልህ ልጅ ፈጽሞ ይሞታል አለው።
15 ፤ ናታንም ወደ ቤቱ ተመለሰ። እግዚአብሔርም የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችውን ሕፃን ቀሠፈ፥ እጅግም ታምሞ ነበር።
16 ፤ ዳዊትም ስለ ሕፃኑ እግዚአብሔርን ለመነ፤ ዳዊትም ጾመ፥ ገብቶም በመሬት ላይ ተኛ።
17 ፤ የቤቱም ሽማግሌዎች ተነሥተው ከምድር ያነሡት ዘንድ በአጠገቡ ቆሙ፤ እርሱ ግን እንቢ አለ፥ ከእነርሱም ጋር እንጀራ አልበላም።
18 ፤ በሰባተኛውም ቀን ሕፃኑ ሞተ። የዳዊትም ባሪያዎች። ሕፃኑ በሕይወት ሳለ ብንነግረው አልሰማንም፤ ይልቁንስ ሕፃኑ እንደ ሞተ ብንነግረው እንዴት ይሆን? በነፍሱ ክፉ ያደርጋል ብለው ሕፃኑ እንደ ሞተ ይነግሩት ዘንድ ፈሩ።
19 ፤ ዳዊትም ባሪያዎቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ ባየ ጊዜ ዳዊት ሕፃኑ እንደ ሞተ አወቀ፤ ዳዊትም ባሪያዎቹን። ሕፃኑ ሞቶአል? አላቸው። እነርሱም። ሞቶአል አሉት።
20 ፤ ዳዊትም ከምድር ተነሥቶ ታጠበ፥ ተቀባም፥ ልብሱንም ለወጠ፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገብቶ ሰገደ። ወደ ቤቱም መጣ። እንጀራ አምጡልኝ አለ፤ በፊቱም አቀረቡለት፥ በላም።
21 ፤ ባሪያዎቹም። ይህ ያደረግኸው ነገር ምንድር ነው? በሕይወት ሳለ ስለ ሕፃኑ ጾምህና አለቀስህ፤ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ እንጀራ በላህ አሉት።
22 ፤ እርሱም። ሕፃኑ ሕያው ሳለ። እግዚአብሔር ይምረኝ፥ ሕፃኑም በሕይወት ይኖር እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ብዬ ጾምሁ አለቅሰሁም።
23 ፤ አሁን ግን ሞቶአል፤ የምጾመው ስለ ምንድር ነው? በውኑ እንግዲህ እመልሰው ዘንድ ይቻለኛልን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ አይመለስም አለ።
24 ፤ ዳዊትም ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፥ ወደ እርስዋም ገባ፥ ከእርስዋም ጋር ተኛ፤ ወንድ ልጅም ወለደች፥ ስሙንም ሰሎሞን ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም ወደደው፤
25 ፤ ደግሞም በነቢዩ በናታን እጅ ልኮ ስሙን ስለ እግዚአብሔር ይዲድያ ብሎ ጠራው።
26 ፤ ኢዮአብም የአሞንን ልጆች ከተማ ረባትን ወጋ፥ የውኃውንም ከተማ ያዘ።
27 ፤ ኢዮአብም ወደ ዳዊት። ረባትን ወግቻለሁ፥ የውኃውንም ከተማ ይዤአለሁ።
28 ፤ አሁንም ከተማይቱን እንዳልይዝ፥ በስሜም እንዳትጠራ፥ የቀረውን ሕዝብ ሰብስብ፥ ከተማይቱንም ከብበህ ያዝ ብሎ መልእክተኞችን ላከ።
29 ፤ ዳዊትም ሕዝቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ረባት ሄደ፥ ወግቶም ያዛት።
30 ፤ የንጉሣቸውንም ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ። ክብደቱም አንድ መክሊት ወርቅ ያህል ነበር፥ ክቡር ዕንቍም ነበረበት፤ ዳዊትም በራሱ ላይ አደረገው። ከከተማይቱም እጅግ ብዙ ምርኮ አወጣ።
31 ፤ በውስጥዋም የነበሩትን ሕዝብ አውጥቶ በመጋዝና በብረት መቈፈሪያና በብረት መጥረቢያ እንዲሠሩ አደረጋቸው፤ የሸክላ ጡብም እንዲያቃጥሉ አደረጋቸው፤ በአሞን ልጆች ከተሞች ሁሉ እንዲህ አደረገ። ዳዊትም ሕዝቡም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።