ምዕራፍ 20

እንዲህም ሆነ፤ አንድ ብንያማዊ የቢክሪ ልጅ ስሙ ሳቤዔ የሚባል ምናምንቴ ሰው ነበረ፤ እርሱም። ከዳዊት ዘንድ እድል ፈንታ የለንም፥ ከእሴይም ልጅ ዘንድ ርስት የለንም፤ እስራኤል ሆይ፥ እያንዳንድህ ወደ ድንኳንህ ተመለስ ብሎ ቀንደ መለከት ነፋ።
2 ፤ የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ከዳዊት ተለይተው የቢክሪን ልጅ ሳቤዔን ተከተሉ፤ የይሁዳ ሰዎች ግን ከዮርዳኖስ ጀምረው ኢየሩሳሌም እስኪደርሱ ንጉሣቸውን ተከተሉ።
3 ፤ ዳዊትም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ቤቱ መጣ፤ ንጉሡም ቤቱን ሊጠብቁ የተዋቸውን አሥሩን ቁባቶች ወስዶ ለጠባቂ ሰጣቸው፥ ቀለብም ሰጣቸው፥ ነገር ግን ወደ እነርሱ አልገባም፤ በቤት ተዘግተው እስኪሞቱም ድረስ ባልቴቶች ሆነው ተቀመጡ።
4 ፤ ንጉሡም አሜሳይን። የይሁዳን ሰዎች ሁሉ በሦስት ቀን ውስጥ ጥራልኝ፥ አንተም አብረህ በዚህ ሁን አለው።
5 ፤ አሜሳይም የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ይጠራ ዘንድ ሄደ፤ ነገር ግን እርሱ የተቀጠረውን ቀን አሳልፎ ዘገየ።
6 ፤ ዳዊትም አቢሳን። አሁን ከአቤሴሎም ይልቅ የሚጎዳን የቢክሪ ልጅ ሳቤዔ ነው፤ እርሱ የተመሸጉትን ከተሞች አግኝቶ ከዓይናችን እንዳያመልጥ፥ አንተ የጌታህን ባሪያዎች ወስደህ አሳድደው አለው።
7 ፤ አቢሳንም ተከትለው የኢዮአብ ሰዎች ከሊታውያንም ፈሊታውያንም ኃያላንም ሁሉ ሄዱ፤ የቢክሪንም ልጅ ሳቤዔን ለማሳደድ ከኢየሩሳሌም ወጡ።
8 ፤ በገባዖንም ወዳለው ወደ ታላቁ ድንጋይ በደረሱ ጊዜ አሜሳይ ሊገናኛቸው መጣ፤ ኢዮአብም የሰልፍ ልብስ ለብሶ ነበር፥ በላዩም መታጠቂያ ነበረ፥ በወገቡም ላይ ሰገባ ያለው ሰይፍ ታጥቆ ነበር፤ እርሱም ሲራመድ ሰይፉ ወደቀ።
9 ፤ ኢዮአብም አሜሳይን። ወንድሜ ሆይ፥ ደኅና ነህን? አለው ኢዮአብም አሜሳይን የሚስም መስሎ በቀን እጁ ጢሙን ያዘው።
10 ፤ አሜሳይ ግን በኢዮአብ እጅ ከነበረው ሰይፍ አልተጠነቀቀም ነበር፤ ኢዮአብም ሆዱን ወጋው፥ አንጀቱንም በምድር ላይ ዘረገፈው፤ ሁለተኛም አልወጋውም፥ ሞተም። ኢዮአብና ወንድሙ አቢሳ የቢክሪን ልጅ ሳቤዔን አሳደዱ።
11 ፤ ከኢዮአብም ብላቴኖች አንዱ በአሜሳይ ሬሳ አጠገብ ቆሞ። ለኢዮአብ ወዳጅ የሚሆን ለዳዊትም የሆነ ሁሉ ኢዮአብን ይከተል ይል ነበር።
12 ፤ አሜሳይም በመንገድ መካከል ወድቆ በደሙ ላይ ይንከባለል ነበር፤ ያም ሰው ወደ እርሱ የሚመጣ ሁሉ ሲቆም አይቶአልና ሕዝቡ ሁሉ እንደ ቆመ ባየ ጊዜ አሜሳይን ከመንገድ ላይ ወደ እርሻ ውስጥ ፈቀቅ አደረገው፥ በልብስም ከደነው።
13 ፤ ከመንገድ ራቅ ባለ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ የቢክሪን ልጅ ሳቤዔን ለማሳደድ ኢዮአብን ተከትሎ ያልፍ ነበር።
14 ፤ እርሱ ግን ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ወደ አቤል፥ ወደ ቤትመዓካ፥ ወደ ቤሪም ሁሉ አለፈ፤ ሰዎችም ደግሞ ተሰብስበው ተከተሉት።
15 ፤ በቤትመዓካ ባለ በአቤልም መጥተው ከበቡት፥ በከተማይቱም ላይ እስከ ቅጥርዋ ድረስ የአፈርን ድልድል ደለደሉ፤ ቅጥሩንም ያፈርሱ ዘንድ ከኢዮአብ ጋር የነበሩ ሕዝብ ሁሉ ይደባደቡ ነበር።
16 ፤ ከከተማይቱም አንዲት ብልሃተኛ ሴት። ስሙ፥ ስሙ፤ ኢዮአብንም። እነግርህ ዘንድ ወደዚህ ቅረብ በሉት ስትል ጮኸች።
17 ፤ ወደ እርስዋም ቀረበ፤ ሴቲቱም። ኢዮአብ አንተ ነህን? አለች። እርሱም። እኔ ነኝ ብሎ መለሰላት። እርስዋም። የባሪያህን ቃል ስማ አለችው። እርሱም። እሰማለሁ አላት።
18 ፤ እርስዋም። ቀድሞ። የሚጠይቅ በአቤል ዘንድ ይጠይቅ ይባል ነበር፤ እንዲሁም ነገሩ ይፈጸም ነበር።
19 ፤ በእስራኤል ዘንድ ሰላምንና እውነትን ከሚወድዱ እኔ ነኝ፤ አንተ በእስራኤል ያለችውን ከተማና እናት ለማፍረስ ትሻለህ፤ ስለ ምንስ የእግዚአብሔርን ርስት ትውጣለህ? ብላ ተናገረች።
20 ፤ ኢዮአብም መልሶ። ይህ መዋጥና ማጥፋት ከእኔ ይራቅ፤
21 ፤ ነገሩ እንዲህ አይደለም፤ ከተራራማው ከኤፍሬም አገር የሚሆን የቢክሪ ልጅ ሳቤዔ የሚባል አንድ ሰው ግን በንጉሡ በዳዊት ላይ እጁን አነሣ፤ እርሱን ብቻውን ስጡኝ፥ እኔም ከከተማይቱ እርቃለሁ አላት። ሴቲቱም ኢዮአብን። እነሆ፥ ራሱ ከቅጥር ላይ ይጣልልሃል አለችው።
22 ፤ ሴቲቱም በብልሃትዋ ወደ ሕዝቡ ሁሉ ሄደች፤ እነርሱም የቢክሪን ልጅ የሳቤዔን ራስ ቈርጠው ወደ ኢዮአብ ጣሉት። እርሱም ቀንደ መለከቱን ነፋ፥ ሰውም ሁሉ ከከተማይቱ ርቆ እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ ሄደ። ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
23 ፤ ኢዮአብም በእስራኤል ሠራዊት ሁሉ ላይ አለቃ ነበረ፤ የዩዳሄም ልጅ በናያስ በከሊታውያንና በፈሊታውያን ላይ ነበረ፤
24 ፤ አዶኒራምም ግብር አስገባሪ ነበረ፤ የአሒሉድም ልጅ ኢዮሣፍጥ ታሪክ ጸሐፊ ነበረ፤
25 ፤ ሱሳም ጸሐፊ ነበረ፤ ሳዶቅና አብያታርም ካህናት ነበሩ፤
26 ፤ የኢያዕር ሰውም ዒራስ ለዳዊት አማካሪ ነበረ።