ምዕራፍ 5

የእስራኤልም ነገድ ሁሉ ወደ ኬብሮን ወደ ዳዊት መጥተው። እነሆ፥ እኛ የአጥንትህ ፍላጭ የሥጋህ ቍራጭ ነን።
2 ፤ አስቀድሞ ሳኦል በእኛ ላይ ንጉሥ ሆኖ ሳለ እስራኤልን የምታወጣና የምታገባ አንተ ነበርህ፤ እግዚአብሔርም። አንተ ሕዝቤን እስራኤልን ትጠብቃለህ፥ በእስራኤልም ላይ አለቃ ትሆናለህ ብሎህ ነበር አሉት።
3 ፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ኬብሮን መጡ፤ ንጉሡ ዳዊትም በኬብሮን በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደረገ፤ በእስራኤልም ንጉሥ ይሆን ዘንድ ዳዊትን ቀቡት።
4 ፤ ዳዊትም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ዓመት ልጅ ነበረ፥ አርባ ዓመትም ነገሠ።
5 ፤ በኬብሮን በይሁዳ ላይ ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነገሠ፤ በኢየሩሳሌምም በእስራኤል ሁሉና በይሁዳ ላይ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ።
6 ፤ ንጉሡና ሰዎቹም በአገሩ ውስጥ ከተቀመጡት ከኢያቡሳውያን ጋር ለመዋጋት ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ፤ እነርሱም። ዳዊት ወደዚህ ሊገባ አይችልም ብለው አስበው ነበርና ዳዊትን። ዕውሮችንና አንካሶችን ካላወጣህ በቀር ወደዚህ አትገባም አሉት።
7 ፤ ነገር ግን ዳዊት አምባይቱን ጽዮንን ያዘ፥ እርስዋም የዳዊት ከተማ ናት።
8 ፤ በዚያም ቀን ዳዊት። ኢያቡሳውያንን የሚመታ በውኃ መሄጃው ይውጣ፤ የዳዊትም ነፍስ የምትጠላቸውን ዕውሮችንና አንካሶችን ያውጣ አለ። ስለዚህም በምሳሌ። ዕውርና አንካሳ ወደ ቤት አይግቡ ተባለ።
9 ፤ ዳዊትም በአምባይቱ ውስጥ ተቀመጠ፥ የዳዊትም ከተማ ብሎ ጠራት። ዳዊትም ዙሪያዋን ከሚሎ ጀምሮ ወደ ውስጥ ቀጠራት።
10 ፤ ዳዊትም እየበረታ ሄደ፤ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ።
11 ፤ የጢሮስም ንጉሥ ኪራም ወደ ዳዊት መልእክተኞችን የዝግባ እንጨትንም አናጢዎችንም ጠራቢዎችንም ላከ፤ ለዳዊትም ቤት ሠሩለት።
12 ፤ ዳዊትም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናው፥ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤልም መንግሥቱን ከፍ እንዳደረገ አወቀ።
13 ፤ ዳዊትም ከኬብሮን ከመጣ በኋላ ሌሎቹን ቁባቶቹንና ሚስቶቹን ከኢየሩሳሌም ወሰደ፤ ለዳዊትም ደግሞ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ተወለዱለት።
14 ፤ በኢየሩሳሌምም የተወለዱለት ስማቸው ይህ ነው፤ ሳሙስ፥
15 ፤ ሶባብ፥ ናታን፥ ሰሎሞን፥ ኢያቤሐር፥ ኤሊሱዔ፥
16 ፤ ናፌቅ፥ ያፍያ፥ ኤሊሳማ፥ ኤሊዳሄ፥ ኤሊፋላት።
17 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ዳዊት በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ እንደ ተቀባ ሰሙ፥ ፍልስጥኤማውያንም ሁሉ ዳዊትን ሊፈልጉ ወጡ፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ ወደ ምሽጉ ወረደ።
18 ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበትነው ሰፈሩ።
19 ፤ ዳዊትም። ወደ ፍልስጥኤማውያን ልውጣን? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም ዳዊትን። ፍልስጥኤማውያንን በእርግጥ በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና ውጣ አለው።
20 ፤ ዳዊትም ወደ በኣልፐራሲም መጣ፥ በዚያም መታቸውና። ውኃ እንዲያፈርስ እግዚአብሔር ጠላቶቼን በፊቴ አፈረሳቸው አለ። ስለዚህም የዚያን ስፍራ ስም በኣልፐራሲም ብሎ ጠራው።
21 ፤ ጣዖቶቻቸውንም በዚያ ተዉ፥ ዳዊትና ሰዎቹም ወሰዱአቸው።
22 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ደግሞ መጡ፥ በራፋይምም ሸለቆ ተበትነው ሰፈሩ።
23 ፤ ዳዊትም እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እርሱም። በኋላቸው ዞረህ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት ግጠማቸው እንጂ አትውጣ።
24 ፤ በሾላውም ዛፍ ራስ ውስጥ የሽውሽውታ ድምፅ ስትሰማ፥ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ለመምታት በፊትህ ወጥቶ ይሆናልና በዚያን ጊዜ ቸኵል አለው።
25 ፤ ዳዊትም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ከገባዖንም እስከ ጌዝር ድረስ ፍልስጥኤማውያንን መታ።