ምዕራፍ 6

ዳዊትም ዳግም ከእስራኤል የተመረጡትን ሠላሳ ሺህ ያህል ሰው ሰበሰበ።
2 ፤ ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ በይሁዳ ካለች ከበኣል ተነሥተው በኪሩቤል ላይ በተቀመጠ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም የተጠራውን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ያመጡ ዘንድ ሄዱ።
3 ፤ የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሰረገላ ላይ ጫኑ፥ በኮረብታውም ላይ ከነበረው ከአሚናዳብ ቤት አመጡት፤ የአሚናዳብ ልጆችም ዖዛ እና አሒዮ አዲሱን ሰረገላ ይነዱ ነበር።
4 ፤ በኮረብታውም ላይ ከነበረው ከአሚናዳብ ቤት የእግዚአብሔርን ታቦት ባመጡ ጊዜ አሒዮ በታቦቱ ፊት ይሄድ ነበር።
5 ፤ ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ በቅኔና በበገና በመሰንቆም በከበሮም በነጋሪትና በጸናጽል በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር።
6 ፤ ወደ ናኮንም አውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ ይፋንኑ ነበርና ዖዛ እጁን ዘርግቶ የእግዚአብሔርን ታቦት ያዘ።
7 ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በዖዛ ላይ ነደደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ድፍረቱ በዚያው ቀሠፈው፤ በእግዚአብሔርም ታቦት አጠገብ በዚያው ሞተ።
8 ፤ እግዚአብሔርም ዖዛን ስለ ሰበረው ዳዊት አዘነ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የዚያ ስፍራ ስም የዖዛ ስብራት ተብሎ ተጠራ።
9 ፤ በዚያም ቀን ዳዊት እግዚአብሔርን ፈራና። የእግዚአብሔር ታቦት ወደ እኔ እንዴት ይመጣል? አለ።
10 ፤ ዳዊትም የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እርሱ ወደ ዳዊት ከተማ ያመጣው ዘንድ አልወደደም፤ ዳዊትም በጌት ሰው በአቢዳራ ቤት አገባው።
11 ፤ የእግዚአብሔርም ታቦት በጌት ሰው በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ያህል ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርም አቢዳራንና ቤቱን ሁሉ ባረከ።
12 ፤ ንጉሡ ዳዊትም እግዚአብሔር የአቢዳራን ቤትና የነበረውን ሁሉ ስለ እግዚአብሔር ታቦት እንደ ባረከ ሰማ። ዳዊትም ሄዶ የእግዚአብሔርን ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ዳዊት ከተማ በደስታ አመጣው።
13 ፤ የእግዚአብሔርንም ታቦት የተሸከሙ ስድስት እርምጃ በሄዱ ጊዜ አንድ በሬና አንድ ፍሪዳ ሠዋ።
14 ፤ ዳዊትም በሙሉ ኃይሉ በእግዚአብሔር ፊት ይዘፍን ነበር፤ ዳዊትም የበፍታ ኤፉድ ለብሶ ነበር።
15 ፤ ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ ሆ እያሉ ቀንደ መለከትም እየነፉ የእግዚአብሔርን ታቦት አመጡ።
16 ፤ የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በገባ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፥ ንጉሡም ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልልና ሲዘፍን አየች፤ በልብዋም ናቀችው።
17 ፤ የእግዚአብሔርንም ታቦት አገቡ፥ ዳዊትም በተከለለት ድንኳን ውስጥ በስፍራው አኖሩት፤ ዳዊትም የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕትን በእግዚአብሔር ፊት አሳረገ።
18 ፤ ዳዊትም የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕት ማሳረግ ከፈጸመ በኋላ ሕዝቡን በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም መረቀ።
19 ፤ ለሕዝቡም ሁሉ ለእስራኤል ወገን ለወንዱም ለሴቱም ለእያንዳንዱ አንዳንድ እንጀራ አንዳንድም የሥጋ ቍራጭ አንዳንድም የዘቢብ ጥፍጥፍ አከፋፈለ። ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ ወደ ቤቱ ሄደ።
20 ፤ ዳዊትም ቤተ ሰቡን ሊመርቅ ተመለሰ። የሳኦልም ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ለመቀበል ወጣችና። ምናምንቴዎች እርቃናቸውን እንደሚገልጡ የእስራኤል ንጉሥ በባሪያዎቹ ቈነጃጅት ፊት እርቃኑን በመግለጡ ምንኛ የተከበረ ነው! አለችው።
21 ፤ ዳዊትም ሜልኮልን። በእግዚአብሔር ፊት ዘፍኛለሁ፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ከአባትሽና ከቤቱ ሁሉ ይልቅ የመረጠኝ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት እጫወታለሁ።
22 ፤ አሁንም ከሆንሁት ይልቅ የተናቅሁ እሆናለሁ፥ በዓይንሽም እዋረዳለሁ፤ ነገር ግን በተናገርሽው ቈነጃጅት ዘንድ እከብራለሁ አላት።
23 ፤ የሳኦልም ልጅ ሜልኮል እስከ ሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም።፤