ምዕራፍ 3

በሳኦል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል ብዙ ዘመን ጦርነት ሆነ፤ የዳዊት ቤት እየበረታ፥ የሳኦል ቤት ግን እየደከመ የሚሄድ ሆነ።
2 ፤ ለዳዊትም ወንድ ልጆች በኬብሮን ተወለዱለት፤ በኵሩም ከኢይዝራኤላዊቱ ከአኪናሆም የተወለደው አምኖን ነበረ።
3 ፤ ሁለተኛውም የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረች ከአቢግያ የተወለደው ዶሎሕያ ነበረ። ሦስተኛውም ከጌሹር ንጉሥ ከተልማይ ልጅ ከመዓካ የተወለደው አቤሴሎም ነበረ።
4 ፤ አራተኛውም የአጊት ልጅ አዶንያስ፥ አምስተኛውም የአቢጣል ልጅ ሰፋጥያስ ነበረ።
5 ፤ ስድስተኛውም የዳዊት ልጅ ሚስት የዔግላ ልጅ ይትረኃም ነበረ። እነዚህም ለዳዊት በኬብሮን ተወለዱለት።
6 ፤ በሳኦል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል ጦርነት ሆኖ ሳለ አበኔር በሳኦል ቤት ይበረታ ነበር።
7 ፤ ለሳኦልም የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ የተባለች ቁባት ነበረችው፤ ኢያቡስቴም አበኔርን። ወደ አባቴ ቁባት ለምን ገባህ? አለው።
8 ፤ አበኔርም በኢያቡስቴ ቃል እጅግ ተቈጥቶ እንዲህ አለ። እኔ ለአባትህ ለሳኦል ቤት ለወንድሞቹም ለዘመዶቹም ቸርነት አድርጌአለሁ፥ አንተንም ለዳዊት እጅ አሳልፌ አልሰጠሁም፤ አንተም ዛሬ ከዚህች ሴት ጋር ስለ ሠራሁት ኃጢአት ትከስሰኛለህ፤ በውኑ እኔ የውሻ ራስ ነኝን?
9
10 ፤ መንግሥትን ከሳኦል ቤት ያወጣ ዘንድ የዳዊትንም ዙፋን በእስራኤልና በይሁዳ ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ከፍ ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር ለዳዊት እንደ ማለለት እንዲሁ ከእርሱ ጋር ባላደርግ እግዚአብሔር በአበኔር ይህን ያድርግበት ይህንም ይጨምርበት።
11 ፤ ኢያቡስቴም አበኔርን ይፈራው ነበርና አንዳች ይመልስለት ዘንድ አልቻለም።
12 ፤ አበኔርም ለዳዊት። ምድሪቱ ለማን ናት? ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን አድርግ፥ እጄም ከአንተ ጋር ትሆናለች፥ እስራኤልንም ሁሉ ወደ አንተ እመልሰዋለሁ ብለው ይነግሩት ዘንድ መልእክተኞች ሰደደለት።
13 ፤ ዳዊትም። ይሁን፥ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር ከአንተ እሻለሁ፤ ፊቴን ለማየት በመጣህ ጊዜ፥ የሳኦልን ልጅ ሜልኮልን ካላመጣህልኝ ፊቴን አታይም አለ።
14 ፤ ዳዊትም ወደ ሳኦል ልጅ ወደ ኢያቡስቴ። በመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ያጨኋትን ሚስቴን ሜልኮልን ስጠኝ ብሎ መልእክተኞችን ሰደደ።
15 ፤ ኢያቡስቴም ልኮ ከሌሳ ልጅ ከባልዋ ከፈልጢኤል ወሰዳት።
16 ፤ ባልዋም እያለቀሰ ከእርስዋ ጋር ሄደ፥ እስከ ብራቂም ድረስ ተከተላት። አበኔርም። ሂድ፥ ተመለስ አለው፤ እርሱም ተመለሰ።
17 ፤ አበኔርም ለእስራኤል ሽማግሌዎች። አስቀድሞ ዳዊት በእናንተ ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ ፈልጋችሁ ነበር።
18 ፤ እግዚአብሔርም ስለ ዳዊት። በባሪያዬ በዳዊት እጅ ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅና ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ አድናለሁ ብሎ ተናግሮአልና እንግዲህ አሁን አድርጉ ብሎ ነገራቸው።
19 ፤ አበኔርም ደግሞ በብንያም ወገን ጆሮ ተናገረ፤ አበኔርም ደግሞ በእስራኤልና በብንያም ቤት ሁሉ መልካም የነበረውን ለዳዊት ሊነግረው ወደ ኬብሮን ሄደ።
20 ፤ አበኔርም ከሀያ ሰዎች ጋር ወደ ዳዊት ወደ ኬብሮን መጣ። ዳዊትም ለአበኔርና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሰዎች ግብዣ አደረገላቸው።
21 ፤ አበኔርም ዳዊትን። ተነሥቼ ልሂድ፥ ከአንተ ጋርም ቃል ኪዳን እንዲያደርጉ፥ ነፍስህም እንደ ወደደች ሁሉን እንድትገዛ እስራኤልን ሁሉ ለጌታዬ ለንጉሥ ልሰብስብ አለው። ዳዊትም አበኔርን አሰናበተው፥ በደኅናም ሄደ።
22 ፤ በዚያን ጊዜም የዳዊት ባሪያዎችና ኢዮአብ ከዘመቻ ታላቅ ምርኮ ይዘው መጡ። አበኔር ግን ዳዊት አሰናብቶት በደኅና ሄዶ ነበር እንጂ በኬብሮን አልነበረም።
23 ፤ ኢዮአብና ከእርሱም ጋር የነበረ ጭፍራ ሁሉ በመጡ ጊዜ። የኔር ልጅ አበኔር ወደ ንጉሥ መጣ፥ አሰናበተውም በደኅናውም ሄደ ብለው ሰዎች ለኢዮአብ ነገሩት።
24 ፤ ኢዮአብም ወደ ንጉሥ ገብቶ። ምን አደረግህ? እነሆ፥ አበኔር መጥቶልህ ነበር፤ በደኅና እንዲሄድ ስለ ምን አሰናበትኸው?
25 ፤ የኔር ልጅ አበኔር ያታልልህ ዘንድ፥ መውጫህንና መግቢያህንም ያውቅ ዘንድ፥ የምታደርገውንም ነገር ሁሉ ያስተውል ዘንድ እንደ መጣ አታውቅምን? አለው።
26 ፤ ኢዮአብም ከዳዊት በወጣ ጊዜ መልእክተኞችን ከአበኔር በኋላ ላከ፥ ከሴይርም ጕድጓድም መለሱት። ዳዊት ግን ይህን አላወቀም።
27 ፤ አበኔርም ወደ ኬብሮን በተመለሰ ጊዜ ኢዮአብ በበር ውስጥ በቈይታ ይናገረው ዘንድ ወደ አጠገቡ ወሰደው፤ በዚያም ለወንድሙ ለአሣሄል ደም ተበቅሎ ሆዱን መታው፥ ሞተም።
28 ፤ በኋላም ዳዊት ይህ ነገር እንደ ተደረገ በሰማ ጊዜ። ከኔር ልጅ ከአበኔር ደም በእግዚአብሔር ዘንድ ለዘላለም እኔ ንጹሕ ነኝ፥ መንግሥቴም ንጹሕ ነው፤
29 ፤ በኢዮአብ ራስ ላይና በአባቱ ቤት ሁሉ ላይ ይምጣበት፤ በኢዮአብም ቤት ፈሳሽ ነገር ያለበት ወይም ለምጻም ወይም አንካሳ ወይም በሰይፍ የሚወድቅ ወይም እንጀራ የሌለው ሰው አይታጣ አለ።
30 ፤ ኢዮአብና ወንድሙ አቢሳም በሰልፍ በገባዖን ወንድማቸው አሣሄልን ገድሎ ነበርና አበኔርን ገደሉት።
31 ፤ ዳዊትም ኢዮአብንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ሁሉ። ልብሳችሁን ቅደዱ፥ ማቅም ልበሱ፥ በአበኔርም ፊት አልቅሱ አላቸው። ንጉሡም ዳዊት ከቃሬዛው በኋላ ሄደ።
32 ፤ አበኔርንም በኬብሮን ቀበሩት፤ ንጉሡም ድምፁን ከፍ አድርጎ በአበኔር መቃብር አጠገብ አለቀሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ አለቀሱ። ንጉሡም ለአበኔር።
33 ፤ አበኔር ሰነፍ እንደሚሞት ይምታልን?
34 ፤ እጅህ አልታሰረም፥ እግርህም በሰንሰለት አልተያዘም፤ ሰው በዓመፀኞች ፊት እንደሚወድቅ አንተ እንዲሁ ወደቅህ ብሎ የልቅሶ ቅኔ ተቀኘለት። ሕዝቡም ሁሉ ዋይታ አብዝተው አለቀሱ።
35 ፤ ሕዝቡም ሁሉ ገና ሳይመሽ ዳዊትን እንጀራ ይበላ ዘንድ ሊጋብዙት መጡ፤ ዳዊት ግን። ፀሐይ ሳትጠልቅ እንጀራ ወይም ሌላ ነገር ብቀምስ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፥ ይህንም ይጨምርብኝ ብሎ፤ ማለ።
36 ፤ ሕዝቡም ሁሉ ይህን ተመለከቱ፥ ደስ አሰኛቸውም፤ በሕዝቡም ሁሉ ፊት ንጉሥ ያደረገው ሁሉ ደስ አሰኛቸው።
37 ፤ በዚያም ቀን ሕዝቡ ሁሉ እስራኤልም ሁሉ የኔር ልጅ የአበኔር ሞት ከንጉሡ ዘንድ እንዳልሆነ አወቁ።
38 ፤ ንጉሡም ባሪያዎቹን። ዛሬ በእስራኤል ዘንድ መኰንንና ታላቅ ሰው እንደ ወደቀ አታውቁምን?
39 ፤ እኔም ዛሬ ምንም ለመንገሥ የተቀባሁ ብሆን ደካማ ነኝ፤ እነዚህም ሰዎች የጽሩያ ልጆች በርትተውብኛል፤ እግዚአብሔር ክፋት በሠራ ላይ እንደ ክፋቱ ይመልስበት አላቸው።