ምዕራፍ 22

ዳዊትም እግዚአብሔር ከሳኦል እጅና ከጠላቶቹ እጅ ሁሉ ባዳነው ቀን የዚህን ቅኔ ቃል ለእግዚአብሔር ተናገረ።
2 ፤ እንዲህም አለ። እግዚአብሔር ዓለቴ አምባዬ መድኃኒቴ ነው፤
3 ፤ እግዚአብሔር ጠባቂዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ፤ ጋሻዬና የረድኤቴ ቀንድ፥ መጠጊያዬና መሸሸጊያዬ፥ መድኃኒቴ ሆይ፥ ከግፍ ሥራ ታድነኛለህ።
4 ፤ ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ ከጠላቶቼም እድናለሁ።
5 ፤ የሞት ጣር ያዘኝ፤ የዓመፅ ፈሳሽም አስፈራኝ፤
6 ፤ የሲኦል ጣር ከበበኝ፤ የሞት ወጥመድ ደረሰብኝ።
7 ፤ በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፥ ወደ አምላኬም ጮኽሁ፤ ከመቅደሱም ቃሌን ሰማኝ፥ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ።
8 ፤ ምድርም ተንቀጠቀጠች፥ ተናወጠችም፥ የሰማዮችም መሠረቶች ተነቃነቁ፤ እግዚአብሔርም ተቈጥቶአልና ተንቀጠቀጡ።
9 ፤ ከቍጣው ጢስ ወጣ፥ ከአፉም የሚበላ እሳት ነደደ፤ ፍምም ከእርሱ በራ።
10 ፤ ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ፥ ወረደም፤ ጨለማም ከእግሩ በታች ነበረ።
11 ፤ በኪሩብም ላይ ተቀምጦ በረረ፤ በነፋስም ክንፍ ሆኖ ታየ፤
12 ፤ መሰወርያውን ጨለማ፥ በዙሪያውም የነበረውን ድንኳን፥ በደመና ውስጥ የነበረ የጨለማ ውኃ አደረገ።
13 ፤ በፊቱም ካለው ብርሃን የተነሣ ፍም ተቃጠለ።
14 ፤ እግዚአብሔርም ከሰማያት አንጐደጐደ፥ ልዑልም ቃሉን ሰጠ፤
15 ፤ ፍላጻውን ላከ፥ በተናቸውም መብረቆችን ላከ፥ አወካቸውም።
16 ፤ ከእግዚአብሔር ዘለፋ፥ ከመዓቱም መንፈስ እስትንፋስ የተነሣ፥ የባሕር ፈሳሾች ታዩ፥ የዓለም መሠረቶችም ተገለጡ።
17 ፤ ከላይ ሰደደ፥ ወሰደኝም፤ ከብዙ ውኆችም አወጣኝ።
18 ፤ ከብርቱዎች ጠላቶቼ፥ ከሚጠሉኝም አዳነኝ፤ በርትተውብኝ ነበርና።
19 ፤ በመከራዬ ቀን ደረሱብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ደገፋዬ ሆነ።
20 ፤ ወደ ሰፊ ስፍራም አወጣኝ፤ ወድዶኛልና አዳነኝ።
21 ፤ እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ ይከፍለኛል፤ እንደ እጄ ንጽሕና ይመልስልኛል፤
22 ፤ የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፥ በአምላኬም አላመፅሁምና።
23 ፤ ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነበረና፤ ከሥርዓቱም አልራቅሁምና።
24 ፤ በእርሱ ዘንድ ቅን ነበርሁ፥ ከኃጢአቴም ተጠበቅሁ።
25 ፤ እግዚአብሔርም እንደ ጽድቄ፥ እንደ እጄም ንጽሕና በዓይኖቹ ፊት መለሰልኝ።
26 ፤ ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፤ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤
27 ፤ ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ።
28 ፤ አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህና፤ የትዕቢተኞችን ዓይን ግን ታዋርዳለህ።
29 ፤ አቤቱ፥ አንተ መብራቴ ነህና፤ እግዚአብሔርም ጨለማዬን ያበራል።
30 ፤ በአንተ ኃይል በጭፍራ ላይ እሮጣለሁና፤ በአምላኬም ቅጥሩን እዘልላለሁና።
31 ፤ የአምላክ መንገድ ፍጹም ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው፤ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው።
32 ፤ ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን ነው? ከአምላካችንስ በቀር አምባ ማን ነው?
33 ፤ ኃይልን የሚያስታጥቀኝ፥ መንገዴንም የሚያቃና፥
34 ፤ እግሮቼን እንደ ብሆር እግሮች የሚያበረታ፥ በኮረብቶችም የሚያቆመኝ እግዚአብሔር ነው።
35 ፤ እጆቼን ሰልፍ ያስተምራል፤ በክንዴም የናስ ቀስት እገትራለሁ።
36 ፤ የማዳንህንም ጋሻ ሰጠኸኝ፤ ተግሣጽህም አሳደገኝ።
37 ፤ አረማመዴን በበታቼ አሰፋህ፥ እግሮቼም አልተንሸራተቱም።
38 ፤ ጠላቶቼን አሳድዳቸዋለሁ፥ አጠፋቸውማለሁ፤ እስካጠፋቸውም ድረስ አልመለስም።
39 ፤ አስጨንቃቸዋለሁ መቆምም አይችሉም፥ ከእግሬም በታች ይወድቃሉ።
40 ፤ ለሰልፍም ኃይልን ታስታጥቀኛለህ፤ በላዬ የቆሙትን በበታቼ ታስገዛቸዋለህ።
41 ፤ የጠላቶቼን ጀርባ ሰጠኸኝ፥ የሚጠሉኝንም አጠፋሃቸው።
42 ፤ ጮኹ፥ የሚረዳቸውም አልነበረም፤ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ አልሰማቸውምም።
43 ፤ እንደ ምድር ትቢያ ፈጨኋቸው፤ እንደ አደባባይም ጭቃ ረገጥኋቸው፥ ደቀደቅኋቸውም።
44 ፤ ከሕዝብ ክርክር ታድነኛለህ፤ የአሕዛብም ራስ አድርገህ ትሾመኛለህ፤ የማላውቀው ሕዝብም ይገዛልኛል።
45 ፤ የባዕድ ልጆች ደለሉኝ፤ በጆሮ ሰምተው ተገዙልኝ።
46 ፤ የባዕድ ልጆች እየጠፉ ይሄዳሉ፤ ከተዘጉ ስፍሮች እየተንቀጠቀጡ ይወጣሉ።
47 ፤ እግዚአብሔር ሕያው ነው፥ ጠባቂዬም ቡሩክ ነው፤ የመድኃኒቴ ጠባቂ አምላኬ ከፍ ከፍ ይበል፤
48 ፤ በቀሌን የሚመልስልኝ አምላክ፥ አሕዛብን በበታቼ የሚያስገዛ፥
49 ፤ ከጠላቶቼ የሚያወጣኝ እርሱ ነው፤ በእኔም ላይ ከቆሙ ከፍ ከፍ ታደርገኛለህ፤ ከግፈኛ ሰው ታድነኛለህ።
50 ፤ አቤቱ፥ ስለዚህ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ ለስምህም እዘምራለሁ።
51 ፤ የንጉሡን መድኃኒት ታላቅ ያደርጋል፤ ቸርነቱንም ለቀባው፥ ለዳዊትና ለዘሩ፥ ለዘላለም ይሰጣል።