ምዕራፍ 9

ዳዊትም። ስለ ዮናታን ቸርነት አደርግለት ዘንድ ከሳኦል ቤት አንድ ሰው ቀርቶአልን? አለ።
2 ፤ ከሳኦልም ቤት ሲባ የሚባል አንድ ባሪያ ነበረ፥ ወደ ዳዊትም ጠሩት፤ ንጉሡም። አንተ ሲባ ነህን? አለው። እርሱም። እኔ ባሪያህ ነኝ አለ።
3 ፤ ንጉሡም። የእግዚአብሔርን ቸርነት አደርግለት ዘንድ ከሳኦል ቤት አንድ ሰው አልቀረምን? አለ። ሲባም ንጉሡን። እግሩ ሽባ የሆነ አንድ የዮናታን ልጅ አለ አለው።
4 ፤ ንጉሡም። ወዴት ነው? አለው፤ ሲባም ንጉሡን። እነሆ፥ እርሱ በሎዶባር በዓሚኤል ልጅ በማኪር ቤት አለ አለው።
5 ፤ ንጉሡም ዳዊት ልኮ ከሎዶባር ከዓሚኤል ልጅ ከማኪር ቤት አስመጣው።
6 ፤ የሳኦልም ልጅ የዮናታን ልጅ ሜምፊቦስቴ ወደ ዳዊት መጣ፥ በግምባሩም ወድቆ እጅ ነሣ፤ ዳዊትም። ሜምፊቦስቴ ሆይ፥ አለ፤ እርሱም። እነሆኝ ባሪያህ አለ።
7 ፤ ዳዊትም። ስለ አባትህ ስለ ዮናታን ቸርነት ፈጽሜ አደርግልሃለሁና አትፍራ፤ የአባትህንም የሳኦልን ምድር ሁሉ እመልስልሃለሁ፥ አንተም ሁልጊዜ ከገበታዬ እንጀራ ትበላለህ አለው።
8 ፤ እርሱም። የሞተ ውሻ ወደምመስል ወደ እኔ የተመለከትህ እኔ ባሪያህ ምንድር ነኝ? ብሎ እጅ ነሣ።
9 ፤ ንጉሡም የሳኦልን ባሪያ ሲባን ጠርቶ። ለሳኦልና ለቤቱ ሁሉ የነበረውን ሁሉ ለጌታህ ልጅ ሰጥቻለሁ።
10 ፤ አንተና ልጆችህ ሎሌዎችህም ምድሩን እረሱለት፤ ለጌታህም ልጅ እንጀራ ይሆነው ዘንድ ፍሬውን አግባ፤ የጌታህ ልጅ ሜምፊቦስቴ ግን ሁልጊዜ ከገበታዬ ይበላል አለው። ለሲባም አሥራ አምስት ልጆችና ሀያ ባሪያዎች ነበሩት።
11 ፤ ሲባም ንጉሡን። ጌታዬ ንጉሡ ባሪያውን እንዳዘዘ እንዲሁ ባሪያህ ያደርጋል አለው። ሜምፊቦስቴም ከንጉሡ ልጆች እንደ አንዱ ከዳዊት ገበታ ይበላ ነበር።
12 ፤ ለሜምፊቦስቴም ሚካ የተባለ ታናሽ ልጅ ነበረው። በሲባም ቤት ያሉ ሁሉ ለሜምፊቦስቴ ያገለግሉ ነበር።
13 ፤ ሜምፊቦስቴም ከንጉሥ ገበታ ሁልጊዜ እየበላ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ነበር፤ ሁለት እግሩም ሽባ ነበረ።