ምዕራፍ 21

በዳዊትም ዘመን ሦስት ዓመት ያህል ቀጥሎ ራብ ሆነ፤ ዳዊትም የእግዚአብሔርን ፊት ጠየቀ። እግዚአብሔርም። የገባዖንን ሰዎች ስለ ገደለ በሳኦልና በቤቱ ላይ ደም አለበት አለ።
2 ፤ ንጉሡም የገባዖንን ሰዎች ጠራ፤ የገባዖን ሰዎችም ከአሞራውያን የተረፉ ነበሩ እንጂ ከእስራኤል ልጆች ወገን አልነበሩም፤ የእስራኤልም ልጆች ምለውላቸው ነበር፤ ሳኦል ግን ለእስራኤል ልጆችና ለይሁዳ ስለ ቀና ሊገድላቸው ወድዶ ነበር።
3 ፤ ዳዊትም የገባዖንን ሰዎች። የእግዚአብሔርን ርስት ትባርኩ ዘንድ ምን ላድርግላችሁ? ማስተስረያውስ ምንድር ነው? አላቸው።
4 ፤ የገባዖን ሰዎችም። በእኛና በሳኦል ወይም በእኛና በቤቱ መካከል ያለው የብርና የወርቅ ነገር አይደለም፤ ከእስራኤልም ወገን እኛ የምንገድለው የለም አሉት። እርሱም። የምትናገሩትን አደርግላችኋለሁ አለ።
5 ፤ ንጉሡንም። እኛን ካጠፋ፥ በእስራኤልም ዳርቻ ሁሉ እንዳንቀመጥ መፍረሳችንን
6 ፤ ካሰበው ሰው ልጆች ሰባት ሰዎች አሳልፈህ ስጠንና ከእግዚአብሔር በተመረጠው በሳኦል አገር በጊብዓ ለእግዚአብሔር እንሰቅላቸዋለን አሉት። ንጉሡም። እሰጣችኋለሁ አለ።
7 ፤ ንጉሡም በሳኦል ልጅ በዮናታንና በዳዊት መካከል ስለ ነበረው ስለ እግዚአብሔር መሐላ የሳኦልን ልጅ የዮናታንን ልጅ ሜምፊቦስቴን አዳነ።
8 ፤ ንጉሡም ለሳኦል የወለደቻቸውን የኢዮሄል ልጅ የሪጽፋን ሁለቱን ልጆች ሄርሞንንና ሜምፊቦስቴን ለመሓላታዊውም ለቤርዜሊ ልጅ ለኤስድሪኤል የወለደቻቸውን የሳኦልን ልጅ የሜሮብን አምስቱን ልጆች ወሰደ፥
9 ፤ ለገባዖንም ሰዎች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ በእግዚአብሔርም ፊት በተራራው ላይ ሰቀሉአቸው፥ ሰባቱም በአንድነት ወደቁ፤ እህል በሚታጨድበት ወራት በገብሱ መከር መጀመሪያ ተገደሉ።
10 ፤ የኢዮሄልም ልጅ ሪጽፋ ማቅ ወስዳ ከመከር ወራት ጀምሮ ዝናብ ከሰማይ እስኪዘንብ ድረስ በድንጋይ ላይ ዘረጋችው፤ በቀንም ወፎች በሌሊትም አራዊት ያርፉባቸው ዘንድ አልተወችም።
11 ፤ የሳኦልም ቁባት የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ያደረገችውን ለዳዊት ነገሩት።
12 ፤ ዳዊትም ሄደ፥ ሳኦልንም በጊልቦዓ በገደሉ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን ከሰቀሉአቸው ስፍራ ከቤትሳን አደባባይ ከሰረቁት ከኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት ወሰደ፤
13 ፤ ከዚያም የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት ይዞ መጣ፤ የተሰቀሉትንም ሰዎች አጥንት ሰበሰቡ።
14 ፤ የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት በብንያም አገር በጼላ በአባቱ በቂስ መቃብር ቀበሩት፤ ንጉሡም ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ። ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር ስለ አገሩ የተለመነውን ሰማ።
15 ፤ በፍልስጥኤማውያንና በእስራኤልም መካከል ደግሞ ሰልፍ ነበረ፤ ዳዊትም ከእርሱም ጋር ባሪያዎቹ ወረዱ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ተዋጉ፤ ዳዊትም ደከመ።
16 ፤ ከራፋይም ወገን የነበረው ይሽቢብኖብ ዳዊትን ይገድል ዘንድ አሰበ፤ የጦሩም ሚዛን ክብደት ሦስት መቶ ሰቅል ናስ ነበረ፥ አዲስም የጦር መሣሪያ ታጥቆ ነበር።
17 ፤ የጽሩያም ልጅ አቢሳ አዳነው፥ ፍልስጥኤማዊውንም መትቶ ገደለው። ያንጊዜም የዳዊት ሰዎች። አንተ የእስራኤልን መብራት እንዳታጠፋ ከእንግዲህ ወዲህ ከእኛ ጋር ለሰልፍ አትወጣም ብለው ማሉለት።
18 ፤ ከዚህም በኋላ እንደ ገና በጎብ ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰልፍ ሆነ፥ ኩሳታዊውም ሴቦካይ ከራፋይም ወገን የነበረውን ሳፍን ገደለ።
19 ፤ ደግሞም በጎብ ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰልፍ ነበረ፤ የቤተ ልሔማዊውም የየዓሬኦርጊም ልጅ ኤልያናን የጦሩ የቦ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የነበረውን የጌት ሰው ጎልያድን ገደለ።
20 ፤ ደግሞም በጌት ላይ ሰልፍ ሆነ፤ በዚያም በእጁና በእግሩ ስድስት ስድስት ሁላሁሉ ሀያ አራት ጣቶች የነበሩት አንድ ረጅም ሰው ነበረ፤ እርሱ ደግሞ ከራፋይም የተወለደ ነበረ።
21 ፤ እስራኤልንም በተገዳደረ ጊዜ የዳዊት ወንድም የሣማ ልጅ ዮናታን ገደለው።
22 ፤ እነዚያም አራቱ በጌት ውስጥ ከራፋይም የተወለዱ ነበሩ፤ በዳዊትም እጅ በባሪያዎቹም እጅ ወደቁ።