መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29


ምዕራፍ 14

የጢሮስም ንጉሥ ኪራም ቤት ይሠሩለት ዘንድ መልእክተኞችን የዝግባ እንጨትንም ጠራቢዎችንም አናጢዎችንም ወደ ዳዊት ላከ።
2 ፤ ስለ ሕዝቡም ስለ እስራኤል መንግሥቱ ከፍ ብሎአልና እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናው ዳዊት አወቀ።
3 ፤ ዳዊትም በኢየሩሳሌም ሚስቶችን ጨምሮ ሌሎችን ወንዶችንና ሴቶችን ልጆች ወለደ።
4 ፤ በኢየሩሳሌምም የወለዳቸው የልጆቹ ስም ይህ ነው፤ ሳሙስ፥
5 ፤ ሶባብ፥ ናታን፥ ሰሎሞን፥ ኢያቤሐር፥ ኤሊሱዔ፥
6 ፤ ኤሊፋላት፥ ኖጋ፥ ናፌቅ፥ ያፍያ፥
7 ፤ ኤሊሳማ፥ ኤሊዳሄ፥ ኤሊፋላት።
8 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ንጉሥ ሆኖ እንደተቀባ ሰሙ፥ ፍልስጥኤማውያንም ሁሉ ዳዊትን ሊፈልጉ ወጡ፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ ሊጋጠማቸው ወጣ።
9 ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው በራፋይም ሸለቆ አደጋ ጣሉ።
10 ፤ ዳዊትም። ወደ ፍልስጥኤማውያን ልውጣን? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም። በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና ውጣ አለው።
11 ፤ ወደ በአልፐራሲም ወጡ፥ በዚያም ዳዊት መታቸው። ዳዊትም። ውኃ እንዲያፈርስ እግዚአብሔር ጠላቶቼን በእጄ አፈረሳቸው አለ። ስለዚህም የዚያን ስፍራ ስም በአልፐራሲም ብለው ጠሩት።
12 ፤ አማልክቶቻቸውንም በዚያ ተዉ፤ ዳዊትም አዘዘ፥ በእሳትም አቃጠሏቸው።
13 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ደግሞ በሸለቆው አደጋ ጣሉ።
14 ፤ ዳዊትም እንደ ገና እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም። ከእነርሱ ዞረህ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት ግጠማቸው እንጂ ወደ እነርሱ አትውጣ።
15 ፤ በሾላውም ዛፍ እራስ ውስጥ የሽውሽውታ ድምፅ ስትሰማ የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ሊመታ እግዚአብሔር በፊትህ ይወጣልና በዚያን ጊዜ ወደ ሰልፍ ውጣ አለው።
16 ፤ ዳዊትም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ከገባዖንም ጀምሮ እስከ ጌዝር ድረስ የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ መቱት።
17 ፤ የዳዊትም ዝና በየአገሩ ሁሉ ወጣ፤ መፈራቱንም እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ አደረገው።