መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29


ምዕራፍ 19

ከዚህም በኋላ የአሞን ልጆች ንጉሥ ናዖስ ሞተ፥ ልጁም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
2 ፤ ዳዊትም። አባቱ ስላደረገልኝ ወረታ እኔ ለናዖስ ልጅ ለሐኖን ቸርነት አደርጋለሁ አለ። ዳዊትም አባቱ ስለ ሞተ ልያጽናናው መልእክተኞችን ላከ፤ የዳዊትም ባሪያዎች ሊያጽናኑት ወደ ሐኖን ወደ አሞን ልጆች ምድር መጡ።
3 ፤ የአሞን ልጆች አለቆች ግን ሐኖንን። ዳዊት አባትህን አክብሮ የሚያጽናኑህን ወደ አንተ የላከ ይመስልሃልን? ባሪያዎቹስ አገሪቱን ለመመርመር፥ ለማጥፋት፥ ለመሰለልም ወደ አንተ የመጡ አይደሉምን? አሉት።
4 ፤ ሐኖንም የዳዊትን ባሪያዎች ወስዶ አስላጫቸው፥ ልብሳቸውንም እስከ ወገባቸው ድረስ ከሁለት ቀድዶ ሰደዳቸው።
5 ፤ ወሬኞችም ሄደው በሰዎቹ ላይ የተደረገውን ለዳዊት አስታወቁት። ሰዎቹም በብዙ አፍረዋልና ተቀባዮች ላከ፤ ንጉሡም። ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ተቀመጡ፥ ከዚያም በኋላ ተመለሱ አለ።
6 ፤ የአሞንም ልጆች በዳዊት ዘንድ እንደ ተጠሉ ባዩ ጊዜ ሐኖንና የአሞን ልጆች ከመስጴጦምያ፥ ከአራምመዓካ፥ ከሱባ ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን ይቀጥሩ ዘንድ አንድ ሺህ መክሊት ብር ላኩ።
7 ፤ ሠላሳ ሁለትም ሺህ ሰረገሎች የመዓካንም ንጉሥ ሕዝቡንም ቀጠሩ፤ መጥተውም በሜድባ ፊት ለፊት ሰፈሩ። የአሞንም ልጆች ከየከተሞቻቸው ተሰብስበው ወደ ሰልፍ መጡ።
8 ፤ ዳዊትም ይህ በሰማ ጊዜ ኢዮአብንና የኃያላኑን ሠራዊት ሁሉ ላከ።
9 ፤ የአሞንም ልጆች ወጥተው በከተማይቱ በር አጠገብ ተሰለፉ፤ የመጡትም ነገሥታት ለብቻቸው በሜዳው ላይ በሩ።
10 ፤ ኢዮአብም በፊትና በኋላ ሰልፍ እንደ ከበበው ባየ ጊዜ ከእስራኤል ምርጥ ምርጦችን ሁሉ ለይቶ በሶርያውያን ላይ አሰለፋቸው።
11 ፤ የቀረውንም ሕዝብ ለወንድሙ ለአቢሳ ሰጠው፥ በአሞንም ልጆች ላይ ተሰለፉ።
12 ፤ እርሱም። ሶርያውያን ቢበረቱብኝ እርዳኝ፤ የአሞንም ልጆች ቢበረቱብህ እረዳሃለሁ።
13 ፤ አይዞህ፥ ስለ ሕዝባችንና ስለ አምላካችንም ከተሞች እንበርታ፤ እግዚአብሔርም ደስ ያሰኘውን ያድርግ አለ።
14 ፤ ኢዮአብና ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ለሰልፍ ወደ ሶርያውያን ፊት ቀረቡ፥ እነርሱም ከፊቱ ሸሹ።
15 ፤ የአሞንም ልጆች ሶርያውያን እንደ ሸሹ ባዩ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ከወንድሙ ከአቢሳ ፊት ሸሹ፥ ወደ ከተማይቱም ገቡ። ኢዮአብም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።
16 ፤ ሶርያውያንም በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ መልእክተኞች ልከው በወንዝ ማዶ የነበሩትን ሶርያውያን አስመጡ፤ የአድርአዛርም ሠራዊት አለቃ ሾፋክ በፊታቸው ነበረ።
17 ፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፥ ዮርዳኖስንም ተሻግሮ መጣባቸው፥ ከእነርሱም ጋር ተዋጋ፤ ዳዊትም በሶርያውያን ላይ በተሰለፈ ጊዜ እነርሱ ከእርሱ ጋር ተዋጉ።
18 ፤ ሶርያውያንም ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ሰባት ሺህ ሰረገለኞች፥ አርባ ሺህም እግረኞች ገደለ፥ የሠራዊቱንም አለቃ ሾፋክን ገደለ።
19 ፤ የአድርአዛርም ባሪያዎች በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ ከዳዊት ጋር ታረቁ፥ ገበሩለትም፤ ሶርያውያንም ከዚያ ወዲያ የአሞንን ልጆች ይረዱ ዘንድ እንቢ አሉ።