መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29


ምዕራፍ 22

ዳዊትም። ይህ የእግዚአብሔር ቤት ነው፥ ይህም ለእስራኤል ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነው መሠዊያ ነው አለ።
2 ፤ ዳዊትም በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች ይሰበስቡ ዘንድ አዘዘ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት ለመሥራት የሚወቀሩትን ድንጋዮች ይወቅሩ ዘንድ ጠራቢዎችን አኖረ።
3 ፤ ዳዊትም ለበሮቹ ሳንቃ ለሚሆኑ ለምስማርና ለመጠረቂያ ብዙ ብረት፥ ከብዛቱም የተነሣ የማይመዘን ናስ አዘጋጀ።
4 ፤ ሲዶናውያውንና የጢሮስ ሰዎች ብዙ የዝግባ እንጨት ወደ ዳዊት ያመጡ ነበርና ቍጥር ያሌላቸውን የዝግባ እንጨቶች አዘጋጀ።
5 ፤ ዳዊትም። ልጄ ሰሎሞን ታናሽና ለጋ ብላቴና ነው፥ ለእግዚአብሔርም የሚሠራው ቤት እጅግ ማለፊያና በአገሩ ሁሉ ስሙና ክብሩ እንዲጠራ ይሆን ዘንድ ይገባል፤ ስለዚህ አዘጋጅለታለሁ አለ። ዳዊትም ሳይሞት አስቀድሞ ብዙ አዘጋጀ።
6 ፤ ልጁንም ሰሎሞንን ጠርቶ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ይሠራ ዘንድ አዘዘው።
7 ፤ ዳዊትም ሰሎሞንን እንዲህ አለ። ልጄ ሆይ፥ እኔ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ቤት እሠራ ዘንድ በልቤ አስቤ ነበር።
8 ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ። እጅግ ደም አፍስሰሃል፥ ታላቅም ሰልፍ አድርገሃል፤ በፊቴ በምድር ላይ ብዙ ደም አፍስሰሃልና ለስሜ ቤት አትሠራም።
9 ፤ እነሆ፥ የዕረፍት ሰው የሚሆን ልጅ ይወለድልሃል፤ በዙሪያው ካሉ ከጠላቶቹ ሁሉ አሳርፈዋለሁ፤ ስሙ ሰሎሞን ይባላልና፥ በዘመኑም ሰላምንና ጸጥታን ለእስራኤል እሰጣለሁ።
10 ፤ እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፥ ልጅም ይሆነኛል፥ እኔም አባት እሆነዋለሁ፤ የመንግሥቱንም ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ።
11 ፤ አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን፤ ስለ አንተም እንደ ተናገረው ያከናውንልህ፥ የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ።
12 ፤ ብቻ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ሕግ ትጠብቅ ዘንድ እግዚአብሔር ጥበብንና ማስተዋልን ይስጥህ፥ በእስራኤልም ላይ ያሠልጥንህ።
13 ፤ እግዚአብሔር ስለ እስራኤል ሙሴን ያዘዘውን ሥርዓትና ፍርድ ታደርግ ዘንድ ብትጠነቀቅ በዚያን ጊዜ ይከናወንልሃል፤ አይዞህ፥ በርታ፤ አትፍራ፥ አትደንግጥም።
14 ፤ አሁንም፥ እነሆ፥ በድህነቴ ለእግዚአብሔር ቤት መቶ ሺህ መክሊት ወርቅና አንድ ሚሊዮን መክሊት ብር፥ ሚዛንም የሌላቸው ብዙ ናስና ብረት አዘጋጀሁ፤ ደግሞም እንጨትና ድንጋዮች አዘጋጀሁ፥ አንተም ከዚያ በላይ ጨምር።
15 ፤ በአንተም ዘንድ ብዙ ሠራተኞች፥ ድንጋይና እንጨት ወቃሪዎችና ጠራቢዎች፥ ሥራውንም ሁሉ ለማድረግ ጠቢባን ሰዎች ሁሉ አሉ።
16 ፤ የሚሠሩበት ወርቅና ብር ናስና ብረት ቍጥር የለውም፤ ተነሥተህ ሥራ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን።
17 ፤ ዳዊትም ደግሞ ልጁን ሰሎሞንን ያግዙ ዘንድ የእስራኤልን አለቆች ሁሉ እንዲህ ሲል አዘዛቸው።
18 ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር አይደለምን? በምድርም የሚቀመጡትን በእጄ አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ምድርም በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ፊት ተገዝታለችና በዙሪያችሁ ሁሉ ዕረፍትን ሰጥቶአችኋል።
19 ፤ አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትፈልጉ ዘንድ ልባችሁንና ነፍሳችሁን ስጡ፤ ለእግዚአብሔርም ስም ወደሚሠራው ቤት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦትና የእግዚአብሔርን ንዋየ ቅድሳት ታመጡ ዘንድ ተነሥታችሁ የአምላክን የእግዚአብሔርን መቅደስ ሥሩ።