መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29


ምዕራፍ 23

ዳዊትም በሸመገለ ጊዜ፥ ዕድሜንም በጠገበ ጊዜ ልጁን ሰሎሞንን በእስራኤል ላይ አነገሠው።
2 ፤ የእስራኤልንም አለቆች ሁሉ፥ ካህናቱንም፥ ሌዋውያኑንም ሰበሰበ።
3 ፤ ሌዋውያንም ከሠላሳ ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ወደ ላይ ተቈጠሩ፤ ቍጥራቸው በእያንዳንዱ ነፍስ ወከፍ ሠላሳ ስምንት ሺህ ነበረ።
4 ፤ ከእነዚህም ውስጥ የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ የሚያሠሩት ሀያ አራት ሺህ ነበሩ፤ ስድስቱ ሺህም አለቆችና ፈራጆች ነበሩ።
5 ፤ አራቱ ሺህም በረኞች ነበሩ፤ አራቱ ሺህም ለምስጋና በተሠሩት በዜማ ዕቃዎች እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር።
6 ፤ ዳዊትም እንደ ሌዊ ልጆች እንደ ጌድሶንና እንደ ቀዓት እነደ ሜራሪም በየሰሞናቸው ከፈላቸው።
7 ፤ ከጌድሶናውያን ለአዳንና ሰሜኢ ነበሩ።
8 ፤ የለአዳን ልጆች አለቃው ይሒኤል፥ ዜቶም፥ ኢዮኤል ሦስት ነበሩ።
9 ፤ የሰሜኢ ልጆች ሰሎሚት፥ ሐዝኤል፥ ሐራን ሦስት ነበሩ። እነዚህ የለአዳን አባቶች ቤቶች አለቆች ነበሩ።
10 ፤ የሰሜኢ ልጆች ኢኢት፥ ዚዛ፥ የዑስ፥ በሪዓ ነበሩ። እነዚህ አራቱ የሰሜኢ ልጆች ነበሩ።
11 ፤ አለቃው ኢኢት ነበረ፤ ሁለተኛው ዚዛ ነበረ፤ የዑስና በሪዓ ግን ብዙ ልጆች አልነበሩአቸውም፤ ስለዚህ እንደ አንድ አባት ቤት ሆነው ተቈጠሩ።
12 ፤ የቀአት ልጆች እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል አራት ነበሩ።
13 ፤ የእንበረም ልጆች አሮንና ሙሴ ነበሩ፤ አሮንም ከሁሉ በላይ የተቀደሰ ይሆን ዘንድ ተለየ፥ እርሱና ልጆቹ፥ ለዘላለም በእግዚአብሔር ፊት ያጥንና ያገለግል ዘንድ፥ በስሙም ለዘላለም ይባርክ ዘንድ።
14 ፤ የእግዚአብሔርም ሰው የሙሴ ልጆች በሌዊ ነገድ ተቈጠሩ።
15 ፤ የሙሴ ልጆች ጌርሳምና አልዓዛር ነበሩ።
16 የጌርሳም ልጆች አለቃ ሱባኤል ነበረ።
17 ፤ የአልዓዛርም ልጆች አለቃ ረዓብያ ነበረ፤ አልዓዛርም ሌሎች ልጆች አልነበሩትም፤ የረዓብያ ልጆች እጅግ ብዙ ነበሩ።
18 ፤ የይስዓር ልጆች አለቃው ሰሎሚት ነበረ።
19 ፤ የኬብሮን ልጆች አለቃው ይሪያ፥ ሁለተኛው አማርያ፥ ሦስተኛው የሕዚኤል፥ አራተኛው ይቅምዓም ነበሩ።
20 ፤ የዑዝኤል ልጆች አለቃው ሚካ፥ ሁለተኛው ይሺያ ነበሩ።
21 ፤ የሜራሪ ልጆች ሞሖሊና ሙሲ ነበሩ። የሞሖሊ ልጆች አልዓዛርና ቂስ ነበሩ።
22 ፤ አልዓዛርም ሴቶች ልጆች ብቻ እንጂ ወንዶች ልጆች ሳይወልድ ሞተ፤ ወንድሞቻቸውም የቂስ ልጆች አገቡአቸው።
23 ፤ የሙሲ ልጆች ሞሖሊ፥ ዔደር፥ ኢያሪሙት ሦስት ነበሩ።
24 ፤ የእግዚአብሔርን ቤት አገልግሎት በሠሩ ከሀያ ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ወደ ላይ በነበሩ በእያንዳንዳቸው በስማቸው በተቆጠሩት ላይ የአባቶች ቤት አለቆች የሆኑት በየአባቶቻቸው ቤት የሌዊ ልጆች እነዚህ ነበሩ።
25 ፤ ዳዊትም። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ዕረፍት ሰጥቶአል፥ በኢየሩሳሌምም ለዘላለም የቀመጣል።
26 ፤ ሌዋውያንም ከእንግዲህ ወዲህ ማደሪያውንና የማገልገያውን ዕቃ ሁሉ አይሸከሙም አለ።
27 ፤ በመጨረሻውም በዳዊት ትእዛዝ ከሀያ ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት የሌዊ ልጆች ተቈጠሩ።
28 ፤ ሥራቸውም የእግዚአብሔርን ቤት በየአደባባዩና በየጓዳው ውስጥ ለማገልገል፥ ቅዱሱንም ዕቃ ሁሉ ለማንጻት፥ የእግዚአብሔርንም ቤት አገልግሎት ለመሥራት ከአሮን ልጆች እጅ በታች ነበረ።
29 ፤ ደግሞም ገጸ ኅብስት፥ ስስ ቂጣም ቢሆን፥ በምጣድም ቢጋገር፥ ቢለወስም፥ ለእህል ቍርባን በሆነው በመልካሙ ዱቄት በመስፈሪያና በልክ ሁሉ ያገለግሉ ነበር።
30 ፤ ሥራቸውም በየጥዋቱና በየማታው ቆመው እግዚአብሔርን ለማመስገንና ለማክበር፥
31 ፤ በየሰንበታቱም በየመባቻዎቹም በየበዓላቱም እንደ ሥርዓቱ ቍጥር በእግዚአብሔር ፊት ዘወትር ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሁሉ ለማቅረብ፥
32 ፤ ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት የመገናኛውን ድንኳን ሥርዓት የመቅደሱንም ሥርዓት የወንድሞቻቸውንም የአሮንን ልጆች ሥርዓት ለመጠበቅ ነበረ።