መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29


ምዕራፍ 29

ንጉሡም ዳዊት ለጉባኤው ሁሉ እንዲህ አለ። እግዚአብሔር ብቻውን የመረጠው ልጄ ሰሎሞን ገና ብላቴና ለጋ ነው፤ ሕንፃው ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክ ነው እንጂ ለሰው አይደለምና ሥራው ታላቅ ነው።
2 ፤ እኔም እንደ ጕልበቴ ሁሉ ለአምላኬ ቤት ለወርቁ ዕቃ ወርቁን፥ ለብሩም ዕቃ ብሩን፥ ለናሱም ዕቃ ናሱን፥ ለብረቱም ዕቃ ብረቱን፥ ለእንጨቱም ዕቃ እንጨቱን፥ ደግሞም መረግድንና በፈርጥ የሚገባ ድንጋይን፥ የሚለጠፍ ድንጋይን፥ ልዩ ልዩ መልክ ያለውንም ድንጋይ፥ የከበረውንም ድንጋይ ከየዓይነቱ፥ ብዙም እብነ በረድ አዘጋጅቻለሁ።
3 ፤ ከዚህም በላይ ደግሞ የአምላኬን ቤት ስለወደድሁ፥ ለመቅደሱ ካዘጋጀሁት ሁሉ ሌላ የግል ገንዘቤ የሚሆን ወርቅና ብር አለኝና ለአምላኬ ቤት ሰጥቼዋለሁ።
4 ፤ የቤቶቹ ግንብ ይለበጡበት ዘንድ ከኦፊር ወርቅ ሦስት ሺህ መክሊት ወርቅ፥ ሰባት ሺህም መክሊት ጥሩ ብር፥
5 ፤ በሠራተኞች እጅ ለሚሠራው ሥራ ሁሉ ለወርቁ ዕቃ ወርቁን፥ ለብሩም ዕቃ ብሩን ሰጥቻለሁ። ዛሬ በፈቃዱ ራሱን ለእግዚአብሔር የሚቀድስ ማነው?
6 ፤ የአባቶችም ቤቶች አለቆች፥ የእስራኤልም ነገዶች አለቆች፥ ሻለቆችም፥ የመቶ አለቆችም፥ በንጉሡም ሥራ ላይ የተሾሙት በፈቃዳቸው አቀረቡ።
7 ፤ ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት አምስት ሺህ መክሊት ወርቅና አሥር ሺህ ዳሪክ፥ አሥር ሺህም መክሊት ብር፥ አሥራ ስምንት ሺህም መክሊት ናስ፥ መቶ ሺህም መክሊት ብረት ሰጡ።
8 ፤ ዕንቍም ያለው ሰው ሁሉ ለእግዚአብሔር ቤት ለሆነው ቤተ መዛግብት በጌድሶናዊው በይሒኤል እጅ ሰጠ።
9 ፤ ሕዝቡም ፈቅደው ሰጥተዋልና፥ በፍጹም ልባቸውም ለእግዚአብሔር በፈቃዳቸው አቅርበዋልና ደስ አላቸው፤ ንጉሡም ዳዊት ደግሞ ታላቅ ደስታ ደስ አለው።
10 ፤ ዳዊትም በጉባኤው ሁሉ ፊት እግዚአብሔርን ባረከ፤ ዳዊትም አለ። አቤቱ፥ የአባታችን የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ተባረክ።
11 ፤ አቤቱ፥ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና ታላቅነትና ኃይል፥ ክብርም፥ ድልና ግርማ ለአንተ ነው፤ አቤቱ፥ መንግሥት የአንተ ነው፥ አንተም በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያልህ ራስ ነህ።
12 ፤ ባለጠግነትና ክብር ከአንተ ዘንድ ነው፥ አንተም ሁሉን ትገዛለህ፤ ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው፤ ታላቅ ለማድረግ፥ ለሁሉም ኃይልን ለመስጠት በእጅህ ነው።
13 ፤ አሁንም እንግዲህ፥ አምላካችን ሆይ፥ እንገዛልሃለን፥ ለክቡር ስምህም ምስጋና እናቀርባለን።
14 ፤ ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና፥ ከእጅህም የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና ይህን ያህል ችለን ልናቀርብልህ እኔ ማን ነኝ? ሕዝቤስ ማን ነው?
15 ፤ አባቶቻችንም ሁሉ እንደነበሩ እኛ በፊትህ ስደተኞችና መጻተኞች ነን፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ናት፥ አትጸናም።
16 ፤ አቤቱ አምላካችን ሆይ፥ ለቅዱስ ስምህ ቤት እንሠራ ዘንድ ይህ ያዘጋጀነው ባለጠግነት ሁሉ ከእጅህ የመጣ ነው፥ ሁሉም የአንተ ነው።
17 ፤ አምላኬ ሆይ፥ ልብን እንድትመረምር፥ ቅንነትንም እንድትወድድ አውቃለሁ፤ እኔም በልቤ ቅንነትና በፈቃዴ ይህን ሁሉ አቅርቤአለሁ፤ አሁንም በዚህ ያለው ሕዝብህ በፈቃዱ እንዳቀረበልህ በደስታ አይቻለሁ።
18 ፤ አቤቱ፥ የአባቶቻችን የአብርሃምና የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ ሆይ፥ ይህን አሳብ በሕዝብህ ልብ ለዘላለም ጠብቅ፥ ልባቸውንም ወደ አንተ አቅና።
19 ፤ ትእዛዝህንም ምስክርህንም ሥርዓትህንም ይጠብቅ ዘንድ፥ ይህንም ነገር ሁሉ ያደርግ ዘንድ፥ ያዘጋጀሁለትንም ቤት ይሠራ ዘንድ ለልጄ ለሰሎሞን ፍጹም ልብ ስጠው።
20 ፤ ዳዊትም ጉባኤውን ሁሉ። አምላካችሁን እግዚአብሔርን ባርኩ አላቸው። ጉባኤውም ሁሉ የአባታቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ባረኩ፥ ራሳቸውንም አዘንብለው ለእግዚአብሔርና ለንጉሡ ሰገዱ።
21 ፤ በነጋውም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሠዉ፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረቡ፤ አንድ ሺህ ወይፈን፥ አንድ ሺህም አውራ በጎች፥ አንድ ሺህም የበግ ጠቦቶች፥ የመጠጥ ቍርባናቸውንም፥ ስለ እስራኤልም ሁሉ ብዙ መሥዋዕት አቀረቡ።
22 ፤ በዚያም ቀን በታላቅ ደስታ በእግዚአብሔር ፊት በሉ ጠጡም። የዳዊትንም ልጅ ሰሎሞንን ሁለተኛ ጊዜ አነገሡት፤ እርሱንም አለቃ ይሆን ዘንድ ለእግዚአብሔር ቀቡት፥ ሳዶቅንም ካህን ይሆን ዘንድ ቀቡት።
23 ፤ ሰሎሞንም በአባቱ በዳዊት ዙፋን ላይ ተቀመጠ፥ ተከናወነለትም፤ እስራኤልም ሁሉ ታዘዙለት።
24 ፤ አለቆቹም ሁሉ፥ ኃያላኑም፥ ደግሞም የንጉሡ የዳዊት ልጆች ሁሉ ለንጉሡ ለሰሎሞን እጅ ሰጡት።
25 ፤ እግዚአብሔርም ሰሎሞንን በእስራኤል ሁሉ ፊት እጅግ አገነነው፤ ከእርሱ በፊትም ለነበሩት ለእስራኤል ነገሥታት ያልሆነውን የመንግሥት ክብር ሰጠው።
26 ፤ የእሴይም ልጅ ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ።
27 ፤ በእስራኤልም ላይ የነገሠበት ዘመን አርባ ዓመት ነበረ፤ ሰባት ዓመት በኬብሮን ነገሠ፥ ሠላሳ ሦስትም ዓመት በኢየሩሳሌም ነገሠ።
28 ፤ ዕድሜም፥ ባለጠግነትም፥ ክብርም ጠግቦ በመልካም ሽምግልና ሞተ፤ ልጁም ሰሎሞን በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
29 ፤ የንጉሡም የዳዊት የፊተኛውና የኋለኛው ነገር፥ እነሆ፥ በባለ ራእዩ በሳሙኤል ታሪክ፥ በነቢዩም በናታን ታሪክ፥ በባለ ራእዩም በጋድ ታሪክ ተጽፎአል።
30 ፤ እንደዚሁም የመንግሥቱ ነገርና ኃይሉ ሁሉ በእርሱም በእስራኤልም በአገሮችም መንግሥታት ሁሉ ላይ ያለፉት ዘመናት ተጽፈዋል።