ምዕራፍ 11

ሮብዓምም ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ እስራኤልን ወግተው መንግሥቱን ወደ ሮብዓም ይመልሱ ዘንድ ከይሁዳና ከብንያም ቤት የተመረጡትን አንድ መቶ ሰማንያ ሺህ ሰልፈኞች ሰዎች ሰበሰበ።
2 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ሸማያ እንዲህ ሲል መጣ።
3 ፤ ለይሁዳ ንጉሥ ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓም፥ በይሁዳና በብንያምም ላሉት ለእስራኤል ሁሉ።
4 ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህ ነገር ከእኔ ዘንድ ነውና አትውጡ፥ ወንድሞቻችሁንም አትውጉ፤ እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ይመለስ ብለህ ንገራቸው። የእግዚአብሔርንም ቃል ሰሙ፥ በኢዮርብዓምም ላይ ከመሄድ ተመለሱ።
5 ፤ ሮብዓምም በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፥ በይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች ሠራ።
6 ፤ በይሁዳና በብንያም ያሉትንም የተመሸጉትን ከተሞች፥ ቤተ ልሔም፥ ኤጣምን፥ ቴቁሔን፥
7
8 ፤ ቤትጹርን፥ ሦኮን፥ ዓዶላምን፥ ጌትን፥ መሪሳን፥
9 ፤ ዚፍን፥ አዶራይምን፥ ለኪሶን፥ ዓዜቃን፥
10 ፤ ጾርዓን፥ ኤሎንን፥ ኬብሮንን፥ ሠራ።
11 ፤ ምሽጎቹንም አጠነከረ፥ አለቆችንም አኖረባቸው፥ ምግቡንም ዘይቱንም የወይን ጠጁንም አከማቸባቸው።
12 ፤ በከተሞቹ ሁሉ ጋሻና ጦርን አኖረ። ከተሞቹንም እጅግ አጠነከራቸው፤ ይሁዳና ብንያምም የእርሱ ወገን ነበሩ።
13 ፤ በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ የነበሩ ካህናትና ሌዋውያን ከየአገራቸው ሁሉ ወደ እርሱ መጡ።
14 ፤ የእግዚአብሔርም ካህናት እንዳይሆኑ ኢዮርብዓምና ልጆቹ አስለቅቀዋቸው ነበርና ሌዋውያን መሰመሪያቸውንና ቦታቸውን ትተው ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።
15 ፤ እርሱ ግን ለኮረብታው መስገጃዎች ለአጋንንቱም ለሠራቸውም እምቦሶች ካህናትን አቆመ።
16 ፤ ደግሞም ለአባቶቻቸው አምላክ ለእግዚአብሔር ይሠዉ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ልባቸውን የሰጡ ሁሉ እነርሱን ተከትለው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።
17 ፤ ሦስት ዓመት በዳዊትና በሰሎሞን መንገድ ይሄዱ ነበርና ሦስት ዓመት የይሁዳን መንግሥት አበረቱ፥ የሰሎሞንንም ልጅ ሮብዓምን አጸኑ።
18 ፤ ሮብዓምም መሐላትን አገባ፤ አባትዋ የዳዊት ልጅ ኢያሪሙት ነበረ፤ እናትዋም የእሴይ ልጅ የኤልያብ ልጅ አቢካኢል ነበረች።
19 ፤ እርስዋም የዑስን፥ ሰማራያን፥ ዘሃምን ወንዶች ልጆች ወለደችለት።
20 ፤ ከእርስዋም በኋላ የአቤሴሎምን ልጅ መዓካን አገባ፤ እርስዋም አብያን፥ ዓታይን፥ ዚዛን፥ ሰሎሚትን ወለደችለት።
21 ፤ ሮብዓምም ከሚስቶቹና ከቁባቶቹ ሁሉ ይልቅ የአቤሴሎምን ልጅ መዓካን ወደደ፤ አሥራ ስምንትም ሚስቶችና ስድሳ ቁባቶች ነበሩት፥ ሀያ ስምንት ወንዶችና ስድሳ ሴቶች ልጆች ወለደ።
22 ፤ ሮብዓምም ንጉሥ ያደርገው ዘንድ አስቦአልና የመዓካን ልጅ አብያን በወንድሞቹ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው።
23 ፤ ተጠበበም፥ ልጆቹንም ሁሉ በይሁዳና በብንያም አገር ሁሉ በምሽጉ ከተሞች ሁሉ ከፋፈላቸው፤ ብዙም ምግብ ሰጣቸው፤ ብዙም ሚስቶች ፈለገላቸው።