ምዕራፍ 17

በእርሱም ፋንታ ልጁ ኢዮሳፍጥ ነገሠ፥ በእስራኤልም ላይ ጠነከረ።
2 ፤ በተመሸጉትም በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ወታደሮችን አኖረ፥ በይሁዳም አገር አባቱም አሳ በወሰዳቸው በኤፍሬም ከተሞች ዘበኞችን አስቀመጠ።
3 ፤ እግዚአብሔርም ከኢዮሳፍጥ ጋር ነበረ፥ በፊተኛይቱ በአባቱ በዳዊት መንገድ ሄዶአልና፥ በኣሊምንም አልፈለገምና፤
4 ፤ ነገር ግን የአባቱን አምላክ ፈለገ፥ በትእዛዙም ሄደ፥ የእስራኤልንም ሥራ አልሠራም።
5 ፤ እግዚአብሔርም መንግሥቱን በእጁ አጸና፤ ይሁዳም ሁሉ እጅ መንሻ ለኢዮሳፍጥ አመጣ፤ እጅግም ብዙ ብልጥግናና ክብር ሆነለት።
6 ፤ ልቡም በእግዚአብሔር መንገድ ከፍ ከፍ አለ፤ የኮረብታውን መስገጃዎችና የማምለኪያ ዐፀዱንም ከይሁዳ አስወገደ።
7 ፤ በነገሠም በሦስተኛው ዓመት በይሁዳ ከተሞች ያስተምሩ ዘንድ መሳፍንቱን፥ ቤንኃይልን፥ አብድያስን፥ ዘካርያስን፥ ናትናኤልን፥ ሚክያስን፥ ሰደደ።
8 ፤ ከእነርሱም ጋር ሌዋውያንን ሸማያን፥ ነታንያን፥ ዝባድያን፥ አሣሄልን፥ ሰሚራሞትን፥ ዮናትንን፥ አዶንያስን፥ ጦብያን፥ ጦባዶንያን ሰደደ ከእነርሱም ጋር ካህናቱን ኤሊሳማንና ኢዮራምን ሰደደ።
9 ፤ እነርሱም የእግዚአብሔርን የሕጉን መጽሐፍ ይዘው በይሁዳ ያስተምሩ ነበር፤ ወደ ይሁዳም ከተሞች ሁሉ ሄደው ሕዝቡን ያስተምሩ ነበር።
10 ፤ በይሁዳም ዙሪያ በነበሩ መንግሥታት ሁሉ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ድንጋጤ ሆነ፥ ከኢዮሳፍጥም ጋር አልተዋጉም።
11 ፤ ከፍልስጥኤማውያን ለኢዮሳፍጥ እጅ መንሻና የብር ግብር ያመጡ ነበር፤ ዓረባውያንም ደግሞ ከመንጎቻቸው ሰባት ሺህ ሰባት መቶ አውራ በጎችና ሰባት ሺህ ሰባት ሺህ ሰባት መቶ አውራ ፍየሎች ያመጡለት ነበር።
12 ፤ ኢዮሳፍጥም እየበረታና እጅግም እየከበረ ሄደ፤ በይሁዳም ግንቦችንና የጎተራ ከተሞችን ሠራ።
13 ፤ በይሁዳም ከተሞች ብዙ ሥራ ሠራ፥ በኢየሩሳሌምም ጽኑዓን ኃያላን ሰልፈኞች ነበሩት።
14 ፤ ቍጥራቸውም እንደ አባቶቻቸው ቤት ይህ ነበረ፤ ከይሁዳ ሻለቆች አለቃው ዓድና፥ ከእርሱም ጋር ሦስት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ፤
15 ፤ ከእርሱም በኋላ አለቃው ይሆሐናን፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሰማንያ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤
16 ፤ ከእርሱም በኋላ በፈቃዱ ራሱን ለእግዚአብሔር የቀደሰ የዝክሪ ልጅ ዓማስያ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ።
17 ፤ ከብንያምም ጽኑዕ ኃያል የነበረው ኤሊዳሄ፥ ከእርሱም ጋር ቀስትና ጋሻ የሚይዙ ሁለት መቶ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤
18 ፤ ከእርሱም በኋላ ዮዛባት፥ ከእርሱም ጋር ለሰልፍ የተዘጋጁ መቶ ሰማኒያ ሺህ ሰዎች ነበሩ።
19 ፤ ንጉሡ በተመሸጉ በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ካኖራቸውም ሌላ እነዚህ ንጉሡን ያገለግሉ ነበር።