ምዕራፍ 4

ደግሞም ርዝመቱ ሀያ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም አሥር ክንድ የነበረውን የናሱን መሠዊያ ሠራ።
2 ፤ ከፈሰሰም ናስ ከዳር እስከ ዳር አሥር ክንድ፥ ቁመቱም አምስት ክንድ፥ በዙሪያውም ሠላሳ ክንድ የሆነ ክብ ኵሬ ሠራ።
3 ፤ በበታቹም ለአንድ ክንድ አሥር፥ ለአንድም ክንድ አሥር፥ ጕብጕቦች አዞረበት፤ ኵሬውም በቀለጠ ጊዜ ጕብጕቦቹ በሁለት ተራ ከእርሱ ጋር አብረው ቀልጠው ነበር።
4 ፤ በአሥራ ሁለትም በሬዎች ምስል ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ከእነርሱም ሦስቱ ወደ ሰሜን ሦስቱም ወደ ምዕራብ ሦስቱም ወደ ደቡብ ሦስቱም ወደ ምሥራቅ ይመለከቱ ነበር፤ ኵሬውም በላያቸው ነበር፥ የሁሉም ጀርባቸው በስተ ውስጥ ነበረ።
5 ፤ ውፍረቱም አንድ ጋት ያህል ነበረ፤ ከንፈሩም አንደ ጽዋ ከንፈር፥ እንደ ሱፍ አበባ ሆኖ ተሠርቶ ነበር፤ ሦስት ሺህም የባዶስ መሥፈሪያ ይይዝ ነበር።
6 ፤ ደግሞም አሥር የመታጠቢያ ሰኖች ሠራ፥ ለሚቃጠለውም መሥዋዕት የሚቀርበው ነገር ሁሉ ይታጠብባቸው ዘንድ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ አኖራቸው፤ ኵሬው ግን ካህናት ይታጠቡበት ነበር።
7 ፤ አሥሩንም መቅረዞች እንደ ሥርዓታቸው ከወርቅ ሠርቶ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ በመቅደሱ ውስጥ አኖራቸው።
8 ፤ አሥሩንም ገበታዎች ሠርቶ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ በመቅደሱ ውስጥ አኖራቸው። አንድ መቶም የወርቅ ድስቶች ሠራ።
9 ፤ ደግሞም የካህናቱን አደባባይ፥ ታላቁንም አደባባይ፥ የአደባባዩንም ደጆች ሠራ፥ ደጆቻቸውንም በናስ ለበጠ።
10 ፤ ኵሬውንም በቤቱ ቀኝ በአዜብ በኩል አኖረው።
11 ፤ ኪራምም ምንቸቶቹንና መጫሪያዎቹን ድስቶቹንም ሠራ። ኪራምም ለንጉሡ ለሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት የሠራውን ሥራ ሁሉ ጨረሰ።
12 ፤ ሁለቱን አዕማድ፥ ጽዋዎቹንም፥ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ሁለት ጕልላቶች፥ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን የጕልላቶች ሁለቱን ጽዋዎች የሚሸፍኑትን ሁለቱን መርበቦች ሠራ።
13 ፤ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጕልላቶች ይሸፍኑ ዘንድ፥ ለእያንዳንዱ መርበብ ሁለት ሁለት ተራ ሮማኖች፥ ለሁለቱ መርበቦች አራት መቶ ሮማኖች አደረገ።
14 ፤ መቀመጫዎቹንና በመቀመጫዎቹ ላይ የሚቀመጡትን የመታጠቢያ ሰኖች፥
15 ፤ አንዱንም ኵሬ፥ በበታቹም የሚሆኑትን አሥራ ሁለት በሬዎች ሠራ።
16 ፤ ምንቸቶቹንም መጫሪያዎቹንም ሜንጦዎቹንም ዕቃቸውንም ሁሉ ኪራም ለንጉሡ ለሰሎሞን ስለ እግዚአብሔር ቤት ከለስላሳ ናስ ሠራ።
17 ፤ ንጉሡም በዮርዳኖስ ሜዳ በሱኮትና በጽሬዳ መካከል ባለው በወፍራሙ መሬት ውስጥ አስፈሰሰው።
18 ፤ ሰሎሞንም እነዚህን ዕቃዎች ሁሉ እጅግ አብዝቶ ሠራ፤ የናሱም ሚዛን አይቈጠርም ነበር።
19 ፤ ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን ዕቃ ሁሉ የወርቁንም መሠዊያ፥ የገጹንም ኅብስት የነበረባቸውን ገበታዎች፥
20 ፤ በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት እንደ ሥርዓታቸው ያበሩ ዘንድ መቅረዞችንና ቀንዲሎቻቸውን ከጥሩ ወርቅ ሠራ።
21 ፤ አበባዎቹንና ቀንዲሎቹን መኮስተሪያዎቹንም ከጥሩ ወርቅ ሠራ።
22 ፤ ጕጦቹንም ድስቶቹንም ጭልፋዎቹንም ማንደጃዎቹንም ከጥሩ ወርቅ ሠራ። የውስጠኛውም ቤት የቅድስተ ቅዱሳን ደጆች የቤተ መቅደሱም ደጆች የወርቅ ነበሩ።