ምዕራፍ 18

ለኢዮሣፍጥም ብዙ ብልጥግናና ክብር ነበረው፤ ለአክዓብም ጋብቻ ሆነ።
2 ፤ ከጥቂት ዓመት በኋላም ወደ አክዓብ ወደ ሰማርያ ወረደ። አክዓብም ለእርሱና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሕዝብ ብዙ በጎችንና በሬዎችን አረደ፥ ከእርሱም ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ይሄድ ዘንድ አባበለው።
3 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። ከእኔ ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ትሄዳለህን? አለው። እርሱም እኔ እንደ አንተ ነኝ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ ናቸው፤ በሰልፍም ከአንተ ጋር እንሆናለን ብሎ መለሰለት።
4 ፤ ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ። የእግዚአብሔርን ቃል አስቀድመህ ትጠይቅ ዘንድ እለምንሃለሁ አለው።
5 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ነቢያቱን አራት መቶ ሰዎች ሰብስቦ። ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር? አላቸው። እነርሱም። እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ አሉት።
6 ፤ ኢዮሣፍጥ ግን። እንጠይቀው ዘንድ የእግዚአብሔርን ነቢይ የሆነ ሌላ ሰው በዚህ አይገኝምን? አለ።
7 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ሁል ጊዜ ክፉ እንጂ ከቶ መልካም ትንቢት አይነግርልኝምና እጠላዋለሁ፤ እርሱም የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው አለው። ኢዮሳፍጥም። ንጉሥ እንዲህ አይበል አለው።
8 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ አንድ ጃንደረባ ጠርቶ። የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ አምጣው አለው።
9 ፤ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ ልብሰ መንግሥት ለብሰው በሰማሪያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያትም ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር።
10 ፤ የክንዓና ልጅ ሰዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሶሪያውያንን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋለህ አለ።
11 ፤ ነቢያትም ሁሉ። እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሂድና ተከናወን እያሉ እንዲሁ ትንቢት ይናገሩ ነበር።
12 ፤ ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልእክተኛ። እነሆ፥ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካም ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ አለው።
13 ፤ ሚክያስም። ሕያው እግዚአብሔርን! አምላኬ የሚለውን እርሱን እናገራለሁ አለ።
14 ፤ ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ። ሚክያስ ሆይ፥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ እንሂድን? ወይስ እንቅር? አለው። እርሱም። ውጣ፥ ተከናወን፤ በእጅህም አልፈው ይሰጣሉ አለ።
15 ፤ ንጉሡም። በእግዚአብሔር ስም ከእውነት በቀር እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ? አለው።
16 ፤ እርሱም። እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም። ለእነዚህ ጌታ የላቸውም፥ እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ አለ ብሎ ተናገረ።
17 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርልኝም አላልሁህምን? አለው።
18 ፤ ሚክያስም አለ። እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ።
19 ፤ እግዚአብሔርም። ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን የሚያታልል ማን ነው? አለ። አንዱም እንደዚህ፥ ሌላውም እንደዚያ ያለ ነገር ተናገረ።
20 ፤ መንፈስም መጣ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ። እኔ አታልለዋለሁ አለ። እግዚአብሔርም። በምን? አለው።
21 ፤ እርሱም። ወጥቼ በነቢያቱ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ አለ። እግዚአብሔርም። ታታልለዋለህ፤ ይቀናሃል፤ ውጣ፥ እንዲህም አድርግ አለ።
22 ፤ አሁንም፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ አፍ ሐሰተኛ መንፈስን አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በአንተ ላይ ክፉ ተናግሮብሃል።
23 ፤ የክንዓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፥ ሚክያስንም በጥፊ መታውና። የእግዚአብሔር መንፈስ ከአንተ ጋር ይናገር ዘንድ በምን መንገድ ከእኔ አለፈ? አለ።
24 ፤ ሚክያስም። እነሆ፥ በዚያ ቀን ልትሸሸግ ወደ እልፍኝህ ስትሄድ ታያለህ አለ።
25 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ። ሚክያስን ውሰዱ፥ ወደ ከተማይቱም አለቃ ወደ አሞን፥ ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ።
26 ፤ ንጉሡ እንዲህ ይላል። በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በግዞት አኑሩት፥ የመከራም እንጀራ መግቡት፥ የመከራም ውኃ አጠጡት በሉ አለ።
27 ፤ ሚክያስም። በደህና ብትመለስ እግዚአብሔር በእኔ የተናገረ አይደለም አለ። ደግሞም። እናንተ ሕዝብ ሁሉ፥ ስሙኝ አለ።
28 ፤ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ወጡ።
29 ፤ የእስራኤል ንጉሥም ኢዮሣፍጥን። ልብሴን ለውጬ ወደ ሰልፍ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብስህን ልበስ አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለወጠ፥ ወደ ሰልፍም ገቡ።
30 ፤ የሶርያም ንጉሥ የሰረገሎቹን አለቆች። ከእስራኤል ንጉሥ በቀር ትንሽ ቢሆን ወይም ትልቅ ከማናቸውም ጋር አትጋጠሙ ብሎ አዝዞ ነበር።
31 ፤ የሰረገሎችም አለቆች ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ። የእስራኤል ንጉሥ ነው አሉ፥ ሊጋጠሙትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፥ እግዚአብሔርም ረዳው፥ አምላኩም ከእርሱ መለሳቸው።
32 ፤ የሰረገሎቹም አለቆች የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ።
33 ፤ አንድ ሰውም ቀስቱን በድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በጥሩሩ መጋጠሚያ በኩል ሳምባውን ወጋው። ሰረጋለኛውንም። ተወግቻለሁና እጅህን ግታ ከሰልፍም ውስጥ አውጣኝ አለው።
34 ፤ በዚያም ቀን ሰልፍ በረታ፤ የእስራኤልም ንጉሥ በሶሪያውያን ፊት እስከ ማታ ድረስ በሰረገላው ላይ ራሱን ይደግፍ ነበር፤ ፀሐይም በገባ ጊዜ ሞተ።