ምዕራፍ 3

ሰሎሞንም እግዚአብሔር ለአባቱ ለዳዊት በተገለጠበት በሞሪያ ተራራ ዳዊት ባዘጋጀው ስፍራ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ በኢየሩሳሌም የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመረ።
2 ፤ በነገሠም በአራተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር መሥራት ጀመረ።
3 ፤ ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት ይሠራ ዘንድ የጣለው መሠረት ይህ ነው፤ ርዝመቱም በዱሮው ስፍር ስድሳ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ ነበረ።
4 ፤ በቤቱም ፊት የነበረው ወለል ርዝመቱ እንደ ቤቱ ወርድ ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም መቶ ሀያ ክንድ ነበረ፤ ውስጡንም በጥሩ ወርቅ ለበጠው።
5 ፤ ታላቁንም ቤት በጥድ እንጨት ከደነው፥ በጥሩም ወርቅ ለበጠው፤ የዘንባባና የሰንሰለት አምሳል ቀረጸበት።
6 ፤ ቤቱንም በዕንቍ አስጌጠው፤ ወርቁንም የፈርዋይም ወርቅ ነበረ።
7 ፤ ቤቱንም ሰረገሎቹንም መድረኮቹንም ግንቦቹንም ደጆቹንም በወርቅ ለበጠ፤ በግንቦቹም ላይ ኪሩቤልን ቀረጸ።
8 ፤ ቅድስተ ቅዱሳኑንም ሠራ፤ ርዝመቱም እንደ ቤቱ ወርድ ሀያ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ ነበረ፤ ስድስት መቶ መክሊት በሚያህል በጥሩ ወርቅ ለበጠው።
9 ፤ የምስማሮቹም ሚዛን አምሳ ሰቅል ወርቅ ነበረ። የደርቡንም ጓዳዎች በወርቅ ለበጠ።
10 ፤ በቅድስተ ቅዱሳንም ውስጥ ከእንጨት ሥራ ሁለቱ ኪሩቤልን ሠራ፥ በወርቅም ለበጣቸው።
11 ፤ የኪሩቤልም ክንፎች ሀያ ክንድ ሙሉ ተዘርግተው ነበር፤ የአንዱ ኪሩብ ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የቤቱንም ግንብ ይነካ ነበረ፤ ሁለተኛው ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የሁለተኛውንም ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበር።
12 ፤ የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የቤቱንም ግንብ ይነካ ነበር፤ ሁለተኛውም ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የሌላውንም ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበር።
13 ፤ የእነዚህም ኪሩቤል ክንፎች ሀያ ክንድ ሙሉ ተዘርግተው ነበር፤ በእግራቸውም ቆመው ነበር፥ ፊቶቻቸውም ወደ ቤቱ ይመለከቱ ነበር።
14 ፤ ከሰማያዊውም ከሐምራዊውም ከቀዩም ሐር ከጥሩም በፍታ መጋረጃውን ሠራ፥ ኪሩቤልንም ጠለፈበት።
15 ፤ በቤቱም ፊት ቁመታቸው ሠላሳ አምስት ክንድ የነበረውን ሁለቱን ዓምዶች ሠራ፥ በእያንዳንዳቸውም ላይ የነበረው ጕልላት አምስት ክንድ ነበረ።
16 ፤ እንደ ድሪ ያሉ ሰንሰለቶችንም ሠርቶ በአዕማዱ ራስ ላይ አደረጋቸው፤ መቶም ሮማኖች ሠርቶ በሰንሰለቱ ላይ አደረጋቸው።
17 ፤ አዕማዶቹንም አንደኛውን በቀኝ፥ ሁለተኛውን በግራ በመቅደሱ ፊት አቆማቸው፤ በቀኝም የነበረውን ስም ያቁም በግራም የነበረውን ስም በለዝ ብሎ ጠራቸው።