ምዕራፍ 32

ከዚህም ነገርና ከዚህ እምነት በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ወደ ይሁዳ ገባ፥ በተመሸጉትም ከተሞች ፊት ሰፈረ፥ ሊወስዳቸውም አሰበ።
2 ፤ ሕዝቅያስም ሰናክሬም እንደ መጣ፥ ኢየሩሳሌምንም ሊወጋ ፊቱን አንዳቀና ባየ ጊዜ፥
3 ፤ ከከተማይቱ በስተ ውጭ ያለውን የውኃውን ምንጭ ይደፍኑ ዘንድ ከአለቆቹና ከኃያላኑ ጋር ተማከረ፤ እነርሱም ረዱት።
4 ፤ እጅግም ሰዎች ተሰብስበው። የአሦር ነገሥታት መጥተው ብዙ ውኃ ስለ ምን ያገኛሉ? ብለው ምንጩን ሁሉ፥ በምድርም መካከል ይንዶለዶል የነበረውን ወንዝ ደፈኑ።
5 ፤ ሰውነቱንም አጸናና፥ የፈረሰውንም ቅጥር ሁሉ ጠገነ፥ በላዩም ግንብ ሠራበት፥ ከእርሱም በስተ ውጭ ሌላ ቅጥር ሠራ፤ በዳዊትም ከተማ ያለችውን ሚሎን አጠነከረ፤ ብዙም መሣሪያና ጋሻ ሠራ።
6 ፤ የጦር አለቆቹንም በሕዝቡ ላይ ሾሞ፥ ሁሉንም በከተማይቱ በር ወዳለው አደባባይ ሰብስቦ።
7 ፤ ጽኑ፥ አይዞአችሁ፤ ከእኛም ጋር ያለው ከእርሱ ጋር ካለው ይበልጣልና ከአሦር ንጉሥና ከእርሱ ጋር ካለው ጭፍራ ሁሉ አትፍሩ፥ አትደንግጡም።
8 ፤ ከእርሱ ጋር የሥጋ ክንድ ነው፤ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳንና የሚዋጋልን አምላካችን እግዚአብሔር ነው ብሎ አጸናናቸው። ሕዝቡም በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ቃል ተጽናና።
9 ፤ ከዚህም በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር በለኪሶ ፊት ሳለ ባሪያዎቹን ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሕዝቅያስና በኢየሩሳሌም ወደ ነበሩ ወደ ይሁዳ ሁሉ እንዲህ ሲል ላከ።
10 ፤ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም እንዲህ ይላል። እናንተ በማን ተማምናችሁ በኢየሩሳሌም ምሽግ ትቀመጣላችሁ?
11 ፤ አምላካችን እግዚአብሔር ከአሦር ንጉሥ እጅ ያድነናል እያለ በራብና በጥም እንድትሞቱ አሳልፎ ይሰጣችሁ ዘንድ የሚያባብላችሁ ሕዝቅያስ አይደለምን?
12 ፤ በአንድ መሠዊያ ፊት ስገዱ፥ በእርሱም ላይ ዕጠኑ እያለ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አዝዞ፥ የኮረብታው መስገጃዎቹና መሠዊያዎቹን ያፈረሰ ይህ ሕዝቅያስ አይደለምን?
13 ፤ እኔና አባቶቼ በምድር አሕዛብ ሁሉ ያደረግነውን አላወቃችሁምን? የምድርስ ሁሉ አሕዛብ አማልክት አገራቸውን ከእጄ ያድኑ ዘንድ በውኑ ተቻላቸውን?
14 ፤ አምላካችሁስ ከእጄ እናንተን ለማዳን ይችል ዘንድ አባቶቼ ካጠፉአቸው ከአሕዛብ አማልክት ሁሉ ሕዝቡን ከእጄ ያድን ዘንድ የቻለ ማን ነው?
15 ፤ አሁንም ሕዝቅያስ አያስታችሁ፥ እንዲህም አያባብላችሁ፥ አትመኑትም፤ ከአሕዛብና ከመንግሥታት አማልክት ሁሉ ሕዝቡን ከእጄና ከአባቶቼ እጅ ያድን ዘንድ ዘንድ ማንም አልቻለም፤ ይልቁንስ አምላካችሁ ከእጄ ያድናችሁ ዘንድ እንዴት ይችላል?
16 ፤ ባሪያዎቹም ደግሞ በአምላክ በእግዚአብሔርና በባሪያው በሕዝቅያስ ላይ ሌላ ብዙ ነገር ተናገሩ።
17 ፤ ደግሞም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ለመስደብ፥ በእርሱም ላይ ለመናገር። የምድር አሕዛብ አማልክት ሕዝባቸውን ከእጄ ያድኑ ዘንድ እንዳልቻሉ፥ እንዲሁ የሕዝቅያስ አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ያድን ዘንድ አይችልም የሚል ደብዳቤ ጻፈ።
18 ፤ ከተማይቱንም እንዲወስዱ፥ በቅጥር ላይ የተቀመጡትን የኢየሩሳሌም ሕዝብ ያስፈሩና ያስደነግጡ ዘንድ፥ በታላቅ ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ይጮኹባቸው ነበር።
19 ፤ በሰውም እጅ በተሠሩ በምድር አሕዛብ አማልክት ላይ አንደሚናገሩ መጠን በኢየሩሳሌም አምላክ ላይ ተናገሩ።
20 ፤ ንጉሡም ሕዝቅያስና የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለዚህ ጸለዩ፥ ወደ ሰማይም ጮኹ።
21 ፤ እግዚአብሔርም ጽኑዓን ኃያላኑንና መሳፍንቱን አለቆቹንም ከአሦር ንጉሥ ሰፈር እንዲያጠፋ መልአኩን ሰደደ። የአሦርም ንጉሥ አፍሮ ወደ አገሩ ተመለሰ። ወደ አምላኩም ቤት በገባ ጊዜ ከወገቡ የወጡት ልጆቹ በዚያ በሰይፍ ገደሉት።
22 ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ሕዝቅያስንና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ከአሦር ንጉሥ ከሰናክሬም እጅ ከሁሉም እጅ አዳናቸው፤ በዙሪያቸውም ካለው ሁሉ አሳረፋቸው።
23 ፤ ብዙዎቹም ለእግዚአብሔር መባ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ይመጡ ነበር፥ ለይሁዳም ንጉሥ ለሕዝቅያስ እጅ መንሻ ይሰጡ ነበር፤ እርሱም ከዚህ ነገር በኋላ በአሕዛብ ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አለ።
24 ፤ በዚያም ወራት ሕዝቅያስ እስኪሞት ድረስ ታመመ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፤ እርሱም ተናገረው፥ ምልክትም ሰጠው።
25 ፤ ሕዝቅያስ ግን እንደ ተቀበለው ቸርነት መጠን አላደረገም፥ ልቡም ኰራ፤ ስለዚህም በእርሱና በይሁዳ በኢየሩሳሌምም ላይ ቍጣ ሆነ።
26 ፤ ሕዝቅያስም ከኢየሩሳሌም ሰዎች ጋር ስለ ልቡ ኵራት ሰውነቱን አዋረደ፥ የእግዚአብሔርም ቍጣ በሕዝቅያስ ዘመን አልመጣባቸውም።
27 ፤ ለሕዝቅያስም እጅግ ብዙ ሀብትና ክብር ነበረው፤ ለብርና ለወርቅም፥ ለከበረው ዕንቍና ለሽቱው፥ ለጋሻውና ለከበረው ዕቃ ሁሉ ግምጃ ቤቶች ሠራ።
28 ፤ ለእህልና ለወይን ጠጅም ለዘይትም ዕቃ ቤቶች፥ ለልዩ ልዩም እንስሳ ጋጥ፥ ለመንጎችም በረት ሠራ።
29 ፤ እግዚአብሔርም እጅግ ብዙ ጥሪት ሰጥቶት ነበርና ከተሞችን ሠራ፥ ብዙም የበግና የላም መንጋ ሰበሰበ።
30 ፤ ይህም ሕዝቅያስ የላይኛውን የግዮንን ውኃ ምንጭ ደፈነ፥ በዳዊትም ከተማ በምዕራብ በኩል አቅንቶ አወረደው። የሕዝቅያስም ሥራ ሁሉ ተከናወነ።
31 ፤ ነገር ግን የባቢሎን መሳፍንት መልእክተኞች በአገሩ ላይ ስለ ተደረገው ተአምራት ይጠይቁት ዘንድ ወደ እርሱ በተላኩ ጊዜ እግዚአብሔር ይፈትነውና በልቡ ያለውን ሁሉ ያውቅ ዘንድ ተወው።
32 ፤ የሕዝቅያስም የቀረው ነገር፥ ቸርነቱም፥ እነሆ፥ በአሞጽ ልጅ በነቢዩ በኢሳይያስ ራእይ በይሁዳና በእስራኤልም ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል።
33 ፤ ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ልጆች መቃብር በላይኛው ክፍል ቀበሩት፤ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ ሁሉ በሞቱ አከበሩት። ልጁም ምናሴ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።