ምዕራፍ 13

ንጉሡም ኢዮርብዓም በነገሠ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያ በይሁዳ ላይ ንጉሥ ሆነ።
2 ፤ ሦስት ዓመት በኢየሩሳሌም ነገሠ፤ የእናቱም ስም ሚካያ ነበረ፥ የገብዓ ሰው የኡርኤል ልጅ ነበረች።
3 ፤ በአብያና በኢዮርብዓም መካከልም ሰልፍ ነበረ። አብያም የተመረጡትን አራት መቶ ሺህ ኃያላን ሰልፈኞች ይዞ ወደ ሰልፍ ወጣ፤ ኢዮርብዓምም የተመረጡትን ስምንት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ይዞ በእርሱ ላይ ተሰለፈ።
4 ፤ አብያም በተራራማው በኤፍሬም አገር ባለው በጽማራይም ተራራ ላይ ቆሞ እንዲህ አለ። ኢዮርብዓምና እስራኤል ሁሉ ሆይ፥ ስሙኝ፤
5 ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ መንግሥትን ለዳዊትና ለልጆቹ በጨው ቃል ኪዳን ለዘላለም እንደ ሰጠ በውኑ አታውቁምን?
6 ፤ የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ባሪያ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ግን ተነሥቶ በጌታው ላይ ዐመፀ።
7 ፤ ክፉዎች ሰዎችና ምናምንቴዎችም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ ሮብዓም ሕፃንና ለጋ በነበረበት ጊዜ፥ ሊቋቋማቸውም ባልቻለበት ጊዜ፥ በሰሎሞን ልጅ በሮብዓም ላይ በረቱበት።
8 ፤ አሁንም በዳዊት ልጆች እጅ የሚሆነውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ልትቋቋሙ ታስባላችሁ። እናንተም እጅግ ታላቅ ሕዝብ ናችሁ፥ ኢዮርብዓምም አማልክት አድርጎ የሠራላችሁ የወርቅ እምቦሶች ከእናንተ ጋር ናቸው።
9 ፤ የአሮንን ልጆች የእግዚአብሔርን ካህናትና ሌዋውያን አላሳደዳችሁምን? እንደ ሌሎችም አሕዛብ ልማድ ካህናትን አላደረጋችሁምን? አንድ ወይፈንና ሰባት አውራ በጎች ይዞ ይቀድስ ዘንድ የሚመጣ ሁሉ አማልክት ላልሆኑት ለእነዚያ ካህን ይሆናል።
10 ፤ ለእኛ ግን አምላካችን እግዚአብሔር ነው፥ አልተውነውም፤ የእግዚአብሔርም አገልጋዮች የአሮን ልጆች ካህናቱ ሌዋውያኑም በሥራቸው ከእኛ ጋር ናቸው።
11 ፤ በየጥዋቱና በየማታውም ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ጣፋጩን ዕጣን ያሳርጋሉ፤ የገጹንም ኅብስት በንጹህ ገበታ ላይ፥ የወርቁን መቅረዝና ቀንዲሎቹንም ማታ ማታ እንዲያበሩ ያዘጋጃሉ፤ እኛም የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንጠብቃለን፥ እናንተ ግን ትታችሁታል።
12 ፤ እነሆም፥ እግዚአብሔር በእኛ ላይ አለቃ ነው፥ መለከቱንም የሚነፉ ካህናቱ ከእኛ ጋር ናቸው፥ በእናንተም ላይ ይጮኻሉ። የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ አይበጃችሁምና ከአባቶቻችሁ አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር አትዋጉ።
13 ፤ ኢዮርብዓም ግን ድብቅ ጦር በስተ ኋላቸው አዞረ፤ እነርሱ በይሁዳ ፊት ሆነው ድብቅ ጦሩ በስተ ኋላቸው ነበረ።
14 ፤ ይሁዳም ወደ ኋላው በተመለከተ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰልፉ በፊቱና በኋላው ነበረ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ፥ ካህናቱም መለከቱን ነፉ።
15 ፤ የይሁዳም ሰዎች ጮኹ፤ የይሁዳም ሰዎች በጮኹ ጊዜ እግዚአብሔር ኢዮርብዓምንና እስራኤልን ሁሉ በአብያና በይሁዳ ፊት መታቸው።
16 ፤ የእስራኤልም ልጆች ከይሁዳ ፊት ሸሹ፥ እግዚአብሔርም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው።
17 ፤ አብያና ሕዝቡ ታላቅ አመታት መቱአቸው፤ ከእስራኤልም አምስት መቶ ሺህ የተመረጡ ሰዎች ተገድለው ወደቁ።
18 ፤ በዚያም ጊዜ የእስራኤል ልጆች ተዋረዱ፥ የይሁዳም ልጆች በአባቶቻቸው አምላክ በእግዚአብሔር ታምነው ነበርና አሸነፉ።
19 ፤ አብያም ኢዮርብዓምን አሳደደው፥ ከእርሱም ከተሞቹን፥ ቤቴልንና መንደሮችዋን፥ ይሻናንና መንደሮችዋን፥ ዔፍሮንንና መንደሮችዋን ወሰደ።
20 ፤ ኢዮርብዓምም ከዚያ በኋላ በአብያ ዘመን አልበረታም፤ እግዚአብሔርም ቀሠፈው፥ ሞተም።
21 ፤ አብያም ጸና፥ አሥራ አራትም ሚስቶች አገባ፥ ሀያ ሁለትም ወንዶች ልጆችንና አሥራ ስድስት ሴቶች ልጆችን ወለደ።
22 ፤ የአብያም የቀረው ነገርና አካሄዱ የተናገራቸውም ቃሎች በነቢዩ በአዶ መጽሐፍ ተጽፈዋል።