ምዕራፍ 29

ሕዝቅያስም የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ በነበረ ጊዜ መንገሥ ጀመረ፥ በኢየሩሳሌም ሀያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዘካርያስ ልጅ አቡ ትባል ነበር።
2 ፤ አባቱም ዳዊት እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።
3 ፤ በነገሠም በመጀመሪያው ዓመት በመጀመሪያው ወር የእግዚአብሔርን ቤት ደጆች ከፈተ፥ አደሳቸውም።
4 ፤ ካህናቱንና ሌዋውያኑንም አስመጣ፥ በምሥራቅ በኩል ባለው አደባባይም ሰበሰባቸው፥
5 ፤ እንዲህም አላቸው። ሌዋውያን ሆይ፥ ስሙኝ፤ ተቀደሱ፥ የአባቶቻችሁንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት ቀድሱ፤ ርኩሱን ነገር ሁሉ ከመቅደሱ አስወግዱ።
6 ፤ አባቶቻችን ተላልፈዋል፥ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድርገዋል፤ እርሱንም ትተዋል፥ ፊታቸውንም ከእግዚአብሔር መኖሪያ መልሰዋል፥
7 ፤ ወደ እርስዋም ጀርባቸውን አዙረዋል፤ ደግሞም የወለሉን ደጆች ቈልፈዋል፥ መብራቶቹንም አጥፍተዋል፥ በመቅደሱም ውስጥ ለእስራኤል አምላክ አላጠኑም፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አላቀረቡም።
8 ፤ ስለዚህም የእግዚአብሔር ቍጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ሆነ፥ በዓይናችሁም እንደምታዩ ለድንጋጤና ለመደነቂያ ለመዘበቻም አሳልፎ ሰጣቸው።
9 ፤ እነሆም፥ ስለዚህ አባቶቻችን በሰይፍ ወደቁ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም ሚስቶቻችንም ተማረኩ።
10 ፤ አሁንም የቍጣው ጽናት ከእኛ እንዲመለስ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን አደርግ ዘንድ በልቤ አስቤአለሁ።
11 ፤ ልጆቼ ሆይ፥ በፊቱ ትቆሙና ታገለግሉት ዘንድ፥ አገልጋዮቹም ትሆኑ ዘንድ፥ ታጥኑለትም ዘንድ እግዚአብሔር መርጦአችኋልና ቸል አትበሉ።
12 ፤ ሌዋውያኑም፥ ከቀዓት ልጆች የአማሢ ልጅ መሐትና የዓዛርያስ ልጅ ኢዮኤል፥ ከሜራሪም ልጆች የአብዲ ልጅ ቂስና የይሃሌልኤል ልጅ ዓዛርያስ፥ ከጌድሶንም ልጆች የዛማት ልጅ ዩአክና የዩአክ ልጅ ዔድን፥
13
14 ፤ ከኤሊጸፋንም ልጆች ሺምሪና ይዒኤል፥ ከአሳፍም ልጆች ዘካርያስና መታንያ፥ ከኤማንም ልጆች ይሒኤልና ሰሜኢ፥ ከኤዶታምም ልጆች ሸማያና ዑዝኤል ተነሡ።
15 ፤ ወንድሞቻቸውንም ሰብስበው ተቀደሱ፤ በእግዚአብሔር ቃል እንደመጣው እንደ ንጉሡ ትእዛዝ የእግዚአብሔርን ቤት ያነጹ ዘንድ ገቡ።
16 ፤ ካህናቱም ያነጹት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ውስጡ ገቡ፥ በእግዚአብሔርም መቅደስ ያገኙትን ርኩስ ነገር ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ቤት አደባባይ አወጡት። ሌዋውያንም ወስደው ወደ ሜዳ ወደ ቄድሮን ወንዝ ጣሉት።
17 ፤ በመጀመሪያውም ወር በመጀመሪያው ቀን ይቀደሱ ጀመር፥ በዚያውም ወር በስምንተኛው ቀን ወደ እግዚአብሔር ቤት ወለል ደረሱ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት በስምንት ቀን ቀደሱ፥ በመጀመሪያውም ወር በአሥራ ስድስተኛው ቀን ፈጸሙ።
18 ፤ ወደ ውስጡም ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ገብተው። የእግዚአብሔርን ቤት ሁሉ፥ ለሚቃጠል መስዋዕት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ፥ የገጹንም ኅብስት ገበታና ዕቃውን ሁሉ አንጽተናል፤
19 ፤ ንጉሡም አካዝ ነግሦ ሳለ በመተላለፍ ያረከሰውን ዕቃ ሁሉ አዘጋጅተናል ቀድሰናልም፤ እነሆም፥ በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ሆነዋል አሉት።
20 ፤ ንጉሡም ሕዝቅያስ ማልዶ ተነሣ የከተማይቱንም አለቆች ሰበሰበ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ወጣ።
21 ፤ ስለ መንግሥቱና ስለ መቅደሱም ስለ ይሁዳም ሰባት ወይፈኖች፥ ሰባትም አውራ በጎች፥ ሰባትም የበግ ጠቦቶች፥ ሰባትም አውራ ፍየሎች ለኃጢያት መሥዋዕት አመጡ። የአሮንንም ልጆች ካህናቱን። በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ አሳረጉአቸው አላቸው።
22 ፤ ወይፈኖቹንም አረዱ፥ ካህናቱም ደሙን ተቀብለው በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ አውራ በጎቹንም አረዱ፥ ደሙንም በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ ጠቦቶቹንም አረዱ ደሙንም በመሠዊያው ላይ ረጩት።
23 ፤ የኃጢያትም መሥዋዕት የሚሆኑትን አውራ ፍየሎች በንጉሡና በጉባኤው ፊት አቀረቡ፥ እጃቸውንም ጫኑባቸው፥ ካህናቱም አረዱአቸው፤
24 ፤ ንጉሡም የሚቃጠል መሥዋዕትና የኃጢያት መሥዋዕት ለእስራኤል ሁሉ እንዲደረግ አዝዞ ነበርና ለእስራኤል ሁሉ ማስተስረያ ያደርጉ ዘንድ የኃጢያቱን መሥዋዕት ደም በመሠዊያው ላይ አቀረቡ።
25 ፤ ይህንም ትእዛዝ እግዚአብሔር በነቢያቱ እጅ አዝዞአልና እንደ ዳዊትና እንደ ንጉሡ ባለ ራእይ እንደ ጋድ፥ እንደ ነቢዩም እንደ ናታን ትእዛዝ፥ ጸናጽልና በገና መሰንቆም አስይዞ ሌዋውያንን በእግዚአብሔር ቤት አቆመ።
26 ፤ ሌዋውያንም የዳዊትን የዜማ ዕቃ ይዘው፥ ካህናቱም መለከቱን ይዘው ቆመው ነበር።
27 ፤ ሕዝቅያስም የሚቃጠለውን መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ ያሳርጉ ዘንድ አዘዘ፤ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ማረግ በተጀመረ ጊዜ የእግዚአብሔር መዝሙር ደግሞ ተጀመረ፥ መለከቱም ተነፋ፥ የእስራኤልም ንጉሥ የዳዊት ዜማ ዕቃ ተመታ።
28 ፤ ጉባኤውም ሁሉ ሰገዱ፥ መዘምራኑም ዘመሩ፥ መለከተኞችም ነፉ፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት እስኪፈጸም ድረስ ይህ ሁሉ ሆነ።
29 ፤ ማቅረቡንም በፈጸሙ ጊዜ ንጉሡና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሁሉ አጐነበሱ ሰገዱም።
30 ፤ ንጉሡም ሕዝቅያስና አለቆቹ ሌዋውያንን በዳዊትና በባለ ራእዩ በአሳፍ ቃል እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ አዘዙ። በደስታም አመሰገኑ፥ አጐነበሱም ሰገዱም።
31 ፤ ሕዝቅያስም። አሁን ለእግዚአብሔር ተቀድሳችኋል፤ ቅረቡ፥ መሥዋዕቱንና የምስጋናውን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር ቤት አምጡ ብሎ ተናገረ። ጉባኤውም መሥዋዕቱንና የምስጋናውን መስዋዕት አመጡ፤ ልባቸውም የፈቀደ ሁሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አመጡ።
32 ፤ ጉባኤውም ያመጡት የሚቃጠል መሥዋዕት ቍጥር ሰባ ወይፈን፥ መቶም አውራ በጎች፥ ሁለት መቶም የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ ይህ ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ።
33 ፤ የተቀደሱትም ቍጥር ስድስት መቶ በሬዎች ሦስት ሺህም በጎች ነበረ።
34 ፤ ነገር ግን ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለመግፈፍ ጥቂቶች ነበሩ፤ ስለዚህም ሌዋውያን በቅን ልብ ከካህናት ይልቅ ይቀደሱ ነበርና ሥራው እስኪፈጸም ድረስ፥ ካህናቱም እስኪቀደሱ ድረስ ወንድሞቻቸው ሌዋውያን ያግዙአቸው ነበር።
35 ፤ የሚቃጠለውም መሥዋዕት የደኅንነቱም መሥዋዕት ስብ፥ ከሚቃጠለውም መሥዋዕት ሁሉ ጋር የሚቀርበው የመጠጥ ቍርባን፥ ብዙ ነበረ። እንዲሁም የእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ተዘጋጀ።
36 ፤ ሕዝቅያስና ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ስላዘጋጀው ነገር ደስ አላቸው። ይህም ነገር በድንገት ተደረገ።