ምዕራፍ 19

የይሁዳም ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ቤቱ ወደ ኢየሩሳሌም በደኅና ተመለሰ።
2 ፤ ባለ ራእዩ የአናኒ ልጅ ኢዩ ሊገናኘው ወጣ፥ ንጉሡንም ኢዮሣፍጥን። ከሐዲውን ታግዛለህን? ወይስ እግዚአብሔርን የሚጠሉትን ትወድዳለህን? ስለዚህም ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ ቍጣ ሆኖብሃል።
3 ፤ ነገር ግን የማምለኪያ ዐፀዶቹን ከምድር አስወግደሃልና፥ እግዚአብሔርንም ትፈልግ ዘንድ ልብህን አዘጋጅተሃልና መልካም ነገር ተገኝቶብሃል አለው።
4 ፤ ኢዮሣፍጥም በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፤ ደግሞም ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ተራራማው እስከ ኤፍሬም አገር ድረስ ወደ ሕዝቡ ወጥቶ ወደ አባቶቻቸው አምላክ ወደ እግዚአብሔር መለሳቸው።
5 ፤ በምድር ላይ በተመሸጉት በይሁዳ ከተሞች ሁሉ በእያንዳንዱ ከተማ ውስጥ ፈራጆች አኖረ።
6 ፤ ፈራጆቹንም። ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አትፈርዱምና፥ እርሱም በፍርድ ነገር ከእናንተ ጋር ነውና የምታደርጉትን ተመልከቱ።
7 ፤ አሁንም እግዚአብሔርን መፍራት በእናንተ ላይ ይሁን፤ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ዘንድ በደልና ለሰው ፊት ማድላት መማለጃም መውሰድ የለምና ሁሉን ተጠንቅቃችሁ አድርጉ አላቸው።
8 ፤ ኢዮሣፍጥም ከሌዋውያንና ከካህናት ከእስራኤልም የአባቶች ቤቶች አለቆች፥ በእግዚአብሔር ስም ፍርድን እንዲፈርዱ ክርክርንም እንዲቈርጡ በኢየሩሳሌም ሾመ። እነርሱም በኢየሩሳሌም ተቀመጡ።
9 ፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። እንዲሁ እግዚአብሔርን በመፍራት በቅንነትም በፍጹምም ልብ አድርጉ።
10 ፤ በከተሞቻቸውም ከተቀመጡት ከወንድሞቻችሁ በደምና በደም መካከል በሕግና በትእዛዝ በሥርዓትና በፍርድም መካከል ያለ ማናቸውም ነገር ወደ እናንተ ቢመጣ እግዚአብሔርን እንዳይበድሉ፥ ቍጣም በእናንተና በወንድሞቻችሁ ላይ እንዳይመጣ አስጠንቅቁአቸው፤ እንዲህም ብታደርጉ በደለኞች አትሆኑም።
11 ፤ እነሆም፥ ለእግዚአብሔር በሚሆነው ነገር ሁሉ የካህናቱ አለቃ አማርያ፥ በንጉሡም ነገር ሁሉ የይሁዳ ቤት አለቃ የይስማኤል ልጅ ዝባድያ በላያችሁ ተሾመዋል፤ ሌዋውያኑም ደግሞ በፊታችሁ አለቆች ይሆናሉ፤ በርትታችሁም አድርጉ፥ እግዚአብሔርም መልካም ከሚያደርግ ጋር ይሁን።