ምዕራፍ 12

የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ በዓመፀኛ ቤት መካከል ተቀምጠሃል፤ ያዩ ዘንድ ዓይን አላቸው እነርሱም አያዩም፥ ይሰሙም ዘንድ ጆሮ አላቸው እነርሱም አይሰሙም፤ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና።
3 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የስደተኛ እክት አዘጋጅ በፊታቸውም ቀን ለቀን ተማረክ፥ በፊታቸውም ከስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ተማርከህ ሂድ፤ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት እንደ ሆኑ ምናልባት ያስተውሉ ይሆናል።
4 ፤ ቀን ለቀንም በፊታቸው እክትህን እንደ ስደተኛ እክት አውጣው፥ በማታም ጊዜ በፊታቸው ስደተኞች እንደሚወጡ እንዲሁ ውጣ።
5 ፤ በፊታቸውም ግንቡን ንደል በእርሱም አውጣ።
6 ፤ ለእስራኤልም ቤት ምልክት አድርጌሃለሁና በፊታቸው በጫንቃህ ላይ አንግተው፥ በጨለማም ተሸክመህ ውጣ፤ ምድሪቱንም እንዳታይ ፊትህን ሸፍን።
7 ፤ እንዳዘዘኝም አደረግሁ፤ ቀን ለቀንም እክቱን እንደ ስደተኛ እክት አወጣሁ፥ በማታም ጊዜ ግንቡን በእጄ ነደልሁ፥ በጨለማም አወጣሁት በፊታቸውም በጫንቃዬ ላይ አንግቼ ተሸከምሁት።
8 ፤ በነጋውም የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
9 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ዓመፀኛ ቤት የእስራኤል ቤት። የምታደርገው ምንድር ነው? አላሉህምን?
10 ፤ አንተም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህ ሸክም በኢየሩሳሌም በሚኖረው አለቃ ላይ በመካከላቸውም በሚኖሩት በእስራኤል ቤት ሁሉ ላይ ነው በላቸው።
11 ፤ ደግሞም። እኔ ምልክታችሁ ነኝ፤ እኔ እንዳደረግሁ እንዲሁ ይደረግባቸዋል፥ እነርሱም በስደት ወደ ምርኮ ይሄዳሉ በል።
12 ፤ በመካከላቸውም የሚኖረው አለቃ በጫንቃው ላይ አንግቶ በጨለማ ይወጣል፤ በዚያ ያወጡ ዘንድ ግንቡን ይነድላሉ፥ በዓይኑም ምድርን እንዳያይ ፊቱን ይሸፍናል።
13 ፤ መረቤንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ በወጥመዴም ይያዛል፥ ወደ ከለዳውያንም ምድር ወደ ባቢሎን አመጣዋለሁ፤ ሆኖም አያያትም በዚያም ይሞታል።
14 ፤ ሊረዱትም በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ጭፍሮቹንም ሁሉ ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፤ በኋላቸውም ሰይፍ እመዝዛለሁ።
15 ፤ በአሕዛብም መካከል በበተንኋቸው ጊዜ፥ በአገሮችም በዘራኋቸው ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
16 ፤ በሚሄዱባቸውም አሕዛብ መካከል ርኵሰታቸውን ሁሉ ይናገሩ ዘንድ ከሰይፍና ከራብ ከቸነፈርም ጥቂቶች ሰዎችን ከእነርሱ አስቀራለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
17 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
18 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ እንጀራህን በድንጋጤ ብላ ውኃህንም በመንቀጥቀጥና በኀዘን ጠጣ፤
19 ፤ ለምድሪቱም ሕዝብ። ጌታ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ስለሚኖሩ ስለ እስራኤልም ምድር እንዲህ ይላል። ስለሚኖሩባት ሁሉ ግፍ ምድሪቱ ከነሞላዋ ትጠፋ ዘንድ እንጀራቸውን በችግር ይበላሉ ወኃቸውንም በድንጋጤ ይጠጣሉ።
20 ፤ ሰዎች የሚኖሩባቸው ከተሞች ባድማ ይሆናሉ ምድሪቱም ውድማ ትሆናለች፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ በላቸው።
21 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
22 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ምድር። ዘመኑ ረዝሞአል ራእዩም ሁሉ ጠፍቶአል የምትሉት ምሳሌ ምንድር ነው?
23 ፤ ስለዚህ እንዲህ በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህን ምሳሌ አስቀረዋለሁ በእስራኤልም ዘንድ ደግሞ ምሳሌ አድርገው አይናገሩትም፤ አንተ ግን። ዘመኑና የራእዩ ሁሉ ነገር ቀርቦአል በላቸው።
24 ፤ ከዚህም በኋላ በእስራኤል ቤት መካከል ከንቱ ራእይና ውሸተኛ ምዋርት አይሆንም።
25 ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እናገራለሁ የምናገረውም ቃል ይፈጸማል፥ ደግሞም አይዘገይም፤ እናንተ ዓመፀኛ ቤት ሆይ፥ በዘመናችሁ ቃሌን እናገራለሁ እፈጽመውማለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
26 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
27 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ የእስራኤል ቤት። ይህች የሚያያት ራእይ ለብዙ ዘመን ናት፥ እርሱም ለሩቅ ወራት ትንቢት ይናገራል ይላሉ።
28 ፤ ስለዚህ በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የምናገረው ቃል ይፈጸማል እንጂ ከቃሌ ሁሉ ደግሞ የሚዘገይ የለም፥ ይላል እግዚአብሔር።