ምዕራፍ 27

የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ አንተ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ጢሮስ ሙሾ አድርግ፥
3 ፤ በባሕር መግቢያ የምትኖር በብዙም ደሴቶች ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ጋር ንግድን የምታደርግ ጢሮስንም እንዲህ በላት። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጢሮስ ሆይ፥ አንቺ። በውበት ፍጹም ነኝ ብለሻል።
4 ፤ ዳርቻሽ በባሕር ውስጥ ነው፤ ሠሪዎችሽ ውበትሽን ፈጽመዋል።
5 ፤ ሳንቃዎችሽን ሁሉ ከሳኔር ጥድ ሠርተዋል፥ ደቀልንም ይሠሩልሽ ዘንድ ከሊባኖስ ዝግባ ወስደዋል።
6 ፤ ከባሳን ኮምቦል መቅዘፊያሽን ሠርተዋል፥ በዝሆን ጥርስ ከታሻበ ከኪቲም ደሴቶች ዛፍ መቀመጫዎችሽን ሠርተዋል።
7 ፤ ዓላማ እንዲሆንልሽ ሸራሽ ከግብጽ በፍታና ከወርቅ ዘቦ ተሠርቶአል፥ መደረቢያሽም ከኤሊሳ ደሴቶች ሰማያዊና ቀይ ሐር ተሠርቶአል።
8 ፤ የሲዶናና የአራድ ሰዎች ቀዛፎችሽ ነበሩ፤ ጢሮስ ሆይ፥ ጥበበኞችሽ በአንቺ ዘንድ ነበሩ የመርከቦችሽም መሪዎች ነበሩ።
9 ፤ በአንቺ ውስጥ የነበሩ የጌባል ሽማግሌዎችና ጥበበኞችዋ ስብራትሽን ይጠግኑ ነበር፤ ከአንቺም ጋር ይነግዱ ዘንድ የባሕር መርከቦች ሁሉና መርከበኞቻቸው በመካከልሽ ነበሩ።
10 ፤ ፋርስና ሉድ ፉጥም በሠራዊትሽ ሰልፈኞችሽ ነበሩ፤ ጋሻና ራስ ቍርም በአንቺ ውስጥ ያንጠለጥሉ ነበር፤ እነርሱም ውበትሽን ሰጡ።
11 ፤ የአራድ ሰዎችና ሠራዊቶችሽ በቅጥሮችሽ ላይ በዙሪያ ነበሩ፥ ገማዳውያንም በግንቦችሽ ውስጥ ነበሩ፤ ጋሻቸውንም በዙሪያ በቅጥርሽ ላይ አንጠለጠሉ፥ ውበትሽንም ፈጽመዋል።
12 ፤ ከብልጥግናሽ ሁሉ ብዛት የተነሣ ተርሴስ ነጋዴሽ ነበረች፤ በብርና በብረት በቈርቈሮና በእርሳስ ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር።
13 ፤ ያዋንና ቶቤል ሞሳሕም ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ የሰዎችን ነፍሳትና የናሱን ዕቃ ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር።
14 ፤ ከቴርጋማ ቤትም የነበሩት ሰዎች በፈረሶችና በፈረሰኞች በበቅሎዎችም ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር።
15 ፤ የድዳን ሰዎች ነጋዴዎችሽ ነበሩ። ብዙ ደሴቶች የእጅሽ ገበያዎች ነበሩ፤ ይለውጡ ዘንድ የዝሆን ጥርስና ዞጲ አመጡልሽ።
16 ፤ ከሥራሽ ብዛት የተነሣ ሶርያ ነጋዴሽ ነበረች በበሉርና በቀይ ሐር በወርቀ ዘቦም በጥሩ በፍታም በዛጐልም በቀይ ዕንቍም ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር።
17 ፤ ይሁዳና የእስራኤል ምድር ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ የሚኒትን ስንዴ ጣፋጭም እንጐቻ፥ ማር ዘይትም በለሳንም ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር።
18 ፤ ከሥራሽ ብዛትና ከብልጥግናሽ ሁሉ ብዛት የተነሣ ደማስቆ ነጋዴሽ ነበረች፤ በኬልቦን የወይን ጠጅ በነጭም በግ ጠጕር ይነግዱ ነበር።
19 ፤ ዌንዳንና ያዋን ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር፤ ከኦሴል የተሠራ ብረትና ብርጕድ ቀረፋም ሸቀጥሽ ነበረ።
20 ፤ ድዳን በከብት ላይ ለመቀመጥ በመረሻት ነጋዴሽ ነበረች።
21 ፤ ዓረብና የቄዳር አለቆች ሁሉ የእጅሽ ነጋዴዎች ነበሩ፤ በጠቦቶችና በአውራ በጎች በፍየሎችም በእነዚህ ከአንቺ ጋር ይነግዱ ነበር።
22 ፤ የሳባና የራዕማ ነጋዴዎች እነዚህ ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ በጥሩ ሽቶና በክብር ድንጋይ ሁሉ በወርቅም ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር።
23 ፤ ካራንና ካኔ ዔድንም ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ አሦርና ኪልማድ ነጋዴዎችሽ ነበሩ።
24 ፤ እነዚህ ባማረ ልብስ በሰማያዊ ካባ በወርቀ ዘቦም፥ በዝግባ በተሠራች በገመድም በታሰረች በግምጃም በተሞላች ሳጥን በገበያሽ ይነግዱ ነበር።
25 ፤ የተርሴስ መርከቦች ሸቀጥሽን የሚሸከሙ ነበሩ፤ አንቺም ተሞልተሽ ነበር በባሕርም ውስጥ እጅግ ከበርሽ።
26 ፤ ቀዛፊዎችሽ ወደ ትልቁ ወኃ አመጡሽ፤ የምሥራቅ ነፋስ በባሕር ውስጥ ሰበረሽ።
27 ፤ ብልጥግናሽና ሸቀጥሽ ንግድሽም መርከበኞችሽም መርከብ መሪዎችሽም ሰባራሽንም የሚጠግኑ ነጋዴዎችሽም በአንቺም ዘንድ ያሉ ሰልፈኞችሽ ሁሉ በውስጥሽ ካሉት ጉባኤ ሁሉ ጋር በወደቅሽበት ቀን በባሕር ውስጥ ይወድቃሉ።
28 ፤ ከመርከብ መሪዎች ጩኸት ድምፅ የተነሣ በዙሪያሽ ያሉ ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ።
29 ፤ ቀዛፊዎችም ሁሉ መርከበኞችም መርከብ መሪዎችም ሁሉ ከመርከቦቻቸው ይወርዳሉ በመሬትም ላይ ይቆማሉ፤
30 ፤ ድምፃቸውንም በአንቺ ላይ ያሰማሉ፥ ምርር ብለውም ይጮኻሉ፥ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ይነሰንሳሉ፥ በአመድም ውስጥ ይንከባለላሉ፤
31 ፤ ስለ አንቺም የራሳቸውን ጠጕር ይላጫሉ ማቅም ያሸርጣሉ በነፍስ ምሬትም ስለ አንቺ መራራ ልቅሶ ያለቅሳሉ።
32 ፤ በትካዜያቸውም ልቅሶ ያነሡልሻል፥ ስለ አንቺም ሙሾ ያሞሻሉ እንዲህም ይላሉ። በባሕር መካከል ጠፍቶ እንደ ቀረ እንደ ጢሮስ ያለ ማን ነው?
33 ፤ ሸቀጥሽ ከባሕር በወጣ ጊዜ ብዙ አሕዛብን አጥግበሻል፤ በብልጥግናሽና በንግድሽ ብዛት የምድርን ነገሥታት ባለ ጠጎች አድርገሻል።
34 ፤ አሁን ግን በጥልቅ ውኃ ውስጥ በባህር ተሰብረሻል ንግድሽና ጉባኤሽ ሁሉ በመካከልሽ ወድቀዋል።
35 ፤ በደሴቶሽ የሚኖሩ ሁሉ ተደንቀውብሻል፥ ነገሥታቶቻቸውም እጅግ ፈርተዋል ፊታቸውም ተለውጦአል።
36 ፤ የአሕዛብ ነጋዴዎች አፍዋጩብሽ፤ አንቺ ለድንጋጤ ሆነሻል፥ እስከ ዘላለምም አትገኚም።