ምዕራፍ 18

የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ ስለ እስራኤል ምድር። አባቶች ጨርቋ የወይን ፍሬ በሉ፥ የልጆችም ጥርሶች ጠረሱ ብላችሁ የምትመስሉት ምሳሌ ምንድር ነው?
3 ፤ እኔ ሕያው ነኝና እንግዲህ ወዲህ ይህን ምሳሌ በእስራኤል ዘንድ አትመስሉትም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
4 ፤ እነሆ፥ ነፍሳት ሁሉ የእኔ ናቸው፤ የአባት ነፍስ የእኔ እንደ ሆነች ደግሞ የልጅ ነፍስ የእኔ ናት፤ ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች።
5 ፤ ሰውም ጻድቅ ቢሆን ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ፥
6 ፤ በተራራም ላይ ባይበላ ዓይኞቹንም ወደ እስራኤል ቤት ጣዖታት ባያነሣ የባልንጀራውንም ሚስት ባያረክስ አደፍም ወዳለባት ሴት ባይቀርብ፤
7 ፤ ሰውንም ባያስጨንቅ ለባለ ዕዳም መያዣውን ቢመልስ ፈጽሞም ባይቀማ ከእንጀራውም ለተራበ ቢሰጥ የተራቈተውንም በልብስ ቢያለብስ፤
8 ፤ በአራጣ ባያበድር፥ ትርፎቻም ባይወስድ፥ እጁንም ከኃጢአት ቢመልስ፥ በሰውና በሰው መካከልም የእውነትን ፍርድ ቢፈርድ፤
9 ፤ በትእዛዜም ቢሄድ፥ እውነትንም ለማድረግ ፍርዴን ቢጠብቅ፥ እርሱ ጻድቅ ነው፥ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
10 ፤ እርሱም ቀማኛና ደም አፍሳሽ ልጅ ከዚህም ሁሉ አንዳቸውን የሚያደርገውን ቢወልድ፥
11 ፤ እርሱም ጻድቅ አባቱ የሠራውን ሁሉ ባይሠራ በተራራም ላይ ቢበላ የባልንጀራውንም ሚስት ቢያረክስ፥
12 ፤ ድሀውንና ችግረኛውንም ቢያስጨንቅ ቢቀማም መያዣውንም ባይመልስ ዓይኖቹንም ወደ ጣዖታት ቢያነሣ ርኩስን ነገር ቢያደርግ፥
13 ፤ በአራጣ ቢያበድር፥ ትርፎቻም ቢወስድ፥ በውኑ እርሱ በሕይወት ይኖራልን? በሕይወት አይኖርም፤ ይህን ርኵሰት ሁሉ አድርጎአልና ፈጽሞ ይሞታል፤ ደሙ በላዩ ላይ ይሆናል።
14 ፤ እነሆም፥ ልጅ ቢወልድ፥ እርሱም አባቱ የሠራውን ኃጢአት አይቶ ቢፈራ እንዲህም ባይሠራ፥
15 ፤ በተራራ ላይ ባይበላ ዓይኖቹንም ወደ እስራኤል ቤት ጣዖታት ባያነሣ የባልንጀራውንም ሚስት ባያረክስ፥
16 ፤ ሰውንም ባያስጨንቅ መያዣውን ባይወስድ ባይቀማም ከእንጀራውም ለተራበ ቢሰጥ ለተራቈተውም ልብስን ቢያለብስ፥
17 ፤ እጁንም ድሀን ከመበደል ቢመልስ አራጣን ትርፎቻንም ባይወስድ ፍርዴንም ቢያደርግ በትእዛዜም ቢሄድ፥ እርሱ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ በአባቱ ኃጢአት አይሞትም።
18 ፤ አባቱ ግን ፈጽሞ በድሎአልና፥ ወንድሙንም ቀምቶአልና፥ በሕዝቡም መካከል ክፉን ነገር አድርጎአልና እነሆ፥ እርሱ በበደሉ ይሞታል።
19 ፤ እናንተ ግን። ልጅ የአባቱን ኃጢአት ስለ ምን አይሸከምም? ትላላችሁ። ልጅ ፍርድንና ቅን ነገርን ባደረገ ትእዛዜንም ሁሉ በጠበቀና ባደረገ ጊዜ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል።
20 ፤ ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች፤ ልጅ የአባቱን ኃጢአት አይሸከምም፥ አባትም የልጁን ኃጢአት አይሸከምም፤ የጻድቁ ጽድቅ በራሱ ላይ ይሆናል፥ የኃጢአተኛውም ኃጢአት በራሱ ላይ ይሆናል።
21 ፤ ኃጢአተኛውም ካደረጋት ኃጢአት ሁሉ ቢመለስ ትእዛዜንም ሁሉ ቢጠብቅ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም።
22 ፤ የበደለው በደል ሁሉ አይታሰብበትም፤ በሠራው ጽድቅ በሕይወት ይኖራል።
23 ፤ በውኑ ኃጢአተኛ ይሞት ዘንድ እፈቅዳለሁን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከመንገዱስ ይመለስና በሕይወት ይኖር ዘንድ አይደለምን?
24 ፤ ጻድቁ ግን ከጽድቁ ቢመለስ ኃጢአትንም ቢሠራ ኃጢአተኛውም እንደሚያደርገው ርኵሰት ሁሉ ቢያደርግ፥ በሕይወት ይኖራልን? የሠራት ጽድቅ ሁሉ አትታሰብለትም፤ ባደረገው ዓመፅና በሠራት ኃጢአት በዚያች ይሞታል።
25 ፤ እናንተ ግን። የጌታ መንገድ የቀናች አይደለችም ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እንግዲህ ስሙ፤ በውኑ መንገዴ የቀናች አይደለችምን? ይልቅስ የእናንተ መንገድ ያልቀናች አይደለችምን?
26 ፤ ጻድቁ ከጽድቁ ቢመለስ፥ ኃጢአትንም በሠራ ጊዜ፥ በዚያም ቢሞት፥ እርሱ ባደረገው በደል ይሞታል።
27 ፤ ኃጢአተኛውም ከሠራው ኃጢአት ቢመለስ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ነፍሱን ይጠብቃል።
28 ፤ አስቦ ከሠራው በደል ሁሉ ተመልሶአልና ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም።
29 ፤ ነገር ግን የእስራኤል ቤት። የጌታ መንገድ የቀናች አይደለችም ይላል። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በውኑ መንገዴ የቀናች አይደለችምን? ይልቅስ የእናንተ መንገድ ያልቀናች አይደለችምን?
30 ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለዚህ እንደ መንገዱ በየሰዉ ሁሉ እፈርድባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ንስሐ ግቡ ኃጢአትም ዕንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ።
31 ፤ የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ ምን ትሞታላችሁ?
32 ፤ የምዋቹን ሞት አልፈቅድምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ።