ምዕራፍ 2

እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ በእግርህ ቁም እኔም እናገርሃለሁ አለኝ።
2 ፤ በተናገረኝም ጊዜ መንፈስ ገባብኝ በእግሬም አቆመኝ፥ የሚናገረኝንም ሰማሁ።
3 ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ በእኔ ላይ ወደ ዐመፁ ወደ ዓመፀኞች ሰዎች ወደ እስራኤል ልጆች እልክሃለሁ። እነርሱና አባቶቻቸው እስከ ዛሬ ድረስ ዐመፁብኝ።
4 ፤ እነርሱ ፊታቸው የተጨማተረ ልባቸውም የደነደነ ልጆች ናቸው። እኔ ወደ እነርሱ እልክሃለሁ፤ አንተም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በላቸው።
5 ፤ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ ነቢይ በመካከላቸው እንዳለ ያውቃሉ።
6 ፤ አንተ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ኵርንችትና እሾህ ከአንተ ጋር ቢኖሩም፥ አንተም በጊንጦች መካከል ብትቀመጥም፥ አትፍራቸው፥ ቃላቸውንም አትፍራ፤ አንተ ቃላቸውን አትፍራ፥ ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ፤ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና።
7 ፤ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ ቃሌን ትነግራቸዋለህ።
8 ፤ አንተ ግን፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የምነግርህን ስማ፤ እንደዚያ እንደ ዓመፀኛው ቤት ዓመፀኛ አትሁን፤ አፍህን ክፈት የምሰጥህንም ብላ።
9 ፤ ባየሁም ጊዜ፥ እነሆ፥ እጅ ወደ እኔ ተዘርግታ ነበር፤ እነሆም፥ የመጽሐፍ ጥቅልል ነበረባት።
10 ፤ በፊቴም ዘረጋው፥ በውስጥና በውጭም ተጽፎበት ነበር፤ ልቅሶና ኀዘን ዋይታም ተጽፎበት ነበር።