ምዕራፍ 33

የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለሕዝብህ ልጆች ተናገር እንዲህም በላቸው። ሰይፍን በምድር ላይ ባመጣሁ ጊዜ፥ የምድር ሕዝብ ከመካከላቸው ሰውን ወስደው ለራሳቸው ጕበኛ ቢያደርጉ፥
3 ፤ እርሱም በምድር ላይ የመጣውን ሰይፍ ባየ ጊዜ መለከትን ቢነፋ ሕዝቡንም ቢያስጠነቅቅ፥
4 ፤ የመለከቱን ድምፅ የሚሰማ ሰው ባይጠነቀቅ፥ ሰይፍ መጥቶ ቢወስደው፥ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል።
5 ፤ የመለከቱን ድምፅ ሰምቶ ስላልተጠነቀቀ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፤ ቢጠነቀቅስ ኖሮ ነፍሱን ባዳነ ነበር።
6 ፤ ጕበኛው ግን ሰይፍ ሲመጣ ቢያይ መለከቱንም ባይነፋ ሕዝቡንም ባያስጠነቅቅ ሰይፍም መጥቶ አንድ ሰው ከእርሱ ቢወስድ፥ እርሱ በኃጢአቱ ተወስዶአል ደሙን ግን ከጕበኛው እጅ እፈልጋለሁ።
7 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ጕበኛ አድርጌሃለሁ፤ ከአፌ ቃሌን ስማ ከእኔም ዘንድ አስጠንቅቃቸው።
8 ፤ ኃጢአተኛውን። ኃጢአተኛ ሆይ፥ በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁ ጊዜ፥ ኃጢአተኛውን ከመንገዱ ታስጠነቅቅ ዘንድ ባትናገር ያ ኃጢአተኛ በኃጢአቱ ይሞታል፥ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ።
9 ፤ ነገር ግን ከመንገዱ ይመለስ ዘንድ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቀው እርሱም ከመንገዱ ባይመለስ፥ በኃጢአቱ ይሞታል አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል።
10 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤልን ቤት። እናንተ። በደላችንና ኃጢአታችን በላያችን አሉ እኛም ሰልስለንባቸዋል፤ እንዴትስ በሕይወት እንኖራለን? ብላችሁ ተናግራችኋል በላቸው።
11 ፤ እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ተመለሱ፥ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ? በላቸው።
12 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የሕዝብህን ልጆች እንዲህ በላቸው። በበደለበት ቀን የጻድቅ ጽድቁ አያድነውም፥ ኃጢአተኛም ከኃጢአቱ በተመለሰበት ቀን በኃጢአቱ አይሰናከልም፤ ጻድቁም ኃጢአት በሠራበት ቀን በጽድቁ በሕይወት አይኖርም።
13 ፤ እኔ ጻድቁን። በእርግጥ በሕይወት ትኖራለህ ባልሁ ጊዜ፥ እርሱ በጽድቁ ታምኖ ኃጢአት ቢሠራ በሠራው ኃጢአት ይሞታል እንጂ ጽድቁ አይታሰብለትም።
14 ፤ እኔም ኃጢአተኛውን። በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁ ጊዜ፥ እርሱ ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ፥
15 ፤ ኃጢአተኛውም መያዣን ቢመልስ የነጠቀውንም ቢመልስ በሕይወትም ትእዛዝ ቢሄድ ኃጢአትም ባይሠራ፥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም።
16 ፤ የሠራው ኃጢአት ሁሉ አይታሰብበትም፤ ፍርድንና ቅን ነገርን አድርጎአል፤ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል።
17 ፤ ነገር ግን የሕዝብህ ልጆች። የጌታ መንገድ የቀና አይደለም ይላሉ፤ ነገር ግን የእነርሱ መንገድ የቀና አይደለም።
18 ፤ ጻድቅ ከጽድቁ ተመልሶ ኃጢአትን ቢሠራ ይሞትባታል።
19 ፤ ኃጢአተኛውም ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ በሕይወት ይኖርበታል።
20 ፤ እናንተ ግን። የጌታ መንገድ የቀና አይደለም ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በእያንዳንዳችሁ ላይ እንደ መንገዳችሁ እፈርድባችኋለሁ።
21 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በተማረክን በአሥራ ሁለተኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን ከኢየሩሳሌም ያመለጠ አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ። ከተማይቱ ተመታች አለኝ።
22 ፤ ያመለጠውም ሳይመጣ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረች፥ በነጋውም ወደ እኔ እስኪመጣ ድረስ አፌን ከፈተ፤ አፌም ተከፈተች ከዚያም በኋላ እኔ ዲዳ አልሆንሁም።
23 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
24 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ምድር ባሉ በባድማ ስፍራዎች የተቀመጡ። አብርሃም ብቻውን ሳለ ምድሪቱን ወረሰ፤ እኛም ብዙዎች ነን ምድሪቱም ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታለች ይላሉ።
25 ፤ ስለዚህ እንዲህ በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከደም ጋር ትበላላችሁ፥ ዓይናችሁንም ወደ ጣዖቶቻችሁ ታነሣላችሁ፥ ደምንም ታፈስሳላችሁ፤ በውኑ ምድሪቱን ትወርሳላችሁን?
26 ፤ ሰይፋችሁን ይዛችሁ ቆማችኋል፥ ርኩስ ነገርን ታደርጋላችሁ፥ የባልንጀሮቻችሁንም ሚስቶች ታስነውራላችሁ፤ በውኑ ምድሪቱን ትወርሳላችሁን?
27 ፤ እንዲህም በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ሕያው ነኝና በባድማ ስፍራዎች ያሉ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ በምድረ በዳ ያለውን ለአራዊት መብል አድርጌ እሰጣለሁ፥ በአምባዎችና በዋሾች ያሉ በቸነፈር ይሞታሉ።
28 ፤ ምድሪቱንም ባድማና ውድማ አደርጋታለሁ የኃይልዋም ትዕቢት ይቀራል፥ የእስራኤልም ተራሮች ባድማ ይሆናሉ፥ ማንም አያልፍባቸውም።
29 ፤ ስላደረጉትም ርኵሰት ሁሉ ምድሪቱን ባድማና ውድማ ባደርግሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
30 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የሕዝብህ ልጆች በቅጥር አጠገብና በቤት ደጆች ውስጥ ስለ አንተ ይናገራሉ፥ እርስ በርሳቸውም፥ አንዱ ከአንዱ ጋር። እንሂድና እግዚአብሔር ያለው ቃል ምን እንደ ሆነ እንስማ ብለው ይናገራሉ።
31 ፤ ሕዝብ እንደሚመጣ ወደ አንተ ይመጣሉ፥ እንደ ሕዝቤም በፊትህ ይቀመጣሉ፥ ቃልህንም ይሰማሉ ነገር ግን አያደርጉትም፤ በአፋቸው ብዙ ፍቅር ይገልጣሉ፥ ልባቸው ግን ስስታቸውን ትከተላለች።
32 ፤ እነሆ፥ አንተ መልካም ድምፅ እንዳለው እንደሚወደድ መዝሙር ማለፊያም አድርጎ በገና እንደሚጫወት ሰው ሆነህላቸዋል፤ ቃልህንም ይሰማሉ ነገር ግን አያደርጉትም።
33 ፤ እነሆ፥ ይህ ይመጣል፤ በመጣም ጊዜ እነርሱ ነቢይ በመካከላቸው እንደ ነበረ ያውቃሉ።