ምዕራፍ 34

የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር፥ እረኞችንም እንዲህ በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች በጎችን ያሰማሩ ዘንድ አይገባቸውምን?
3 ፤ ጮማውን ትበላላችሁ ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ፥ የወፈሩትን ታርዳላችሁ፤ በጎቹን ግን አታሰማሩም።
4 ፤ የደከመውን አላጸናችሁትም የታመመውንም አላከማችሁትም የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም የባዘነውንም አልመለሳችሁትም የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም በኃይልና በጭቈናም ገዛችኋቸው።
5 ፤ እረኛንም በማጣት ተበተኑ፥ ለምድርም አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ፥ ተበተኑም።
6 ፤ በጎቼ በተራሮች ሁሉና በረዘሙ ኮረብቶች ሁሉ ላይ ተቅበዝብዘዋል፥ በጎቼም በምድር ፊት ሁሉ ላይ ተበትነዋል፤ የሚሻም የሚፈልግም አልነበረም።
7 ፤ ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤
8 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ሕያው ነኝና እረኛ ስለሌለ እረኞቼም በጎቼን ስላልፈለጉ እረኞችም ራሳቸውን እንጂ በጎቼን ስላላሰማሩ፥ በጎቼ ንጥቂያ ሆነዋልና፥ በጎቼም ለምድር አራዊት ሁሉ መብል ሆነዋልና
9 ፤ ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤
10 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በእረኞች ላይ ነኝ፥ በጎቼንም ከእጃቸው እፈልጋለሁ፥ በጎቼንም ከማሰማራት አስተዋቸዋለሁ። ከዚያም ወዲያ እረኞች ራሳቸውን አያሰማሩም፤ በጎቼንም ከአፋቸው አድናለሁ፥ መብልም አይሆኑላቸውም።
11 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ እኔ ራሴ በጎቼን እሻለሁ እፈልግማለሁ።
12 ፤ እረኛ በተበተኑት በጎች መካከል ባለ ጊዜ መንጋውን እንደሚፈልግ፥ እንዲሁ በጎቼን እፈልጋለሁ፤ በደመናና በጨለማ ቀን ከተበተኑት ስፍራ ሁሉ አድናቸዋለሁ።
13 ፤ ከአሕዛብም ዘንድ አወጣቸዋለሁ ከአገሮችም እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደ ገዛ አገራቸውም አመጣቸዋለሁ፤ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በፈሳሾችም አጠገብ በምድርም ላይ ሰዎች በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ አሰማራቸዋለሁ።
14 ፤ በመልካም ማሰማርያ እሰማራቸዋለሁ ጕረኖአቸውም በረጅሞቹ በእስራኤል ተራሮች ላይ ይሆናል፤ በዚያ በመልካም ጕረኖ ውስጥ ይመሰጋሉ፥ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በለመለመ ማሰማርያ ይሰማራሉ።
15 ፤ እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ አስመስጋቸውማለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
16 ፤ የጠፋውንም እፈልጋለሁ የባዘነውንም እመልሳለሁ የተሰበረውንም እጠግናለሁ የደከመውንም አጸናለሁ፤ የወፈረውንና የበረታውንም አጠፋለሁ፤ በፍርድም እጠብቃቸዋለሁ።
17 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እናንተም መንጋዬ ሆይ፥ እነሆ፥ በበግና በበግ መካከል፥ በአውራ በግና በአውራ ፍየልም መካከል፥ እፈርዳለሁ።
18 ፤ የቀረውን ማሰማርያችሁን በእግራችሁ የረገጣችሁት፥ በመልካሙ ማሰማርያ መሰማራታችሁ ባይበቃችሁ ነውን? የቀረውንስ ውኃ በእግራችሁ ያደፈረሳችሁት፥ ጥሩውን ውኃ መጠጣታችሁ ባይበቃችሁ ነውን?
19 ፤ በጎቼም በእግራችሁ በረገጣችሁት ይሰማራሉ በእግራችሁም ያደፈረሳችሁትን ይጠጣሉ።
20 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል። እነሆ፥ እኔ በወፈሩት በጎችና በከሱት በጎች መካከል እፈርዳለሁ።
21 ፤ እስክትበትኑአቸው ድረስ በእንቢያና በትከሻ ስለምትገፉአቸው የደከሙትንም ሁሉ በቀንዳችሁ ስለምትወጉአቸው፥
22 ፤ ስለዚህ መንጋዬን አድናለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ንጥቂያ አይሆኑም፤ በበግና በበግ መካከልም እፈርዳለሁ።
23 ፤ በላያቸውም አንድ እረኛ አቆማለሁ እርሱም ያሰማራቸዋል፥ እርሱም ባሪያዬ ዳዊት ነው፤ ያሰማራቸዋል እረኛም ይሆናቸዋል።
24 ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላክ እሆናቸዋለሁ ባሪያዬም ዳዊት በመካከላቸው አለቃ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።
25 ፤ የሰላምን ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር እገባለሁ ክፉዎችንም አራዊት ከምድር አጠፋለሁ፤ ተዘልለውም በምድረ በዳ ይኖራሉ በዱርም ውስጥ ይተኛሉ።
26 ፤ እነርሱንና በኮረብታዬ ዙሪያ ያሉትን ስፍራዎች ለበረከት አደርጋቸዋለሁ፥ ዝናቡንም በጊዜው አወርዳለሁ፤ የበረከት ዝናብ ይሆናል።
27 ፤ የምድረ በዳም ዛፍ ፍሬውን ይሰጣል ምድርም ቡቃያዋን ትሰጣለች፥ በምድራቸውም ተዘልለው ይኖራሉ የቀንበራቸውንም ማነቆ በሰበርሁ ጊዜ ከሚገዙአቸውም እጅ ባዳንኋቸው ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
28 ፤ እንግዲህም ለአሕዛብ ንጥቂያ አይሆኑም የምድርም አራዊት አይበሉአቸውም፤ ተዘልለውም ይቀመጣሉ የሚያስፈራቸውም የለም።
29 ፤ የዝናን ተክል አቆምላቸዋለሁ እንግዲህም ከራብ የተነሣ በምድር አያልቁም፤ የአሕዛብንም ስድብ ከእንግዲህ ወዲህ አይሸከሙም።
30 ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ከእነርሱ ጋር እንዳለሁ፥ እነርሱም የእስራኤል ቤት ሕዝቤ እንደ ሆኑ ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
31 ፤ እናንተም በጎቼ፥ የማሰማርያዬ በጎች፥ ሰዎች ናችሁ እኔም አምላካችሁ ነኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።