ምዕራፍ 48

የነገዶችም ስም ይህ ነው። በሔትሎን መንገድ አጠገብ ወደ ሐማት መግቢያ በደማስቆም ድንበር ባለው በሐጸርዔናን በሐማትም አጠገብ በሰሜን በኩል ካለው ከሰሜን ድንበር ይጀምራል። ወርዳቸውም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ይሆናል። ለዳን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
2 ፤ ከዳንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለአሴር አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
3 ፤ ከአሴርም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለንፍታሌም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
4 ፤ ከንፍታሌም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለምናሴ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
5 ፤ ከምናሴም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለኤፍሬም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
6 ፤ ከኤፍሬምም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለሮቤል አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
7 ፤ ከሮቤልም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለይሁዳ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
8 ፤ ከይሁዳም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለመባ የሆነ የዕጣ ክፍል ይሆናል፤ ወርዱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል ርዝመቱም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ከዕጣ ክፍሎች እንደ አንዱ ይሆናል፥ መቅደሱም በመካከሉ ይሆናል።
9 ፤ ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት መባ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ወርዱም ሃያ ሺህ ክንድ ይሆናል።
10 ፤ ለእነዚህም ለካህናቱ የተቀደሰ መባ ይሆናል፤ በሰሜን በኩል ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ፥ በምዕራብም በኩል ወርዱ አሥር ሺህ፥ በምሥራቅም በኩል ወርዱ አሥር ሺህ፥ በደቡብም በኩል ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል። የእግዚአብሔርም መቅደስ በመካከሉ ይሆናል።
11 ፤ የእስራኤልም ልጆች በሳቱ ጊዜ፥ ሌዋውያን እንደ ሳቱ ላልሳቱት ሥርዓቴን ለጠበቁት ከሳዶቅ ልጆች ወገን ለተቀደሱት ካህናት ይሆናል።
12 ፤ ከምድርም መባ የተለየ መባ ይሆንላቸዋል፥ ከሁሉም ይልቅ የተቀደሰ ይሆናል፤ በሌዋውያን ድንበር አጠገብ ይሆናል።
13 ፤ በካህናቱም ድንበር አንጻር ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም አሥር ሺህ የሆነ ዕጣ ለሌዋውያን ይሆናል፤ ርዝመቱ ሁሉ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም ሀያ ሺህ ክንድ ይሆናል።
14 ፤ ለእግዚአብሔርም የተቀደሰ ነውና ከእርሱ ምንም አይሸጡም አይለውጡምም፥ የምድሩም በኵራት አይፋለስም።
15 ፤ በሀያ አምስቱም ሺህ አንጻር አምስት ሺህ ወርድ ያለው የቀረ ስፍራ ለከተማይቱ ለጋራ ጉዳይዋ፥ ለመኖሪያ ለማስማርያም ይሆናል፤ ከተማይቱም በመካከሉ ትሆናለች።
16 ፤ ልክዋም ይህ ነው፤ በሰሜን በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በደቡብም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በምሥራቅም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በምዕራብም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ይሆናል።
17 ፤ ለከተማይቱም ማሰማርያ ይኖራታል፤ በሰሜን በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በደቡብም በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በምሥራቅም በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በምዕራብም በኩል ሁለት መቶ አምሳ ክንድ ይሆናል።
18 ፤ በተቀደሰው መባ አንጻር የተረፈው ርዝመቱ ወደ ምሥራቅ አሥር ሺህ ወደ ምዕራብም አሥር ሺህ ክንድ ይሆናል። በተቀደሰው መባ አንጻር ይሆናል። ፍሬውም ከተማይቱን ለሚያገለግሉ ለመብል ይሆናል።
19 ፤ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከተማይቱን የሚያገለግሉ ያርሱታል።
20 ፤ መባው ሁሉ ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል፤ የተቀደሰውን መባ ከከተማይቱ ይዞታ ጋር አራት ማዕዘን አድርጋችሁ ትሰጣላችሁ።
21 ፤ በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ በዚህና በዚያ ወገን የቀረው ለአለቃው ይሆናል፤ በመባው በሀያ አምስቱ ሺህ ፊት ወደ ምሥራቁ ድንበር፥ በምዕራብም በኩል በሀያ አምስቱ ሺህ ፊት ወደ ምዕራቡ ድንበር፥ እንደ ዕጣ ክፍል ሁሉ መጠን፥ ለአለቃው ይሆናል፤ የተቀደሰውም መባና ቤተ መቅደሱ በመካከሉ ይሆናል።
22 ፤ የሌዋውያንም ርስት የከተማይቱም ይዞታ ለአለቃው በሆነው መካከል ይሆናል፤ በይሁዳ ድንበርና በብንያም ድንበር መካከል የአለቃ ዕጣ ክፍል ይሆናል።
23 ፤ ለቀሩትም ነገዶች እንዲህ ይሆናል፤ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለብንያም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
24 ፤ ከብንያምም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለስምዖን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
25 ፤ ከስምዖንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለይሳኮር አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
26 ፤ ከይሳኮርም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለዛብሎን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
27 ፤ ከዛብሎንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለጋድ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
28 ፤ ከጋድም ድንበር ቀጥሎ በደቡብ በኩል ድንበሩ ከታማር ጀምሮ እስከ ሜሪባ ቃዴስ ውኃ እስከ ግብጽ ወንዝ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሆናል።
29 ፤ ርስት አድርጋችሁ ለእስራኤል ነገዶች በዕጣ የምታካፍሉአት ምድር ይህች ናት፥ የእያንዳንዱም ዕጣ እንደዚህ ነው፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
30 ፤ የከተማይቱም መውጫዎች እነዚህ ናቸው። በሰሜን ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ነው።
31 ፤ የከተማይቱ በሮች እንደ እስራኤል ነገዶች ስም ይሆናሉ፤ በሰሜን በኩል አንዱ የሮቤል በር አንዱም የይሁዳ በር አንዱም የሌዊ በር፥ ሦስት በሮች ይሆናሉ።
32 ፤ በምሥራቁም ወገን አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፤ አንዱ የዮሴፍ በር አንዱም የብንያም በር አንዱም የዳን በር ነው።
33 ፤ በደቡቡም ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፤ አንዱ የስምዖን በር አንዱም የይሳኮር በር አንዱም የዛብሎን በር ነው።
34 ፤ በምዕራቡም ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፤ አንዱ የጋድ በር አንዱም የአሴር በር አንዱም የንፍታሌም በር ነው።
35 ፤ ዙሪያዋም አሥራ ስምንት ሺህ ክንድ ይሆናል፥ ከዚያም ቀን ጀምሮ የከተማይቱ ስም። እግዚአብሔር በዚያ አለ ተብሎ ይጠራል።