ምዕራፍ 5

አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የተሳለን ጐራዴ ውሰድ፥ እንደ ጢም መላጫ ወደ አንተ ትወስደዋለህ፥ ራስህንና ጢምህንም ትላጭበታለህ፤ ሚዛንንም ውሰድ ጠጕሩንም ትከፋፍላለህ።
2 ፤ የመከበብም ወራት በተፈጸመ ጊዜ በከተማይቱ መካከል ሢሶውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ሢሶውንም ወስደህ ዙሪያውን በጐራዴ ትመታለህ፥ ሢሶውንም ወደ ነፋስ ትበትናለህ እኔም በኋላቸው ጐራዴ እመዝዛለሁ።
3 ፤ ከዚያም በጥቂቱ ውሰድ በመጐናጸፊያህም ጫፍ ቋጥራቸው።
4 ፤ ከእነርሱም ደግሞ ወስደህ በእሳት ውስጥ ትጥላለህ በእሳትም ታቃጥላቸዋለህ፤ ከዚያም በእስራኤል ቤት ሁሉ ላይ እሳት ትወጣለች።
5 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህች ኢየሩሳሌም ናት፤ በአሕዛብም መካከል አድርጌአታለሁ፥ አገሮችም በዙሪያዋ አሉ።
6 ፤ እርስዋም ከአሕዛብ ይልቅ ፍርዴን በኃጢአት ለወጠች በዙሪያዋም ካሉ አገሮች ሁሉ ይልቅ ትእዛዜን ተላለፈች፤ ፍርዴን ጥለዋልና፥ በትእዛዜም አልሄዱምና።
7 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዙሪያችሁ ላሉት አሕዛብ ሰበብ ሆናችኋልና፥ በትእዛዜም አልሄዳችሁምና፥ ፍርዴንም አልጠበቃችሁምና፥ በዙሪያችሁም እንዳሉ እንደ አሕዛብ ፍርድ እንኳ አላደረጋችሁምና
8 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እኔ ራሴ በአንቺ ላይ ነኝ፥ አሕዛብም እያዩ ፍርድን በመካከልሽ አደርጋለሁ።
9 ፤ ስለ ርኵሰትሽም ሁሉ ያልሠራሁትን እርሱንም የሚመስል ደግሞ የማልሠራውን ነገር እሠራብሻለሁ።
10 ፤ ስለዚህ በመካከልሽ አባቶች ልጆቻቸውን ይበላሉ ልጆችም አባቶቻቸውን ይበላሉ፤ ፍርድንም አደርግብሻለሁ ከአንቺም የቀረውን ሁሉ ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናለሁ።
11 ፤ ስለዚህ፥ እኔ ሕያው ነኝና በእድፍሽና በርኵሰትሽ መቅደሴን ስላረከስሽ፥ ስለዚህ በእውነት እኔ አሳንስሻለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ዓይኔም አይራራም እኔም አላዝንም።
12 ፤ ከአንቺም ሢሶው በቸነፈር ይሞታል፥ በመካከልሽም በራብ ያልቃል፤ ሢሶውም በዙሪያሽ በሰይፍ ይወድቃል፤ ሢሶውንም ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናለሁ በኋላቸውም ሰይፍ እመዝዛለሁ።
13 ፤ ቍጣዬም ይፈጸማል መዓቴንም እጨርሳለሁ እጽናናማለሁ፥ መዓቴንም በፈጸምሁባቸው ጊዜ እኔ እግዚአብሔር በቅንዓቴ እንደ ተናገርሁ ያውቃሉ።
14 ፤ በዙሪያሽም ባሉ በአሕዛብ መካከል በሚያልፉም ሁሉ ፊት ባድማና መሰደቢያ አደርግሻለሁ።
15 ፤ በቍጣና በመዓት፥ በመዓትም ዘለፋ ፍርድን ባደረግሁብሽ ጊዜ በዙሪያሽ ላሉ አሕዛብ መሰደቢያና መተረቻ፥ ተግሣጽና መደነቂያ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።
16 ፤ ለማጥፋትም የሆነውን፥ አጠፋችሁም ዘንድ የምሰድደውን የራብ ፍላጻ በላያችሁ በሰደድሁ ጊዜ፥ ራብን እጨምርባችኋለሁ፥ የእንጀራችሁንም በትር እሰብራለሁ።
17 ፤ ራብንና ክፉዎችን አራዊት እሰድድባችኋለሁ፥ ልጆቻችሁንም ያጠፋሉ፤ ቸነፈርና ደምም በአንቺ ዘንድ ያልፋሉ፤ ሰይፍንም አመጣብሻለሁ። እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።