ምዕራፍ 1

እግዚአብሔርም ከመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሙሴን ጠርቶ እንዲህ ሲል ተናገረው።
2 ፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራችው። ከእናንተ ማናቸውም ሰው ለእግዚአብሔር መባ ሲያቀርብ መባችሁን ከእንስሳ ወገን ከላሞች ወይም ከበጎች ታቀርባላችሁ።
3 ፤ መባውም የሚቃጠል መሥዋዕት ከላሞች መንጋ ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ተባቱን ያቀርባል፤ በእግዚአብሔር ፊት እንዲሠምር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ፊት ያቀርበዋል።
4 ፤ እጁንም በሚቃጠለው መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፤ ያስተሰርይለትም ዘንድ የሠመረ ይሆንለታል።
5 ፤ በሬውንም በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን ያቀርባሉ፤ ደሙንም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ፊት ባለው በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል።
6 ፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ይገፍፈዋል፥ በየብልቱም ይቈርጠዋል።
7 ፤ የካህኑም የአሮን ልጆች በመሠዊያው ላይ እሳት ያነድዳሉ፥ በእሳቱም ላይ እንጨት ይደረድራሉ፤
8 ፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ የተቈረቱትን ብልቶች ራሱንም ስቡንም በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ይረበርቡታል፤
9 ፤ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ግን በውኃ ያጥባል፤ ካህኑም ሁሉን የሚቃጠል መሥዋዕት የእሳት ቍርባን አድርጎ በእግዚአብሔር ዘንድ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል።
10 ፤ ቍርባኑም የሚቃጠል መሥዋዕት ከበጎች ወይም ከፍየሎች ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ተባቱን ያቀርበዋል።
11 ፤ በመሠዊያውም አጠገብ በሰሜን ወገን በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል።
12 ፤ በየብልቱም ራሱንም ስቡንም ይቈርጠዋል፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ይረበርበዋል፤
13 ፤ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ግን በውኃ ያጥባል። ካህኑም ሁሉን አቅርቦ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ የሚቃጠል መሥዋዕት የእሳት ቍርባን በእግዚአብሔር ዘንድ ጣፋጭ ሽታ ነው።
14 ፤ ለእግዚአብሔርም የሚቀርበው ቍርባን የሚቃጠል መሥዋዕት ከወፎች ቢሆን፥ ቍርባኑን ከዋኖስ ወይም ከርግብ ያቀርባል።
15 ፤ ካህኑም ወደ መሠዊያው ያቀርበዋል፥ ራሱንም ይቈለምመዋል፥ በመሠዊያውም ላይ ያቃጥለዋል። ደሙም በመሠዊያው አጠገብ ይንጠፈጠፋል፤
16 ፤ የሆድ ዕቃውንም ከላባዎች ጋር ለይቶ በመሠዊያው አጠገብ በምሥራቅ ወገን በአመዱ ስፍራ ይጥለዋል፤
17 ፤ በክንፎቹም ይቀድደዋል፥ ነገር ግን አይከፍለውም። ካህኑም በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ያቃጥለዋል፤ የሚቃጠል መሥዋዕት የእሳት ቍርባን በእግዚአብሔር ዘንድ ጣፋጭ ሽታ ነው።