ምዕራፍ 6

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው።
2 ፤ ማናቸውም ሰው ኃጢአትን ቢሠራ፥ እግዚአብሔርንም ቢበድል፥ ያኖረበትን አደራ ወይም ብድር ወስዶ ባልንጀራውን ቢክድ፥ ወይም ቢቀማ፥ ወይም በባልንጀራው ላይ ግፍ ቢያደርግ፥
3 ፤ ወይም የጠፋውን ነገር ቢያገኝ፥ ያንንም ሸሽጎ በሐሰት ቢምል፥ ሰው ከሚያደርጋቸው ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ በአንዲቱ ቢበድል፥
4 ፤ እርሱ ኃጢአትን ሠርቶ በደለኛ ቢሆን፥ በቅሚያ የወሰደውን ወይም በግፍ የተቀበለውን ወይም የተሰጠውን አደራ ወይም ጠፍቶ ያገኘውን፥
5 ፤ ወይም በሐሰት የማለበትን ነገር ይመልስ፤ በሙሉ ይመልስ፥ ከዚያም በላይ አምስተኛውን ክፍል ጨምሮ የበደሉን መሥዋዕት በሚያቀርብበት ቀን ለባለ ገንዘቡ ይስጠው።
6 ፤ ስለ በደል መሥዋዕትም ለእግዚአብሔር ከመንጋው ነውር የሌለበትን አውራ በግ እንደ ግምጋሜህ መጠን ስለ በደል መሥዋዕት ወደ ካህኑ ያምጣ።
7 ፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፥ ስለዚያም ስላደረገው በደል ሁሉ ይቅር ይባላል።
8 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው።
9 ፤ አሮንንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ እዘዛቸው። የሚቃጠለው የመሥዋዕቱ ሕግ ይህ ነው፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ ባለው እንጨት ላይ ሌሊቱን ሁሉ እስኪጸባ ድረስ ይሆናል፤ እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ይነድዳል።
10 ፤ ካህኑም የበፍታ ቀሚስና የበፍታ ሱሪ በሥጋው ላይ ይለብሳል፤ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እሳቱ ከበላው በኋላ አመዱን አንሥቶ በመሠዊያው አጠገብ ያፈስሰዋል።
11 ፤ ልብሱንም ያወልቃል፥ ሌላም ልብስ ይለብሳል፤ አመዱንም ተሸክሞ ከሰፈሩ ንጹሕ ስፍራ ወደ ሆነ ወደ ውጭ ያወጣዋል።
12 ፤ እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ይነድዳል፥ አይጠፋም፤ ካህኑም ማለዳ ማለዳ እንጨት ያቃጥልበታል፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በዚያ ላይ ይረበርባል፤ በዚያም የደኅንነትን መሥዋዕት ስብ ያቃጥላል።
13 ፤ ዘወትር በመሠዊያው ላይ እሳት ይነድዳል፤ አይጠፋም።
14 ፤ የእህሉም ቍርባን ሕግ ይህ ነው፤ የአሮን ልጆች በእግዚአብሔር ፊት በመሠዊያው ፊት ያቀርቡታል።
15 ፤ ካህኑም ከእህሉ ቍርባን መልካሙን ዱቄት ከዘይት ጋር እፍኝ ሙሉ፥ ደግሞም በእህሉ ቍርባን ላይ ያለውን ዕጣን ሁሉ ያነሣል፥ ለእግዚአብሔርም ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል።
16 ፤ ከእርሱም የተረፈውን አሮንና ልጆቹ ይበሉታል፤ ቂጣ ሆኖ በተቀደሰ ስፍራ ይበላል፤ በመገናኛው ድንኳን ዙሪያ ባለው አደባባይ ይበሉታል።
17 ፤ በእርሾ ቦክቶ አይጋገርም። እርሱን ከእሳቱ ቍርባኔ ለእነርሱ እድል ፈንታ እንዲሆን ሰጠሁ፤ እርሱም እንደ ኃጢአትና እንደ በደል መሥዋዕት ቅዱስ ቅዱሳን ነው።
18 ፤ ለእግዚአብሔር ከቀረበ ከእሳት ቍርባን ለዘላለም ለልጅ ልጃችሁ እድል ፈንታቸው እንዲሆን ከአሮን ልጆች ወንዶቹ ሁሉ ይበሉታል። የሚነካቸው ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።
19 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው።
20 ፤ በተቀቡበት ቀን የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል መልካሙን ዱቄት እኵሌታውን በጥዋት፥ እኵሌታውንም በማታ ለዘወትር የእህል ቍርባን አድርገው ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት የአሮንና የልጆቹ ቍርባን ይህ ነው።
21 ፤ ከዘይት ጋር በምጣድ ላይ ይደረጋል፤ ሲለወስ ታገባዋለህ፤ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የእህሉን ቍርባን ቈራርሰህ ታቀርበዋለህ።
22 ፤ ከልጆቹም በአባቱ ፋንታ የተቀባው ካህን ያቀርበዋል። ለዘላለም ሥርዓት እንዲሆን ፈጽሞ ለእግዚአብሔር ይቃጠላል።
23 ፤ ካህኑም የሚያቀርበው የእህል ቍርባን ሁሉ ፈጽሞ ይቃጠላል፤ ከእርሱም አንዳች አይበላም።
24 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው።
25 ፤ አሮንንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ ተናገራቸው። የኃጢአት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የኃጢአቱ መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት ይታረዳል፤ እርሱ ቅዱስ ቅዱሳን ነው።
26 ፤ ለኃጢአት የሚሠዋው ካህን ይበላዋል፤ በመገናኛው ድንኳን ዙሪያ ባለው አደባባይ በተቀደሰ ስፍራ ይበላል።
27 ፤ ሥጋውን የሚነካ ሁሉ ቅዱስ ይሆናል፤ ማናቸው ልብስ ደም ቢረጭበት የተረጨበትን በተቀደሰ ስፍራ ታጥበዋለህ።
28 ፤ የሚቀቀልበትም ሸክላ ይሰበራል፤ በናስም ዕቃ ቢቀቀል ይፈገፈጋል፥ በውኃም ይለቀለቃል።
29 ፤ ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ከእርሱ ይበላል፤ እርሱ ቅዱስ ቅዱሳን ነው።
30 ፤ ነገር ግን በመቅደሱ ውስጥ ለማስተስረያ ይሆን ዘንድ ከደሙ ወደ መገናኛው ድንኳን የሚገባው የኃጢአት መሥዋዕት ሁሉ አይበላም፤ በእሳት ይቃጠላል።