ምዕራፍ 27

እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ማናቸውም ሰው ሰውን ለእግዚአብሔር ሊሰጥ ቢሳል አንተ እንደምትገምተው መጠን ስለ ሰው ዋጋውን ይስጥ።
3 ፤ ለወንድ ከሃያ ዓመት ጀምሮ እስከ ስድሳ ዓመት ድረስ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ግምቱ አምሳ የብር ሰቅል ይሁን።
4 ፤ ሴትም ብትሆን ግምትዋ ሠላሳ ሰቅል ይሁን።
5 ፤ ከአምስት ዓመትም ጀምሮ እስከ ሀያ ዓመት ድረስ ግምቱ ለወንድ ሀያ ሰቅል፥ ለሴትም አሥር ሰቅል ይሁን።
6 ፤ ከአንድ ወርም እስከ አምስት ዓመት ድረስ ለወንድ ግምቱ አምስት የብር ሰቅል፥ ለሴትም ግምትዋ ሦስት የብር ሰቅል ይሁን።
7 ፤ ከስድሳ ዓመትም ጀምሮ ከዚያም በላይ ወንድ ቢሆን ግምቱ አሥራ አምስት ሰቅል፥ ለሴትም አሥር ሰቅል ይሁን።
8 ፤ ለግምቱም የሚከፍለውን ቢያጣ ግን በካህኑ ፊት ይቁም፥ ካህኑም የተሳለውን ሰው ይገምተው፤ ካህኑም የተሳለው ሰው እንደሚችል መጠን ይገምተው።
9 ፤ ለእግዚአብሔርም መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበው እንስሳ ቢሆን፥ ሰው ከእነዚህ ለእግዚአብሔር የሚሰጠው ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።
10 ፤ መልካሙን በክፉ፥ ክፉውንም በመልካም አይለውጥ፤ እንስሳንም በእንስሳ ቢለውጥ እርሱና ልዋጩ የተቀደሱ ይሆናሉ።
11 ፤ እንስሳው ለእግዚአብሔር መሥዋዕት መሆን የማይገባው ርኩስ ቢሆን፥ እንስሳውን በካህኑ ፊት ያኑረው።
12 ፤ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን ካህኑ ይገምተው፤ ካህኑም እነሚገምተው መጠን እንዲሁ ይሁን።
13 ፤ ይቤዠውም ዘንድ ቢወድድ ከግምቱ በላይ አምስተኛ ይጨምር።
14 ፤ ሰውም ለእግዚአብሔር ቅዱስ ይሆን ዘንድ ቤቱን ቢቀድስ፥ ካህኑ መልካም ወይም ክፉ እንደ ሆነ ይገምተዋል፤ ካህኑም እንደሚገምተው መጠን እንዲሁ ይቆማል።
15 ፤ የቀደሰውም ሰው ቤቱን ይቤዠው ዘንድ ቢወድድ ከግምቱ ገንዘብ በላይ አምስተኛ ይጨምር፤ ቤቱም ለእርሱ ይሆናል።
16 ፤ ሰውም ከርስቱ እርሻ ለእግዚአብሔር ቢቀድስ፥ እንደ መዘራቱ መጠን ይገመት፤ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ የሚዘራበት እርሻ አምሳ የብር ሰቅል ይገመታል።
17 ፤ እርሻውንም ከኢዮቤልዩ ዓመት ጀምሮ ቢቀድስ፥ እንደ ግምቱ መጠን ይቆማል።
18 ፤ እርሻውንም ከኢዮቤልዩ ዓመት በኋላ ቢቀድስ፥ ካህኑ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ እንደ ቀሩት ዓመታት ገንዘቡን ይቈጥርለታል፤ ከግምቱም ይጐድላል።
19 ፤ እርሻውንም የቀደሰ ሰው ይቤዠው ዘንድ ቢወድድ፥ ከግምቱ ገንዘብ በላይ አምስተኛ ይጨምር፤ ለእርሱም ይሆናል።
20 ፤ እርሻውንም ባይቤዠው፥ ወይም ለሌላ ሰው ቢሸጥ፥ እንደገና ይቤዠው ዘንድ አይቻለውም።
21 ፤ እርሻው ግን በኢዮቤልዩ ሲወጣ እንደ እርም ለእግዚአብሔር የተቀደሰ እርሻ ይሆናል፤ ርስቱ ለካህኑ ይሆናል።
22 ፤ ከርስቱ እርሻ ያልሆነውን የገዛውን እርሻ ለእግዚአብሔር ቢቀድስ፥
23 ፤ ካህኑ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ የግምቱን ዋጋ ይቈጥርለታል፤ በዚያም ቀን ግምቱን እንደ ተቀደሰ ነገር ለእግዚአብሔር ይሰጣል።
24 ፤ በኢዮቤልዩ ዓመት እርሻው የምድሪቱ ባለ ርስት ወደ ነበረው ወደ ሸጠው ሰው ይመለሳል።
25 ፤ ግምቱም ሁሉ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ይሆናል፤ ሰቅሉ ሀያ አቦሊ ይሆናል።
26 ፤ ለእግዚአብሔር ግን የሚቀርበውን የእንስሳ በኵራት ማንም ይቀድሰው ዘንድ አይቻለውም፤ በሬ ቢሆን ወይም በግ ለእግዚአብሔር ነው።
27 ፤ የረከሰም እንስሳ ቢሆን እንደ ግምቱ ይቤዠው፥ በእርሱም የዋጋውን አምስተኛ ይጨምርበታል፤ ባይቤዠውም እንደ ግምቱ ይሸጣል።
28 ፤ ለእግዚአብሔርም የተለየ እርም የሆነ ነገር ሁሉ፥ ሰው ቢሆን ወይም እንስሳ ወይም የርስቱ እርሻ ቢሆን፥ አይሸጥም፥ አይቤዥም፤ እርም የሆነ ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ቅዱሳን ነው።
29 ፤ ከሰዎችም እርም የሆነ ሁሉ አይቤዥም፤ ፈጽሞ ይገደላል።
30 ፤ የምድርም አሥራት፥ ወይም የምድር ዘር ወይም የዛፍ ፍሬ ቢሆን፥ የእግዚአብሔር ነው፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው።
31 ፤ ሰውም አሥራቱን ሊቤዥ ቢወድድ፥ አምስተኛ ይጨምርበታል።
32 ፤ ከበሬም ሁሉ ከአሥር አንድ፥ ከእረኛውም በትር በታች ከሚያልፍ በግና ፍየል ሁሉ ከአሥር አንድ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል።
33 ፤ መልካም ወይም ክፉ እንዲሆን አይመርምር፥ አይለውጥም፤ ቢለውጠውም እርሱና ልዋጩ የተቀደሱ ይሆናሉ፤ አይቤዠውም።
34 ፤ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ለእስራኤል ልጆች ሙሴን ያዘዘው ትእዛዛት እነዚህ ናቸው።