ምዕራፍ 26

እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ለእናንተ ጣዖት አታድርጉ፥ የተቀረጸም ምስል ወይም ሐውልት አታቁሙ፤ ትሰግዱለትም ዘንድ በምድራችሁ ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ።
2 ፤ ሰንበታቴን ጠብቁ፥ መቅደሴንም ፍሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
3 ፤ በሥርዓቴ ብትሄዱ፥ ትእዛዛቴንም ብትጠብቁ ብታደርጉትም፥
4 ፤ ዝናባችሁን በወቅቱ አዘንባለሁ፥ ምድሪቱም እህልዋን ትሰጣለች፥ የሜዳው ዛፎችም ፍሬአቸውን ይሰጣሉ።
5 ፤ የእህሉም ማበራየት በእናንተ ዘንድ እስከ ወይኑ መቍረጥ ይደርሳል፥ የወይኑም መቍረጥ እስከ እህሉ መዝራት ይደርሳል፤ እስክትጠግቡም ድረስ እንጀራችሁን ትበላላችሁ፥ በምድራችሁም ላይ በጸጥታ ትኖራላችሁ።
6 ፤ በምድራችሁም ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ማንም ሳያስፈራችሁ ትተኛላችሁ፤ ክፉዎችንም አራዊት ከምድራችሁ አጠፋለሁ፥ ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም።
7 ፤ ጠላቶቻችሁንም ታሳድዳላችሁ፥ በፊታችሁም በሰይፍ ይወድቃሉ።
8 ፤ ከእናንተም አምስቱ መቶውን ያሳድዳሉ፥ መቶውም አሥሩን ሺህ ያሳድዳሉ፤ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።
9 ፤ ፊቴም ወደ እናንተ ይሆናል፥ እንድታፈሩም አደርጋችኋለሁ፥ አበዛችሁማለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ።
10 ፤ ብዙ ጊዜ የተቀመጠውንም አሮጌውን እህል ትበላላችሁ፤ ከአዲሱም በፊት አሮጌውን ታወጣላችሁ።
11 ፤ ማደሪያዬንም በእናንተ መካከል አደርጋለሁ፤ ነፍሴም አትጸየፋችሁም።
12 ፤ በመካከላችሁም እሄዳለሁ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፥ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ።
13 ፤ ባሪያዎች እዳትሆኑአቸው ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ የባርነታችሁን ቀንበር ሰብሬአለሁ፤ ቀና ብላችሁ እንድትሄዱ አድርጌአችኋለሁ።
14 ፤ ነገር ግን ባትሰሙኝ፥ እነዚህንም ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥
15 ፤ ሥርዓቴንም ብትንቁ፥ ትእዛዛቴንም ሁሉ እንዳታደርጉ፥ ቃል ኪዳኔንም እንድታፈርሱ ነፍሳችሁ ፍርዴን ብትጸየፍ፥
16 ፤ እኔም እንዲህ አደርግባችኋለሁ፤ ፍርሃትን፥ ክሳትንም፥ ዓይናችሁንም የሚያፈዝዝ፥ ሰውነታችሁንም የሚያማስን ትኩሳት አወርድባችኋለሁ፤ ዘራችሁንም በከንቱ ትዘራላችሁ፥ ጠላቶቻችሁ ይበሉታልና።
17 ፤ ፊቴንም አከብድባችኋለሁ፥ በጠላቶቻችሁም ፊት ትወድቃላችሁ፤ የሚጠሉአችሁም ይገዙአችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ።
18 ፤ እስከዚህም ድረስ ባትሰሙኝ፥ ስለ ኃጢአታችሁ በቅጣታችሁ ላይ ሰባት እጥፍ እጨምራለሁ።
19 ፤ የኃይላችሁንም ትዕቢት እሰብራለሁ፤ ሰማያችሁንም እንደ ብረት፥ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ።
20 ፤ ጕልበታችሁም በከንቱ ያልቃል፤ ምድራችሁም እህልዋን አትሰጥም፥ የምድርም ዛፎች ፍሬአቸውን አይሰጡም።
21 ፤ በእንቢተኝነትም ብትሄዱብኝ ባትሰሙኝም፥ እንደ ኃጢአታችሁ መጠን በመቅሠፍት ላይ ሰባት እጥፍ እጨምራለሁ።
22 ፤ በመካከላችሁም የምድርን አራዊት እሰድዳለሁ፤ ልጆቻችሁንም ይነጥቃሉ፥ እንስሶቻችሁንም ያጠፋሉ፥ እናንተንም ያሳንሳሉ፤ መንገዶቻችሁም በረሃ ይሆናሉ።
23 ፤ እስከዚህም ድረስ ባትቀጡ፥ በእንቢተኝነትም ብትሄዱ፥
24 ፤ እኔ ደግሞ በእንቢተኝነት እሄድባችኋለሁ፤ ስለ ኃጢአታችሁም ሰባት እጥፍ እመታችኋለሁ።
25 ፤ የቃል ኪዳኔንም በቀል ይበቀልባችሁ ዘንድ ሰይፍ አመጣባችኋለሁ፤ ወደ ከተማችሁም ትሰበሰባላችሁ፥ ቸነፈርንም እሰድድባችኋለሁ፤ በጠላትም እጅ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ።
26 ፤ የእህላችሁንም ድጋፍ በሰበርሁ ጊዜ፥ አሥር ሴቶች እንጀራቸውን በአንድ ምጣድ ይጋግራሉ፥ በሚዛንም መዝነው እንጀራችሁን ይመልሱላችኋል፤ በበላችሁም ጊዜ አትጠግቡም።
27 ፤ እስከዚህም ድረስ ባትሰሙኝ፥ በእንቢተኝነትም ብትሄዱብኝ፥
28 ፤ እኔ ደግሞ በቍጣ እሄድባችኋለሁ፤ ስለ ኃጢአታችሁም ሰባት እጥፍ እቀጣችኋለሁ።
29 ፤ የወንዶች ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ፤ የሴቶች ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ።
30 ፤ የኮረብታ መስገጃዎቻችሁንም አፈርሳለሁ፥ የፀሐይ ምስሎቻችሁንም አጠፋለሁ፥ ሬሳችሁንም በጣዖቶቻችሁ ሬሳዎች ላይ እጥላለሁ፤ ነፍሴም ትጸየፋችኋለች።
31 ፤ ከተሞቻችሁንም ባድማ አደርጋለሁ፥ መቅደሶቻችሁንም አፈርሳለሁ፥ መልካሙንም መዓዛችሁን አላሸትትም።
32 ፤ ምድሪቱንም የተፈታች አደርጋለሁ፤ የሚቀመጡባት ጠላቶቻችሁም በእርስዋ የተነሣ ይደነቃሉ።
33 ፤ እናንተንም ከአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፥ ሰይፍንም አስመዝዝባችኋለሁ፤ ምድራችሁም የተፈታች ትሆናለች፥ ከተሞቻችሁም ባድማ ይሆናሉ።
34 ፤ በዚያም በተፈታችበት ዘመን ሁሉ እናንተም በጠላቶቻችሁ ምድር ሳላችሁ፥ ምድሪቱ ሰንበት በማድረግዋ ትደሰታለች፤ በዚያም ጊዜ ምድሪቱ ታርፋለች፥ ሰንበትንም በማድረግዋ ትደሰታለች።
35 ፤ እናንተ ተቀምጣችሁባት በነበረ ጊዜ በሰንበቶቻችሁ አላረፈችም ነበርና በተፈታችበት ዘመን ሁሉ ታርፋለች።
36 ፤ በጠላቶቻቸውም ምድሮች ሳሉ ከእናንተ ተለይተው በቀሩት ላይ በልባቸው ድንጋጤን እሰድድባቸዋለሁ፤ በነፋስም የምትንቀሳቀስ የቅጠል ድምፅ ታሸብራቸዋለች፤ ከሰይፍ እንደሚሸሹ ይሸሻሉ፤ ማንም ሳያሳድዳቸው ይወድቃሉ።
37 ፤ ማንም ሳያሳድዳቸው ከሰይፍ እንዲሸሹ እርስ በርሳቸው ይሰነካከላሉ፤ እናንተም በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም።
38 ፤ በአሕዛብም መካከል ታልቃላችሁ፥ የጠላቶቻችሁም ምድር ትውጣችኋለች።
39 ፤ ከእናንተም ተለይተው የቀሩት በጠላቶቻቸው ምድር ላይ በኃጢአታቸው ይከሳሉ፤ በአባቶቻቸውም ኃጢአት ደግሞ ከእነርሱ ጋር ይከሳሉ።
40 ፤ በእኔም ላይ በእንቢተኝነት ስለ ሄዱብኝ የበደሉኝን በደል፥ ኃጢአታቸውንም፥ የአባቶቻቸውንም ኃጢአት ይናዘዛሉ።
41 ፤ እኔም ደግሞ በእንቢተኝነት ሄድሁባቸው፤ ወደ ጠላቶቻቸውም ምድር አገባኋቸው፤ ነገር ግን በዚያን ጊዜ ያልተገረዘው ልባቸው ቢዋረድ፥ የኃጢአታቸውንም ቅጣት ቢቀበሉ፥
42 ፤ እኔ ለያዕቆብ የማልሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ደግሞ ለይስሐቅና ለአብርሃም የማልሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ምድሪቱንም አስባለሁ።
43 ፤ ምድርም ከእነርሱ መጥፋት የተነሣ ባዶ ትቀራለች፤ እነርሱም ሳይኖሩ በተፈታችበት ዘመን ሰንበት በማድረግዋ ትደሰታለች፤ ፍርዴንም ስለ ናቁ፥ ነፍሳቸውም ሥርዓቴን ስለ ተጸየፈች የኃጢአታቸውን ቅጣት ይሸከማሉ።
44 ፤ ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝኛ እነርሱ በጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ፥ እስካጠፋቸው ድረስ ከእነርሱም ጋር ያለኝን ቃል ኪዳን እስካፈርስ ድረስ አልጥላቸውም አልጸየፋቸውምም።
45 ፤ እኔ አምላካቸው እሆን ዘንድ አሕዛብ እያዩ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸውን የአባቶቻቸውን ቃል ኪዳን ስለ እነርሱ አስባለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
46 ፤ እግዚአብሔርም በእርሱና በእስራኤል ልጆች መካከል በሲና ተራራ ላይ በሙሴ እጅ ያደረጋቸው ሥርዓቶችና ፍርዶች ሕግጋትም እነዚህ ናቸው።