ምዕራፍ 17

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ለአሮንና ለልጆቹ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገር። እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፥ እንዲህም አለ።
3 ፤ ከእስራኤል ቤት ማናቸውም ሰው በሬ ወይም በግ ወይም ፍየል ቢያርድ፥ በሰፈሩ ውስጥ ወይም ከሰፈሩ ውጭ ቢያርደው፥
4 ፤ በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት ለእግዚአብሔር ቍርባን ያቀርብ ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ ደሙ በዚያ ሰው ላይ ይቈጠርበታል፤ ደም አፍስሶአል፤ ያም ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።
5 ፤ ስለዚህ የእስራኤል ልጆች በሜዳ የሚያርዱትን መሥዋዕታቸውን ወደ እግዚአብሔር ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ያመጡታል፤ ወደ ካህኑም አምጥተው ለእግዚአብሔር ለደኅንነት መሥዋዕት ይሠዉታል።
6 ፤ ካህኑም በመገኛኛው ድንኳን ደጃፍ ባለው በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ደሙን ይረጨዋል፥ ስቡንም ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ያቃጥለዋል።
7 ፤ መሥዋዕታቸውንም ደግሞ ተከትለው ላመነዘሩባቸው ለሰይጣናት አይሠዉ። ይህ ለእነርሱ ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም ሥርዓት ይሁን።
8 ፤ ለእነርሱም እንዲህ በላቸው። ከእስራኤል ቤት በመካከላቸውም ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት ቢያቀርብ፥
9 ፤ ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።
10 ፤ ከእስራኤልም ልጆች ወይም በመካከላቸው ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው ደም ቢበላ፥ ደም በሚበላው በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብድበታለሁ፥ ያንንም ሰው ከሕዝቡ ለይቼ አጠፋዋለሁ።
11 ፤ የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፤ ደሙም ከሕይወቱ የተነሣ ያስተሰርያልና በመሠዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ እኔ ለእናንተ ሰጠሁት።
12 ፤ ስለዚህ የእስራኤልን ልጆች። ከእናንተ ማንም ደምን አይበላም፥ በመካከላችሁም ከሚኖሩ እንግዶች ማንም ደምን አይበላም አልሁ።
13 ፤ ከእስራኤልም ልጆች በመካከላቸውም ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው የሚበላ እንስሳ ወይም ወፍ እያደነ ቢይዝ፥ ደሙን ያፈስሳል በአፈርም ይከድነዋል።
14 ፤ የሥጋ ሁሉ ሕይወትና ደሙ አንድ ነውና ስለዚህ ለእስራኤል ልጆች። የሥጋ ሁሉ ሕይወት ደሙ ነውና የሥጋውን ሁሉ ደም አትብሉ፤ የሚበላውም ሁሉ ተለይቶ ይጥፋ አልኋቸው።
15 ፤ የሞተውን ወይም አውሬ የሰበረውን የሚበላ ሰው ሁሉ፥ የአገር ልጅ ወይም እንግዳ ቢሆን፥ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል።
16 ፤ ልብሱንና ገላውን ባያጥብ ግን ኃጢአቱን ይሸከማል።