ምዕራፍ 4

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው።
2 ፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ማናቸውም ሰው ሳያውቅ ኃጢአት ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም። አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፍ፥
3 ፤ የተቀባውም ካህን በሕዝቡ ላይ በደል እንዲቈጠርባቸው ኃጢአት ቢሠራ፥ ስለ ሠራው ስለ ኃጢአቱ ነውር የሌለበት ወይፈን ለእግዚአብሔር ለኃጢአት መሥዋዕት ያቀርበዋል።
4 ፤ ወይፈኑንም ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያመጣዋል፤ እጁንም በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭነዋል፥ ወይፈኑንም በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል።
5 ፤ የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ያመጣዋል፤
6 ፤ ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመቅደሱ መጋረጃ ፊት ደሙን ሰባት ጊዜ ይረጨዋል።
7 ፤ ካህኑም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ያለው ጣፋጭ ዕጣን በሚታጠንበት መሠዊያ ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ የተረፈውንም የወይፈኑን ደም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ባለው ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል።
8 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት ከሚታረደው ወይፈን ስብን ሁሉ ይወስዳል፤ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥
9 ፤ ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር፥
10 ፤ ለደኅንነት መሥዋዕት ከታረደው ወይፈን እንደ ተወሰደው ይወስዳል። ካህኑም ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ላይ ያቃጥለዋል።
11 ፤ የወይፈኑን ቁርበት፥ ሥጋውንም ሁሉ፥ ራሱንም፥ እግሮቹንም፥ ሆድ ዕቃውንም፥
12 ፤ ፈርሱንም፥ ወይፈኑን ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ አመድ ወደሚፈስስበት ወደ ንጹሕ ስፍራ ይወስደዋል፥ በእንጨትም ላይ በእሳት ያቃጥለዋል፤ አመድ በሚፈስስበት ስፍራ ይቃጠላል።
13 ፤ የእስራኤል ማኅበር ሁሉ ቢስቱ፥ ነገሩም ከጉባኤው ፊት ቢሸሸግ፥ እግዚአብሔርም። አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፉ፥
14 ፤ እንዲህም ቢበድሉ፥ የሠሩት ኃጢአት ሲታወቅ ጉባኤው ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ወይፈንን ያቀርባሉ፤ ወደ መገናኛውም ድንኳን ፊት ያመጡታል።
15 ፤ የጉባኤውም ሽማግሌዎች እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ይጭናሉ፤ ወይፈኑም በእግዚአብሔር ፊት ይታረዳል።
16 ፤ የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወደ መገናኛው ድንኳን ያመጣል፤
17 ፤ ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመጋረጃው ፊት ለፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል።
18 ፤ በመገናኛውም ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ባለው በዕጣን መሠዊያው ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ ደሙንም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ባለው ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል።
19 ፤ ስቡንም ሁሉ ከእርሱ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል።
20 ፤ እንዲህም በወይፈኑ ያደርጋል፤ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት በታረደው ወይፈን እንዳደረገ እንዲሁ በዚህ ያደርጋል፤ ካህኑም ስለ እነርሱ ያስተሰርያል፥ እነርሱም ይቅር ይባላሉ።
21 ፤ ወይፈኑንም ከሰፈሩ ወደ ውጭ ይወስደዋል፥ የፊተኛውንም ወይፈን እንዳቃጠለ ያቃጥለዋል፤ ይህ የማኅበሩ የኃጢአት መሥዋዕት ነው።
22 ፤ አንድ መኰንንም ኃጢአትን ሲሠሩ፥ ሳያውቅም እግዚአብሔር አምላኩ። አትሥራ ያለውን ትእዛዝ ሲተላለፍ፥ እንዲህም ሲበድል፥
23 ፤ የሠራው ኃጢአት ቢታወቅ፥ ነውር የሌለበትን ተባት ፍየል ለቍርባኑ ያቀርበዋል፤
24 ፤ በፍየሉም ራስ ላይ እጁን ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል፤ እርሱ የኃጢአት መሥዋዕት ነው።
25 ፤ ካህኑም ከኃጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ያደርገዋል፤ የተረፈውንም ደም ለሚቃጠል መሥዋዕት ከሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል።
26 ፤ ስቡንም ሁሉ እንደ ደኅንነት መሥዋዕት ስብ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ካህኑም ኃጢአቱን ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል።
27 ፤ ከአገሩ ሕዝብም አንድ ሰው ኃጢአትን ሳያውቅ ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም። አትሥራ ያለውን ትእዛዝ ቢተላለፍ፥ ቢበድልም፥
28 ፤ ለእርሱም የሠራው ኃጢአት ቢታወቀው፥ ስለ ሠራው ኃጢአት ነውር የሌለባትን እንስት ፍየል ለቍርባኑ ያመጣል።
29 ፤ እጁንም በኃጢአት መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የኃጢአትን መስዋዕት ያርዳል።
30 ፤ ካህኑም ከደምዋ በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፥ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ያፈስሰዋል።
31 ፤ ስቡም ሁሉ ከደኅንነት መሥዋዕት ላይ እንደሚወሰድ፥ ስብዋን ሁሉ ይወስዳል፤ ካህኑም ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ ካህኑም ስለ እርሱ ያስተሰርያል፥ እርሱም ይቅር ይባላል።
32 ፤ ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት የበግ ጠቦት ቢያቀርብ፥ ነውር የሌለባትን እንስት ያመጣል።
33 ፤ እጁንም በኃጢአት መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፥ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ ለኃጢአት መሥዋዕት ያርዳታል።
34 ፤ ካህኑም ከኃጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፥ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ያፈስሰዋል።
35 ፤ ስቡ ሁሉ ለደኅንነት መሥዋዕት ከታረደው ጠቦት ላይ እንደሚወሰድ ስብዋን ይወስዳል፤ ካህኑም ለእግዚአብሔር በእሳት በተቃጠለው ቍርባን ላይ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ካህኑም ስለ ሠራው ኃጢአት ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል።