ምዕራፍ 18

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
3 ፤ እንደ ተቀመጣችሁባት እንደ ግብፅ ምድር ሥራ አትሥሩ፤ እኔም ወደ እርስዋ እንደማገባችሁ እንደ ከነዓን ምድር ሥራ አትሥሩ፤ በሥርዓታቸውም አትሂዱ።
4 ፤ ፍርዴን አድርጉ፥ በእርስዋም ትሄዱ ዘንድ ሥርዓቴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
5 ፤ የሚሠራቸው ሰው በእነርሱ በሕይወት ይኖራልና ሥርዓቴንና ፍርዴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
6 ፤ ከእናንተም ማንም ሰው ኃፍረተ ሥጋውን ይገልጥ ዘንድ ወደ ዘመዱ ሁሉ አይቅረብ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
7 ፤ የአባትህን ኃፍረተ ሥጋና የእናትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ እናትህ ናት፤ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ።
8 ፤ የአባትህን ሚስት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህን ኃፍረተ ሥጋ ነው።
9 ፤ የእኅትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህ ልጅ ወይም የእናትህ ልጅ፥ በቤት ወይም በውጭ የተወለደች ብትሆን፥ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ።
10 ፤ የወንድ ልጅህን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋዋን ወይም የሴት ልጅህን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአንተ ኃፍረተ ሥጋ ነውና።
11 ፤ ከአባትህ የተወለደችውን የአባትህን ሚስት ልጅ ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ እህትህ ናት፤ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ።
12 ፤ የአባትህን እኅት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህ ዘመድ ናት።
13 ፤ የእናትህን እኅት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የእናትህ ዘመድ ናት።
14 ፤ የአባትህን ወንድም ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፥ ወደ ሚስቱም አትቅረብ፤ የአጎትህ ሚስት ናት።
15 ፤ የምራትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የልጅህ ሚስት ናት፤ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ።
16 ፤ የወንድምህን ሚስት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የወንድምህ ኃፍረተ ሥጋ ነው።
17 ፤ የሴትንና የሴት ልጅዋን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የወንድ ልጅዋን ሴት ልጅ ወይም የሴት ልጅዋን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋዋን ትግለጥ ዘንድ አታግባ፤ ዘመዶች ናቸው፤ ዝሙት ነው።
18 ፤ ሚስትህ በሕይወት ሳለች እኅትዋ ጣውንትዋ እንዳትሆን፥ ኃፍረተ ሥጋዋን ትገልጥ ዘንድ ከእርስዋ ጋር እኅትዋን አታግባ።
19 ፤ እርስዋም በመርገምዋ ርኵሰት ሳለች ኃፍረተ ሥጋዋን ትገልጥ ዘንድ ወደ ሴት አትቅረብ።
20 ፤ እንዳትረክስባትም ከባልንጀራህ ሚስት ጋር አትተኛ።
21 ፤ ከዘርህም ለሞሎክ በእሳት አሳልፈህ አትስጥ፥ የአምላክህንም ስም አታርክስ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
22 ፤ ከሴትም ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ፤ ጸያፍ ነገር ነውና።
23 ፤ እንዳትረክስባትም ከእንሰሳ ጋር አትተኛ፤ ሴት ከእርሱ ጋር ትተኛ ዘንድ በእንስሳ ፊት አትቁም፤ የተጠላ ነገር ነውና።
24 ፤ በእነዚህ ሁሉ ከፊታችሁ የማሳድዳቸው አሕዛብ ረክሰዋልና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ አትርከሱ።
25 ፤ ምድሪቱም ረከሰች፤ ስለዚህ ኃጢአትዋን በእርስዋ ላይ እመልሳለሁ፥ ምድሪቱም የሚኖሩባትን ሰዎች ትተፋለች።
26 ፤ ሥርዓቴንና ፍርዴን ጠብቁ፤ እናንተም የአገሩ ልጆች በእናንተም መካከል የሚኖሩት እንግዶች ከዚህ ርኵሰት ምንም አትሥሩ፤
27 ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩ የአገሩ ልጆች ይህን ርኵሰት ሁሉ ሠርተዋልና፥ ምድሪቱም ረክሳለችና፤
28 ፤ ባረከሳችኋት ጊዜ ምድሪቱ ከእናንተ በፊት የነበረውን ሕዝብ እንደ ተፋች እናንተን እንዳትተፋችሁ።
29 ፤ ከዚህ ርኵሰት ሁሉ ማናቸውን የሚያደርግ ያ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋልና።
30 ፤ ስለዚህ ከእናንተ በፊት የነበሩ ሰዎች የሠሩትን ጸያፍ የሆነውን ወግ ሁሉ እንዳትሠሩ፥ በእርሱም እንዳትረክሱ ሥርዓቴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።