ምዕራፍ 13

እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
2 ፤ ማናቸውም ሰው በሥጋው ቁርበት ላይ እባጭ ወይም ብጕር ወይም ቋቁቻ ቢታይ፥ በሥጋው ቁርበት እንደ ለምጽ ደዌ ቢመስል፥ ወደ ካህኑ ወደ አሮን ወይም ከካህናቱ ልጆቹ ወደ አንዱ ያምጡት።
3 ፤ ካህኑም በሥጋው ቁርበት ያለውን ደዌ ያያል፤ ጠጕሩም ተለውጦ ቢነጣ ደዌውም ወደ ሥጋው ቁርበት ቢጠልቅ፥ እርሱ የለምጽ ደዌ ነው፤ ካህኑም አይቶ። ርኩስ ነው ይበለው።
4 ፤ ቋቁቻውም በሥጋው ቁርበት ላይ ቢነጣ፥ ከቁርበቱም የጠለቀ ባይመስል፥ ጠጕሩም ባይነጣ፥ ካህኑ የታመመውን ሰው ሰባት ቀን ይዘጋበታል።
5 ፤ በሰባተኛውም ቀን ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው በዓይኑ ፊት እንደ ነበረ ቢሆን፥ በቁርበቱም ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ ሰባት ቀን ደግሞ ይዘጋበታል።
6 ፤ ደግሞ በሰባተኛው ቀን ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢከስም፥ ደዌውም በቁርበቱ ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ። ንጹሕ ነው ይለዋል፤ እከክ ነው፤ ልብሱንም አጥቦ ንጹሕ ይሆናል።
7 ፤ ስለ መንጻቱ በካህኑ ዘንድ ከታየ በኋላ እከኩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ፥ እንደ ገና ሊታይ ወደ ካህኑ ይቀርባል።
8 ፤ ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ እከኩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ ለምጽ ነው።
9 ፤ የለምጽ ደዌ በሰው ውስጥ ቢሆን እርሱን ወደ ካህኑ ያመጡለታል።
10 ፤ ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ በቁርበቱ ላይ ነጭ እባጭ ቢሆን፥ ጠጕሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ሥጋውም በእባጩ ውስጥ ቢያዥ፥
11 ፤ እርሱ በሥጋው ቁርበት ላይ አሮጌ ለምጽ ነው፥ ካህኑም። ርኩስ ነው ይለዋል፤ እርሱ ርኩስ ነውና አይዘጋበትም።
12 ፤ ለምጹም በቁርበቱ ላይ ሰፍቶ ቢወጣ፥ ለምጹም የታመመውን ሰው ቁርበቱን ሁሉ ከራሱ እስከ እግሮቹ ድረስ እንደ ከደነው ለካህኑ ቢመስለው፥ ካህኑ ያያል፤
13 ፤ እነሆም፥ ለምጹ ሥጋውን ሁሉ ቢከድን የታመመውን ሰው። ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ሥጋው ሁሉ ፈጽሞ ተለውጦ ነጭ ሆኖአል፤ ንጹሕ ነው።
14 ፤ የሚያዠው ሥጋ ግን ሲታይበት ርኩስ ይሆናል።
15 ፤ ካህኑም የሚያዠውን ሥጋ አይቶ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ የሚያዠው ሥጋ ለምጽ ነውና ርኩስ ነው።
16 ፤ የሚያዠውም ሥጋ ተለውጦ ቢነጣ እንደ ገና ወደ ካህኑ ይመጣል።
17 ፤ ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢነጣ ካህኑ የታመመውን። ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ንጹሕ ነው።
18 ፤ በሥጋውም ቁርበት ላይ ቍስል ቢሆንና ቢሽር፥
19 ፤ በቍስሉም ስፍራ ነጭ እባጭ ወይም ቀላ ያለ ቋቁቻ ቢወጣ፥ በካህኑ ዘንድ ይታያል።
20 ፤ ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ ወደ ቁርበቱ ውስጥ ጠልቆ ቢታይ፥ ጠጕሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ካህኑ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው፤ ከቍስሉ ውስጥ ወጥቶአል።
21 ፤ ካህኑም ቢያየው፥ ነጭም ጠጕር ባይኖርበት፥ ወደ ቁርበቱም ውስጥ ባይጠልቅ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይዘጋበታል።
22 ፤ በቁርበቱም ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ ደዌ ነው።
23 ፤ ቋቁቻው ግን በስፍራው ቢቆም ባይሰፋም፥ የቍስል ጠባሳ ነው፤ ካህኑም። ንጹሕ ነው ይለዋል።
24 ፤ በሥጋውም ቁርበት የእሳት ትኵሳት ቢኖርበት፥ በተቃጠለውም ስፍራ ነጭ ወይም ቀላ ያለ ቋቁቻ ቢታይ፥
25 ፤ ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ በቋቁቻው ጠጕሩ ተለውጦ ቢነጣ፥ ወደ ቁርበቱም ውስጥ ቢጠልቅ፥ ለምጽ ነው፤ ከተቃጠለውም ስፍራ ወጥቶአል፤ ካህኑም። ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው።
26 ፤ ካህኑም ቢያየው፥ በቋቁቻውም ነጭ ጠጕር ባይኖር፥ ወደ ቁርበቱም ባይጠልቅ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይዘጋበታል።
27 ፤ ካህኑም በሰባተኛው ቀን ያየዋል፤ በቁርበቱም ላይ ቢሰፋ ካህኑ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው።
28 ፤ ቋቁቻውም በስፍራው ላይ ቢቆም፥ በቁርበቱም ላይ ባይሰፋ ነገር ግን ቢከስም፥ የትኵሳት እባጭ ነው፤ የትኵሳትም ጠባሳ ነውና ካህኑ። ንጹሕ ነው ይለዋል።
29 ፤ ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በራሱ ወይም በአገጩ ደዌ ቢኖርበት፥
30 ፤ ካህኑ ደዌውን ያያል፤ እነሆም፥ ወደ ቁርበቱ ቢጠልቅ፥ በውስጡም ቀጭን ብጫ ጠጕር ቢኖርበት፥ ካህኑ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ ቈረቈር ነው፤ የራስ ወይም የአገጭ ለምጽ ነው።
31 ፤ ካህኑም የቈረቈሩን ደዌ ቢያይ፥ ወደ ቁርበቱም ባይጠልቅ፥ ጥቁርም ጠጕር ባይኖርበት፥ ካህኑ የቈረቈር ደዌ ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ይዘጋበታል።
32 ፤ ካህኑም በሰባተኛው ቀን ደዌውን ያያል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ ባይሰፋ፥ በውስጡም ብጫ ጠጕር ባይኖር፥ የቈረቈሩም መልክ ወደ ቁርበቱ ባይጠልቅ፥ ይላጫል፥
33 ፤ ቈረቈሩ ግን አይላጭም፤ ካህኑም ቈረቈር ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ደግሞ ይዘጋበታል።
34 ፤ ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቈረቈሩን ያያል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ በቁርበቱ ላይ ባይሰፋ፥ መልኩም ወደ ቁርበቱ ባይጠልቅ፥ ካህኑ። ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ልብሱን አጥቦ ንጹሕ ይሆናል።
35 ፤ ከነጻ በኋላ ግን ቈረቈሩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ ያየዋል፤
36 ፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ ካህኑ ብጫውን ጠጕር አይፈልግም፤ ርኩስ ነው።
37 ፤ ቈረቈሩ ግን በዓይኑ ፊት እንደ ነበረ ቢሆን፥ ጥቁርም ጠጕር ቢበቅልበት፥ ቈረቈሩ ሽሮአል እርሱም ንጹሕ ነው፤ ካህኑም። ንጹሕ ነው ይለዋል።
38 ፤ ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በሥጋው ቁርበት ላይ ነጭ ቋቁቻ ቢኖርበት፥
39 ፤ ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ በሥጋቸው ቁርበት ላይ ያለው ቋቁቻ ፈገግ ቢል አጓጐት ነው፤ ከቁርበቱ ውስጥ ወጥቶአል፤ ንጹሕ ነው።
40 ፤ የሰውም ጠጕር ከራሱ ቢመለጥ እርሱ ቡሀ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው።
41 ፤ ጠጕሩም ከግምባሩ ቢመለጥ እርሱ ራሰ በራ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው።
42 ፤ በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ነጭ ወይም ቀላ ያለ ደዌ ቢኖርበት፥ እርሱ ከቡሀነቱ ወይም ከራሰ በራነቱ የወጣ ለምጽ ነው።
43 ፤ ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ የደዌው እብጠት፥ በሥጋው ቁርበት ላይ የሆነ ለምጽ መስሎ፥ በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ነጭ ወይም ቀላ ያለ ቢሆን፥
44 ፤ ለምጻም ሰው ነው፤ ርኩስ ነው፤ ካህኑ። በእርግጥ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ደዌው በራሱ ነው።
45 ፤ የለምጽ ደዌ ያለበት ሰው ልብሱ የተቀደደ ይሁን፥ ራሱም የተገለጠ ይሁን፥ ከንፈሩንም ይሸፍን፤ ርኩስ ርኩስ ነኝ ይበል።
46 ፤ ደዌው ባለበት ዘመን ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ እርሱ ርኩስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጣል፤ መኖሪያውም ከሰፈር በውጭ ይሆናል።
47 ፤ የለምጽም ደዌ በልብስ ላይ ቢሆን፥ ልብሱም የበግ ጠጕር ወይም በፍታ ቢሆን፥
48 ፤ በድሩ ወይም በማጉ ላይ ቢሆን፥ በፍታ ወይም የበግ ጠጕር ቢሆን፥ አጐዛ ወይም ከአጐዛ የሚደረግ ነገር ቢሆን፥
49 ፤ ደዌው በልብሱ ወይም በአጐዛው ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከአጐዛው በሚደረገው ነገር አረንጓዴ ወይም ቀይ ቢሆን፥ የለምጽ ደዌ ነው፤ ለካህኑ ይታያል።
50 ፤ ካህኑም ደዌውን አይቶ ደዌው ያለበትን ነገር ሰባት ቀን ይዘጋበታል።
51 ፤ በሰባተኛውም ቀን ደዌውን ያያል፤ ደዌውም በልብስ ላይ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም በአጐዛው ወይም ከአጐዛው በሚደረግ ነገር ቢሰፋ፥ ደዌው እየፋገ የሚሄድ ለምጽ ነው፤ ርኩስ ነው።
52 ፤ ልብሱን ያቃጥል፤ ድሩ ወይም ማጉ የበግ ጠጕር ወይም በፍታ ቢሆን ወይም ከአጐዛው የተደረገ ቢሆን፥ ደዌ ያለበት ሁሉ፥ እየፋገ የሚሄድ ለምጽ ነውና በእሳት ይቃጠል።
53 ፤ ካህኑ ቢያይ፥ እነሆም፥ ደዌው በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከአጐዛ በተደረገ ነገር ቢሆን በልብሱ ላይ ባይሰፋ፥
54 ፤ ካህኑ ደዌ ያለበቱ ነገር እንዲታጠብ ይዘዝ፤ ሌላም ሰባት ቀን ይዘጋበታል።
55 ፤ ደዌውም ከታጠበ በኋላ ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው መልኩን ባይለውጥ ባይሰፋም፥ ርኩስ ነው፤ በእሳት አቃጥለው፤ ምልክቱ በውስጥ ወይም በውጭ ቢሆን እየፋገ የሚሄድ ደዌ ነው።
56 ፤ ካህኑም ቢያይ፥ እነሆም፥ ደዌው ከታጠበ በኋላ ቢከስም፥ ከልብሱ ወይም ከአጐዛው ወይም ከድሩ ወይም ከማጉ ይቅደደው።
57 ፤ በልብሱም ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከአጐዛው በተደረገ ነገር ላይ ደግሞ ቢታይ፥ የወጣ ለምጽ ነው፤ ደዌው ያለበትን ነገር አቃጥለው።
58 ፤ አንተም ካጠብኸው ልብስ ወይም ከድሩ ወይም ከማጉ ወይም ከአጐዛው ከተደረገው ነገር ላይ ደዌው ቢጠፋ፥ ሁለተኛ ጊዜ ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል።
59 ፤ በበግ ጠጕር ልብስ ወይም በበፍታ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከአጐዛ በተደረገ ነገር ላይ ቢሆን፥ ንጹሕ ወይም ርኩስ ያሰኝ ዘንድ የለምጽ ደዌ ሕግ ይህ ነው።