ምዕራፍ 24

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ መብራቱን ሁልጊዜ እንድታበራበት ለመብራት ጥሩ ተወቅጦ የተጠለለ የወይራ ዘይት ያመጡልህ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው።
3 ፤ በምስክሩ መጋረጃ ውጭ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አሮን ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ ያሰናዳው፤ ለዘላለም ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ይሁን።
4 ፤ በእግዚአብሔር ፊት በጥሩ መቅረዝ ላይ መብራቶቹን ሁልጊዜ ያሰናዳቸው።
5 ፤ መልካሙንም ዱቄት ወስደህ አሥራ ሁለት ኅብስት ጋግር፤ በአንድ ኅብስት ውስጥ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ ይሁን።
6 ፤ እነዚህንም ስድስት ስድስቱን በሁለት ተርታ አድርገህ በእግዚአብሔር ፊት በጥሩ ገበታ ላይ አኑራቸው።
7 ፤ ለእግዚአብሔርም ለእሳት ቍርባን በእንጀራው ላይ ለመታሰቢያ ይሆን ዘንድ በሁለቱ ተርታ ላይ ጥሩ ዕጣን አድርግ።
8 ፤ በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ በሰንበት ቀን ሁሉ በተርታ ያድርገው፤ በእስራኤል ልጆች ዘንድ የዘላለም ቃል ኪዳን ነው።
9 ፤ ለአሮንና ለልጆቹም ይሁን፤ በእሳት ከተደረገው ከእግዚአብሔር ቍርባን በዘላለም ሥርዓት ለእርሱ ቅዱስ ቅዱሳን ነውና በተቀደሰ ስፍራ ይብሉት።
10 ፤ አባቱ ግብፃዊ የነበረ የእስራኤላዊት ልጅ በእስራኤል ልጆች መካከል ወጣ፤ የእስራኤላዊቱ ልጅና አንድ እስራኤላዊ በሰፈር ውስጥ ተጣሉ፤
11 ፤ የእስራኤላዊቱም ልጅ የእግዚአብሔርን ስም ሰደበ፥ አቃለለውም፤ ወደ ሙሴም አመጡት። እናቱም ከዳን ነገድ የደብራይ ልጅ ነበረች፥ ስምዋም ሰሎሚት ነበረ።
12 ፤ ከእግዚአብሔርም አፍ ስለ እርሱ ፍርድ እስኪወጣላቸው ድረስ በግዞት አኖሩት።
13 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
14 ፤ ተሳዳቢውን ከስፈሩ ወደ ውጭ አውጣው፤ የሰሙትም ሁሉ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጫኑበት፤ ማኅበሩም ሁሉ ይውገረው።
15 ፤ ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ትነግራለህ። ማናቸውም ሰው አምላኩን ቢሰድብ ኃጢአቱን ይሸከማል።
16 ፤ የእግዚአብሔርንም ስም የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል፤ ማኅበሩም ሁሉ ይውገሩት፤ መጻተኛ ወይም የአገር ልጅ ቢሆን፥ የእግዚአብሔርን ስም በሰደበ ጊዜ ይገደል።
17 ፤ ሰውንም እስኪሞት ድረስ የሚመታ ፈጽሞ ይገደል።
18 ፤ እንስሳንም እስኪሞት ድረስ የሚመታ ሕይወት በሕይወት ፋንታ ካሣውን ይክፈል።
19 ፤ ሰውም ባልንጀራውን ቢጐዳ፥ እርሱ እንዳደረገ እንዲሁ ይደረግበት።
20 ፤ ስብራት በስብራት ፋንታ፥ ዓይን በዓይን ፋንታ፥ ጥርስ በጥርስ ፋንታ፥ ሰውን እንደ ጐዳ እንዲሁ ይደረግበት።
21 ፤ እንስሳውንም የሚገድል ካሣ ይተካ፤ ሰውንም የሚገድል ይገደል።
22 ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ለመጻተኛና ለአገር ልጅ አንድ ዓይነት ሕግ ይሁንላችሁ።
23 ፤ ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ተናገራቸው፤ ተሳዳቢውንም ከሰፈሩ ወደ ውጭ አወጡት፥ በድንጋይም ወገሩት። የእስራኤልም ልጆች እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።