ምዕራፍ 25

እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ ምድሪቱ ለእግዚአብሔር ሰንበት ታድርግ።
3 ፤ ስድስት ዓመት እርሻህን ዝራ፥ ስድስት ዓመትም ወይንህን ቍረጥ ፍሬዋንም አግባ።
4 ፤ በሰባተኛው ዓመት ግን ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት፥ ለእግዚአብሔር ሰንበት፥ ትሁን፤ እርሻህን አትዝራ፥ ወይንህንም አትቍረጥ።
5 ፤ የምድራችሁን የገቦ አትጨደው፥ ያልተቈረጠውንም የወይንህን ፍሬ አታከማች፤ ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ዓመት ይሁን።
6 ፤ የምድርም ሰንበት ለአንተ፥ ለወንድ ባሪያህም፥ ለሴት ባሪያህም፥ ለምንደኛውም፥ ከአንተ ጋር ለሚኖር ለመጻተኛም ምግብ ይሁን።
7 ፤ ለእንስሶችህም፥ በምድርህም ላሉት አራዊት ፍሬዋ ሁሉ መኖ ይሁን።
8 ፤ ሰባት ጊዜ ሰባት አድርገህ የዓመታትን ሰንበት ሰባት ቍጠር፤ የሰባት ዓመታትም ሰንበት ዘመን አርባ ዘጠኝ ዓመት ትቈጥራለህ።
9 ፤ ከዚያም በኋላ በሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን በቀንደ መለከት ታውጃለህ፤ በማስተስረያ ቀን በምድራችሁ ሁሉ በቀንደ መለከት ታውጃላችሁ።
10 ፤ አምሳኛውንም ዓመት ትቀድሳላችሁ፥ በምድሪቱም ለሚኖሩባት ሁሉ ነጻነትን ታውጃላችሁ፤ እርሱ ለእናንተ ኢዮቤልዩ ነው፤ ሰው ሁሉ ወደ ርስቱና ወደ ወገኑ ይመለስ።
11 ፤ ያ አምሳኛው ዓመት ለእናንተ ኢዮቤልዩ ይሆናል፤ በእርሱም አትዝሩ፥ የገቦውንም አትጨዱ፥ የወይኑንም ፍሬ አታከማቹ።
12 ፤ ኢዮቤልዩ ነውና የተቀደሰ ይሁንላችሁ፤ በሜዳ ላይ የበቀለውን ብሉ።
13 ፤ በዚች በኢዮቤልዩ ዓመት ሰው ሁሉ ወደ ርስቱ ይመለሳል።
14 ፤ ለባልንጀራህም አንዳች ብትሸጥለት፥ ወይም ከባልንጀራህ እጅ ብትገዛ፥ ሰው ባልንጀራውን አያታልል።
15 ፤ ከኢዮቤልዩ በኋላ እንደ ዓመታቱ ቍጥር ከባልንጀራህ ትገዛለህ፤ እርሱም እንደ መከሩ ዓመታት ቍጥር ይሸጥልሃል።
16 ፤ እንደ ዓመታቱ ብዛት ዋጋውን ታበዛለህ፥ እንደ ዓመታቱም ማነስ ዋጋውን ታሳንሳለህ፤ እንደ መከሩ ቍጥር ይሸጥልሃል።
17 ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሰው ባልንጀራውን አያታልል፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ።
18 ፤ ሥርዓቴንም አድርጉ፥ ፍርዶቼንም ጠብቁ አድርጉትም፤ በምድሪቱም ውስጥ በጸጥታ ትኖራላችሁ።
19 ፤ ምድሪቱም ፍሬዋን ትሰጣለች፥ እስክትጠግቡም ድረስ ትበላላችሁ፤ በእርስዋም ውስጥ በጸጥታ ትኖራላችሁ።
20 ፤ እናንተም። ካልዘራን፥ እህላችንንም ካላከማቸን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን? ብትሉ፥
21 ፤ እኔ በስድስተኛው ዓመት በረከቴን በላያችሁ አዝዛለሁ፤ ምድሪቱም የሦስት ዓመት ፍሬ ታፈራለች።
22 ፤ በስምንተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ፥ ከአሮጌውም እህል ትበላላችሁ፤ ፍሬዋ እስኪገባ፥ እስከ ዘጠነኛው ዓመት ድረስ፥ ከአሮጌው እህል ትበላላችሁ።
23 ፤ ምድርም ለእኔ ናትና፥ እናንተም ከእኔ ጋር እንግዶችና መጻተኞች ናችሁና ምድርን ለዘላለም አትሽጡ።
24 ፤ በርስታችሁም ምድር ሁሉ መቤዠትን ለምድሪቱ አድርጉ።
25 ፤ ወንድምህም ቢደኸይ ከርስቱም ቢሸጥ፥ ለእርሱ የቀረበ ዘመዱ መጥቶ ወንድሙ የሸጠውን ይቤዠዋል።
26 ፤ የሚቤዠውም ሰው ቢያጣ፥ እርሱም እጁ ቢረጥብ፥ ለመቤዠትም የሚበቃ ቢያገኝ፥
27 ፤ የሽያጩን ዘመን ቈጥሮ የቀረውን ወደ ገዛው ሰው ይመልስ፤ እርሱም ወደ ርስቱ ይመለስ።
28 ፤ ለራሱም ዕዳውን መክፈል ባይችል፥ ሽያጩ በገዛው ሰው እጅ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ይቀመጥ፤ በኢዮቤልዩም ዓመት ይውጣ፥ እርሱም ወደ ርስቱ ይመለስ።
29 ፤ ሰውም ቅጥር ባለበት ከተማ መኖሪያ ቤትን ቢሸጥ፥ ከተሸጠ በኋላ አንድ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ለመቤዠት ይችላል፤ ለአንድ ሙሉ ዓመት መቤዠት ይችላል።
30 ፤ አንድ ዓመትም እስኪጨረስ ባይቤዠው፥ ቅጥር ባለበት ከተማ የሚሆን ቤት ለገዛው ለልጅ ልጁ ለዘላለም ይጸናለታል፤ በኢዮቤልዩም ከእርሱ አይወጣም።
31 ፤ ቅጥር በሌለበት መንደር ያሉ ቤቶች ግን እንደ እርሻ ይቈጠራሉ፤ ይቤዣሉ፥ በኢዮቤልዩም ይወጣሉ።
32 ፤ በእነርሱ ከተማ ያለ የሌዋውያን ቤት ግን ሌዋውያን ለዘላለም መቤዠት ይችላሉ።
33 ፤ ማናቸውም ሰው ከሌዋውያን ቢገዛ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል የሌዋውያን ከተማ ቤቶች ርስቶቻቸው ናቸውና በርስቱ ከተማ ያለ የተሸጠው ቤት በኢዮቤልዩ ይመለሳል።
34 ፤ በከተማቸውም ዙሪያ ያለችው መሰምርያ የዘላለም ርስታቸው ናትና አትሸጥም።
35 ፤ ወንድምህ ቢደኸይ እጁም በአንተ ዘንድ ቢደክም፥ አጽናው፤ እንደ እንግዳና እንደ መጻተኛም ከአንተ ጋር ይኑር።
36 ፤ ወንድምህ ከአንተ ጋር ይኖር ዘንድ ከእርሱ ምንም ወለድ ወይም ትርፍ አትውሰድ፤ ነገር ግን አምላክህን ፍራ።
37 ፤ ብርህን በወለድ አታበድረው፤ መኖህንም በትርፍ አትስጠው።
38 ፤ የከነዓንን ምድር እሰጣችሁ ዘንድ፥ አምላክም እሆናችሁ ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
39 ፤ ወንድምህም ቢደኸይ ራሱንም ለአንተ ቢሸጥ፥ እንደ ባሪያ አድርገህ አትግዛው።
40 ፤ እንደ ምንደኛና እንደ መጻተኛ ከአንተ ጋር ይሁን፤ እስከ ኢዮቤልዩም ዓመት ያገልግልህ።
41 ፤ በዚያን ጊዜም እርሱ ከልጆቹ ጋር ከአንተ ይውጣ፥ ወደ ወገኖቹም ወደ አባቱም ርስት ይመለስ።
42 ፤ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው ባሪያዎቼ ናቸውና እንደ ባሪያዎች አይሸጡ።
43 ፤ በጽኑ እጅ አትግዛው፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ።
44 ፤ ወንድ ባሪያና ሴት ባሪያ መግዛት ብትፈልግ ግን በዙሪያችሁ ካሉት ከእነርሱ ከአሕዛብ ወንድና ሴት ባሪያዎችን ግዙ።
45 ፤ ደግሞም በእናንተ መካከል ከሚቀመጡት መጻተኞች፥ በምድራችሁም ውስጥ ከወለዱአቸው በእናንተ መካከል ከሚቀመጡት ከዘራቸው ውስጥ ባሪያዎችን ግዙ፤ ርስትም ይሁኑላችሁ።
46 ፤ ከእናንተም በኋላ ልጆቻችሁ ይወርሱአቸው ዘንድ ተዉአቸው፤ ከእነርሱም ባሪያዎችን ለዘላለም ትወስዳላችሁ፤ ነገር ግን የእስራኤልን ልጆች ወንድሞቻችሁን በጽኑ እጅ አትግዙአቸው።
47 ፤ በአንተም ዘንድ የሚኖር መጻተኛ ወይም እንግዳ ሀብታም ቢሆን፥ ወንድምህም በእርሱ አጠገብ ቢደኸይ፥ ራሱንም ለመጻተኛው ወይም ለእንግዳው ወይም ለወገኖቹ ዘር ቢሸጥ፥
48 ፤ ከተሸጠ በኋላ መቤዠት ይችላል፤ ከወንድሞቹ አንዱ ይቤዠው፤
49 ፤ ወይም አጎቱ ወይም የአጎቱ ልጅ ይቤዠው፤ ወይም ከወገኑ ለእርሱ የቀረበ ዘመድ ይቤዠው፤ ወይም እርሱ እጁ ቢረጥብ ራሱን ይቤዠው።
50 ፤ ከገዛውም ሰው ጋር ከገዛበት ዓመት ጀምሮ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ይቍጠር፤ የሽያጩም ብር እንደ ዓመታቱ ቍጥር ይሁን፤ እንደ ምንደኛውም ዘመን ከእርሱ ጋር ይሁን።
51 ፤ ብዙ ዓመታትም ቢቀሩ እንደ እነርሱ ቍጥር ከሽያጩ ብር የመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ።
52 ፤ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ጥቂቶች ዓመታት ቢቀሩ ከእርሱ ጋር ይቈጥራል፤ እንደ ዓመታቱም መጠንየመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ።
53 ፤ በየዓመቱ እንደ ምንደኛ ከእርሱ ጋር ይኑር፤ በፊትህ በጽኑ እጅ አይግዛው።
54 ፤ በዚህ ዘመን ሁሉ ግን ባይቤዥ በኢዮቤልዩ ዓመት እርሱ ከልጆቹ ጋር ይውጣ።
55 ፤ የእስራኤል ልጆች ለእኔ ባሪያዎች ናቸውና፤ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው ባሪያዎቼ ናቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።