ምዕራፍ 11

እንግዲህ አምላክህን እግዚአብሔርን ውደድ፥ ሕጉንም ሥርዓቱንም ፍርዱንም ትእዛዙንም ሁልጊዜ ጠብቅ።
2 ፤ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ተግሣጽ፥ ታላቅነቱንም፥ የጸናችም እጁን፥ የተዘረጋውንም ክንዱን፥
3 ፤ በግብፅም መካከል በንጉሡ በፈርዖንና በአገሩ ሁሉ ላይ ያደረጋትን ተአምራቱንና ሥራውን፥
4 ፤ በተከተሉአችሁም ጊዜ በኤርትራ ባሕር ውኃ እንዳሰጠማቸው፥ እግዚአብሔርም እስከ ዛሬ ድረስ እንዳጠፋቸው፥ በግብፅ ጭፍራ በፈረሶቻቸውም በሰረገሎቻቸውም ያደረገውን፥
5 ፤ ወደዚህ ስፍራ እስክትመጡ ድረስ በምድረ በዳ ያደረገላችሁን፥
6 ፤ በእስራኤልም ሁሉ መካከል ምድር አፍዋን ከፍታ እነርሱንና ቤተሰቦቻቸውን ድንኳኖቻቸውንም ለእነርሱም የነበራቸውን ሁሉ በዋጠቻቸው በሮቤል ልጅ በኤልያብ ልጆች በዳታንና በአቤሮን ያደረገውን ላላወቁትና ላላዩት ልጆቻችሁ አልነግራቸውምና እናንተ ዛሬ እወቁ።
7 ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ያደረጋትን ታላቂቱን ሥራ ሁሉ ዓይኖቻችሁ አይተዋል።
8
9 ፤ እንግዲህ እንድትጠነክሩ፥ ትወርሱአትም ዘንድ ወደምትሻገሩባት ምድር እንድትገቡ እንድትወርሱአትም፥ እግዚአብሔርም ለእነርሱና ለዘራቸው ይሰጣት ዘንድ በማለላቸው ወተትና ማርም በምታፈስሰው ምድር ዕድሜአችሁ እንዲረዝም፥ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን ትእዛዝ ሁሉ ጠብቁ።
10 ፤ ትወርሳት ዘንድ የምትገባባት ምድር፥ በአትክልት ስፍራ እንደሚዘሩ ዘርህን እንደዘራህባት፥ በእግርህም እንዳጠጣሃት፥ እንደ ወጣህባት እንደ ግብፅ ምድር አይደለችም።
11 ፤ ነገር ግን ትወርሱአት ዘንድ ተሻግራችሁ የምትገቡባት ምድር ኮረብታና ሸለቆ ያለባት አገር ናት፤ በሰማይ ዝናብ ውኃ ትረካለች።
12 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሚጐበኛት አገር ናት፤ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የአምላክህ የእግዚአብሔር ዓይን ሁልጊዜ በእርስዋ ላይ ነው።
13 ፤ እንዲህም ይሆናል፤ እናንተ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፥ በፍጹምም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ታመልኩት ዘንድ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን ትእዛዜን ፈጽማችሁ ብትሰሙ፥
14 ፤ እህልህን ወይንህንም ዘይትህንም ትሰበስብ ዘንድ በየጊዜው የበልጉን ዝናብና የክረምቱን ዝናብ ለምድራችሁ አወርዳለሁ።
15 ፤ በሜዳ ለእንስሶችህ ሣርን እሰጣለሁ፥ ትበላማለህ፥ ትጠግብማለህ።
16 ፤ ልባችሁ እንዳይስት፥ ፈቀቅ እንዳትሉ፥ ሌሎችንም አማልክት እንዳታመልኩ፥ እንዳትሰግዱላቸውም፥
17 ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ እንዳይነድድባችሁ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ ምድሪቱም ፍሬዋን እንዳትሰጥ ሰማይን እንዳይዘጋባችሁ፤ እግዚአብሔርም ከሚሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር ፈጥናችሁ እንዳትጠፉ ተጠንቀቁ።
18 ፤ እንግዲህ እነዚህን ቃሎች በልባችሁና በነፍሳችሁ አኑሩ፤ እነርሱንም ለምልክት በእጃችሁ ላይ እሰሩአቸው፥ በዓይኖቻችሁም መካከል እንደክታብ ይሁኑ።
19 ፤ ልጆቻችሁንም አስተምሩአቸው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም ስትነሣም አጫውቱአቸው።
20
21 ፤ እርስዋንም እንዲሰጣቸው እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ በማለላቸው ምድር፥ እንደ ሰማይ ዘመን በምድር ላይ፥ ዘመናችሁ የልጆቻችሁም ዘመን ይረዝም ዘንድ በቤትህ መቃኖችና በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።
22 ፤ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፥ በመንገዱም ሁሉ ትሄዱ ዘንድ፥ ከእርሱም ጋር ትጣበቁ ዘንድ፥ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን ትእዛዝ ሁሉ ብትጠብቁ ብታደርጉአትም፥
23 ፤ እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ ሁሉ ከፊታችሁ ያወጣል፥ ከእናንተም የሚበልጡትን የሚበረቱትንም አሕዛብ ትወርሳላችሁ።
24 ፤ የእግራችሁ ጫማ የምትረግጣት ስፍራ ሁሉ ለእናንተ ትሆናለች፤ ከምድረ በዳም ከሊባኖስም ከታላቁም ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ባሕር ድረስ ዳርቻችሁ ይሆናል።
25 ፤ በእናንተም ፊት ማንም መቆም አይችልም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር፥ እርሱ እንደ ተናገራችሁ፥ ማስፈራታችሁን ማስደንገጣችሁንም በምትረግጡአት ምድር ሁሉ ላይ ያኖራል።
26 ፤ እነሆ፥ እኔ ዛሬ በፊታችሁ በረከትንና መርገምን አኖራለሁ፤
27 ፤ በረከትም፥ እኔ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትሰሙ፤
28 ፤ መርገምም፥ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባትሰሙ፥ ዛሬም ካዘዝኋችሁ መንገድ ፈቀቅ ብትሉ፥ ሌሎችንም የማታውቋቸውን አማልክት ብትከተሉ ነው።
29 ፤ አምላክህም እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ አንተን ወደምትሄድባት ምድር ባገባህ ጊዜ፥ በረከቱን በገሪዛን ተራራ መርገሙንም በጌባል ተራራ ታኖራለህ።
30 ፤ እነርሱም በዮርዳኖስ ማዶ፥ ከፀሐይ መግቢያ ካለችው መንገድ በኋላ፥ በዓረባ በተቀመጡት በከነዓናውያን ምድር፥ በጌልገላ ፊት ለፊት በሞሬ የአድባር ዛፍ አጠገብ ናቸው።
31 ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር የሚሰጣችሁን ምድር ትወርሱ ዘንድ ዮርዳኖስን ትሻገራላችሁ፥ ትወርሱአታላችሁም፥ ትቀመጡባታላችሁም።
32 ፤ እኔም ዛሬ በፊታችሁ የማኖራትን ሥርዓትና ፍርድ ሁሉ ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ።