ምዕራፍ 33

የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ ሳይሞት የእስራኤልን ልጆች የባረከባት በረከት ይህች ናት።
2 ፤ እንዲህም አለ። እግዚአብሔር ከሲና መጣ፥ በሴይርም ተገለጠ፤ ከፋራን ተራራ አበራላቸው፥ ከአእላፋትም ቅዱሳኑ መጣ፤ በስተ ቀኙም የእሳት ሕግ ነበረላቸው።
3 ፤ ሕዝቡንም ወደዳቸው፤ ቅዱሳኑ ሁሉ በእጅህ ናቸው፤ በእግሮችህም አጠገብ ተቀመጡ፤ ቃሎችህን ይቀበላሉ።
4 ፤ ሙሴ ለያዕቆብ ጉባኤ ርስት የሆነውን ሕግ አዘዘን።
5 ፤ የሕዝቡ አለቆች ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ጋር በተከማቹ ጊዜ፥ ንጉሥ በይሹሩን ነበረ።
6 ፤ ሮቤል በህይወት ይኑር፥ አይሙት፤ ሰዎቹም በቍጥር ብዙ ይሁኑ።
7 ፤ የይሁዳ በረከት ይህ ነው፤ እንዲህም አለ። አቤቱ፥ የይሁዳን ድምፅ ስማ፥ ወደ ወገኖቹም አግባው፤ እጆቹ ይጠንክሩለት፤ በጠላቶቹ ላይ ረዳት ትሆነዋለህ።
8 ፤ ስለ ሌዊም እንዲህ አለ፥ ቱሚምህና ኡሪምህ ለቅዱስህ ሰው ነው፥ በማሳህ ለፈተንኸው፥ በመሪባ ውኃም ለተከራከርኸው፤
9 ፤ ስለ አባቱና ስለ እናቱ። አላየሁም ላለ፥ ወንድሞቹንም ላላስተዋለ፥ ልጆቹንም ላላወቀ፤ ቃልህን አደረጉ፥ ቃል ኪዳንህንም ጠበቁ።
10 ፤ ፍርድህን ለያዕቆብ፥ ሕግህንም ለእስራኤል ያስተምራሉ፤ በፊትህ ዕጣንን፥ በመሠዊያህም የሚቃጠል መሥዋዕት ይሠዋሉ።
11 ፤ አቤቱ፥ ሀብቱን ባርክ፥ የእጁንም ሥራ ተቀበል፤ የሚነሣበትን ወገብ ውጋው፥ የሚጠሉትም አይነሡ።
12 ፤ ስለ ብንያምም እንዲህ አለ። በእግዚአብሔር የተወደደ በእርሱ ዘንድ ተማምኖ ይኖራል፤ ቀኑን ሁሉ ይጋርደዋል፥ በትከሻውም መካከል ያድራል።
13 ፤ ስለ ዮሴፍም እንዲህ አለ፥ ምድሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተባረከ ይሁን፤ በሰማያት ገናንነት በጠል፥ በታችኛውም ቀላይ፥
14 ፤ በፀሐዩ ፍሬያት ገናንነት፥ በጨረቃውም መውጣት ገናንነት
15 ፤ በቀደሙትም ተራሮች ከፍተኛነት፥ በዘላለሙም ኮረብቶች ገናንነት፥
16 ፤ በምድሪቱም ገናንነትና ሞላዋ፥ በቍጥቋጦው ውስጥ ከነበረው በረከት በዮሴፍ ራስ ላይ፥ ከወንድሞቹም በተለየው ራስ አናት ላይ ይውረድ።
17 ፤ ለላሞች በኵር ግርማ ይሆናል፤ ቀንዶቹ አንድ ቀንድ እንዳለው ናቸው፤ በእነርሱ እስከ ምድር ዳርቻ ያሉትን አሕዛብ ሁሉ ይወጋል፤ የኤፍሬም እልፍ አእላፋት፥ የምናሴም አእላፋት እነርሱ ናቸው።
18 ፤ ስለ ዛብሎንም እንዲህ አለ። ዛብሎን ሆይ፥ በመውጣትህ፥ ይሳኮር ሆይ፥ በድንኳንህ ውስጥ ደስ ይበላችሁ።
19 ፤ የተሰወረውን የአሸዋውን መዝገብ፥ የባሕሩንም ባለጠግነት ይጠባሉና አሕዛብን ወደ ተራራው ይጠራሉ፤ በዚያ የጽድቅ መሥዋዕት ይሠዋሉ።
20 ፤ ስለ ጋድም እንዲህ አለ። ጋድን ሰፊ ያደረገ ቡሩክ ይሁን፤ እንደ አንበሳይቱ ዐርፎአል፤ ክንድንና ራስን ይቀጠቅጣል።
21 ፤ በዚያ የአለቃ እድል ፈንታ ቀርቶአልና የመጀመሪያውን ክፍል ለራሱ መረጠ፤ ወደ ሕዝብ አለቆችም መጣ፤ የእግዚአብሔርንም ጽድቅ፥ ፍርዱንም ከእስራኤል ጋር አደረገ።
22 ፤ ስለ ዳንም እንዲህ አለ። ዳን የአንበሳ ደቦል ነው፤ ከባሳን ዘልሎ ይወጣል።
23 ፤ ስለ ንፍታሌምም እንዲህ አለ። ንፍታሌም በሞገስ ጠግቦአል፥ የእግዚአብሔርንም በረከት ተሞልቶአል፤ ባሕሩንና ደቡቡን ይወርሳል።
24 ፤ ስለ አሴርም እንዲህ አለ። አሴር በልጆች የተባረከ ይሁን፤ በወንድሞቹ የተወደደ ይሁን፤ እግሩንም በዘይት ውስጥ ያጥልቅ።
25 ፤ ጫማህ ብረትና ናስ ይሆናል፤ እንደ ዕድሜህ እንዲሁ ኃይልህ ይሆናል።
26 ፤ ይሹሩን ሆይ፥ በሰማያት ላይ ለረድኤትህ፥ በደመናትም ላይ በታላቅነት እንደሚሄድ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም።
27 ፤ መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፥ የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፤ ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ። አጥፋው ይላል።
28 ፤ እስራኤልም ተማምኖ፥ የያዕቆብም ምንጭ ብቻውን፥ እህልና የወይን ጠጅ ባለባት ምድር ይኖራል፤ ሰማያቱም ጠልን ያንጠባጥባሉ።
29 ፤ እስራኤል ሆይ፥ ምስጉን ነህ፤ በእግዚአብሔር የዳነ ሕዝብ እንደ አንተ ማን ነው? እርሱ የረድኤትህ ጋሻ፥ የከፍተኛነትህም ሰይፍ ነው። ጠላቶችህም ይገዙልሃል፤ አንተም ከፍታቸውን ትረግጣለህ።