ምዕራፍ 12

በምድር ላይ በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ለመውረስ በሰጣችሁ አገር፥ የምትጠብቁአትና የምታደርጉአት ሥርዓትና ፍርድ እነዚህ ናቸው።
2 ፤ እናንተ የምትወርሱአቸው አሕዛብ አማልክቶቻቸውን ያመለኩባቸውን በረጅም ተራሮች በኮረብቶችም ላይ ከለምለምም ዛፍ በታች ያለውን ስፍራ ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉአቸው፤
3 ፤ መሠዊያቸውንም አፍርሱ፥ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብሩ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቻቸውንም በእሳት አቃጥሉ፥ የአማልክቶቻቸውንም የተቀረጹ ምስሎች አንከታክቱ፤ ከዚያም ስፍራ ስማቸውን አጥፉ።
4 ፤ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር እንዲህ ያለ ሥራ አትሥሩ።
5 ፤ ነገር ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር ከነገዶቻችሁ ሁሉ ስሙን በዚያ ያኖር ዘንድ ወደዚያ ወደ መረጠው ስፍራ ትመጣላችሁ፥ ማደሪያውንም ትሻላችሁ።
6 ፤ ወደዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን፥ ሌላ መሥዋዕታችሁንም፥ አሥራታችሁንም፥ በእጃችሁም ያነሣችሁትን ቍርባን፥ ስእለታችሁንም፥ በፈቃዳችሁ የምታቀርቡትን፥ የላማችሁንና የበጋችሁንም በኵራት ውሰዱ።
7 ፤ በዚያም በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ብሉ፥ እጃችሁንም በምትዘረጉበት፥ አምላክህ እግዚአብሔር በባረከህ ነገር ሁሉ፥ እናንተና ቤተሰባችሁ ደስ ይበላችሁ።
8 ፤ ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን፥ እኛ በዚህ ዛሬ የምናደርገውን ሁሉ አታደርጉም፤
9 ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ወደሚሰጣችሁ ዕረፍትና ርስት እስከ ዛሬ ድረስ አልገባችሁምና።
10 ፤ ዮርዳኖስን ግን በተሻገራችሁ ጊዜ፥ አምላካችሁም እግዚአብሔር በሚያወርሳችሁ ምድር በተቀመጣችሁ ጊዜ፥ ያለ ፍርሃትም እንድትኖሩ ከከበቡአችሁ ጠላቶች ሁሉ ዕረፍት በሰጣችሁ ጊዜ፥
11 ፤ በዚያን ጊዜ አምላካችሁ እግዚአብሔር ስሙ ይጠራበት ዘንድ ወደዚያ ወደ መረጠው ስፍራ፥ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን፥ ሌላ መሥዋዕታችሁንም፥ አሥራታችሁንም፥ በእጃችሁ ያነሣችሁትንም ቍርባን፥ ለእግዚአብሔርም ተስላችሁ የመረጣችሁትን ስእለታችሁን ሁሉ ውሰዱ።
12 ፤ እናንተም፥ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁም፥ ባሪያዎቻችሁም፥ ገረዶቻችሁም፥ ከእናንተ ጋር ክፍልና ርስት ስለሌለው በደጆቻችሁ ውስጥ የተቀመጠው ሌዋዊም በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበላችሁ።
13 ፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን በሚታይህ ስፍራ ሁሉ እንዳታቀርብ ተጠንቀቅ።
14 ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ከነገዶችህ ከአንዱ ዘንድ በመረጠው ስፍራ በዚያ የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን አቅርብ፥ በዚያም የማዝዝህን ሁሉ አድርግ።
15 ፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ሰጠህ በረከት፥ ሰውነትህ እንደ ፈቀደ፥ በደጆችህ ሁሉ ውስጥ አርደህ ብላ፤ ንጹሕ ሰው ንጹሕም ያልሆነ ሰው እንደ ሚዳቋና እንደ ዋላ ያለውን ይብላው።
16 ፤ ደሙን ግን እንደ ውኃ በምድር ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው።
17 ፤ የእህልህን የወይን ጠጅህን የዘይትህንም አሥራት፥ የላምህንና የበግህንም በኩራት፥ የተሳልኸውንም ስእለት ሁሉ፥ በፈቃድህም ያቀረብኸውን፥ በእጅህም ያነሣኸውን ቍርባን በደጆችህ ውስጥ መብላት አትችልም።
18 ፤ ነገር ግን አንተ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም፥ ባሪያዎችህና ገረዶችህም፥ በአገርህም ደጅ ያለው ሌዋዊ አምላክህ እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ብሉት፤ እጅህንም በምትዘረጋበት ነገር ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበልህ።
19 ፤ በምድርህ ላይ በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ሌዋዊውን ቸል እንዳትል ተጠንቀቅ።
20 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ነገረህ አገርህን ባሰፋ ጊዜ፥ ሰውነትህም ሥጋ መብላት ስለ ወደደች። ሥጋ ልብላ ስትል፥ እንደ ሰውነትህ ፈቃድ ሥጋን ብላ።
21 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር በዚያ ስሙን ያኖር ዘንድ የመረጠው ስፍራ ከአንተ ሩቅ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ከሰጠህ ከላምና ከበግ መንጋህ እንዳዘዝሁህ እረድ፥ እንደ ሰውነትህም ፈቃድ ሁሉ በአገርህ ደጅ ውስጥ ብላው።
22 ፤ ሚዳቋና ዋላ እንደሚበሉ እንዲሁ ብላው፤ ንጹሕ ሰው ንጹሕም ያልሆነ ይብላው።
23 ፤ ነገር ግን ደሙ ነፍሱ ነውና፥ ነፍሱንም ከሥጋው ጋር መብላት አይገባህምና ደሙን እንዳትበላ ተጠንቀቅ።
24 ፤ በምድር ላይ እንደ ውኃ አፍስሰው እንጂ አትብላው።
25 ፤ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር ስታደርግ ለአንተ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም እንዲሆንላችሁ፥ አትብላው።
26 ፤ ነገር ግን የተቀደሰውን ነገርህን ስእለትህንም ይዘህ እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ሂድ።
27 ፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕትህን፥ ሥጋውንና ደሙን፥ በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ አቅርብ፤ የመሥዋዕትህም ደም በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ይፍሰስ፥ ሥጋውንም ብላው።
28 ፤ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ቅን የሆነውን ነገር ስታደርግ ለአንተ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ ለዘላለም መልካም ይሆንላችሁ ዘንድ እኔ የማዝዝህን እነዚህን ቃሎች ሁሉ ሰምተህ ጠብቅ።
29 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳቸው ዘንድ የምትሄድባቸውን አሕዛብን በፊትህ ባጠፋ ጊዜ፥ አንተም በወረስሃቸው ጊዜ፥
30 ፤ በምድራቸውም በተቀመጥህ ጊዜ፥ ከፊትህ ከጠፉ በኋላ እነርሱን ለመከተል እንዳትጠመድ። እነዚህስ አሕዛብ አማልክቶቻቸውን ያመለኩት እንዴት ነው? እንዲሁ ደግሞ እኔ አደርጋለሁ ብለህ ስለ አማልክቶቻቸው እንዳትጠይቅ ተጠንቀቅ።
31 ፤ እግዚአብሔር የሚጠላውን ርኵሰት ሁሉ እነርሱ ለአማልክቶቻቸው አድርገዋልና፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ደግሞ ለአማልክቶቻቸው በእሳት ያቃጥሉአቸዋልና አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር እንዲሁ አታድርግ።
32 ፤ እኔ የማዝዝህን ነገር ሁሉ ታደርገው ዘንድ ጠብቅ፤ ምንም በእርሱ ላይ አትጨምር፥ ከእርሱም ምንም አታጕድል።