ምዕራፍ 3

ተመልሰን በባሳን መንገድ ወጣን፥ የባሳን ንጉሥ ዐግም ሕዝቡም ሁሉ በኤድራይ ሊዋጉን ወጡ።
2 ፤ እግዚአብሔርም። እርሱንና ሕዝቡን ሁሉ ምድሩንም በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼአለሁና አትፍራው፤ በሐሴቦን ይኖር በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ላይ እንዳደረግህ በእርሱም ታደርግበታለህ አለኝ።
3 ፤ አምላካችን እግዚአብሔርም ደግሞ የባሳንን ንጉሥ ዐግን ሕዝቡንም ሁሉ በእጃችን አሳልፎ ሰጠን፤ እኛም መታነው፤ አንድ ሰው እንኳ አምልጦ አልቀረለትም።
4 ፤ በዚያን ጊዜም ከተሞቹን ሁሉ ወሰድን፤ አንድም ያልወሰድነው የለም፤ በባሳን ያለውን የዐግን መንግሥት፥ የአርጎብን አገር ሁሉ፥ ስድሳ ከተሞችን ወሰድን።
5 ፤ በቅጥር ካልተመሸጉት ከእጅግ ብዙ ከተሞች ሌላ፥ እነዚህ ከተሞች ሁሉ ቁመቱ ረጅም በሆነ ቅጥር በመዝጊያና በመወርወሪያም የተመሸጉ ነበሩ።
6 ፤ በሐሴቦንም ንጉሥ በሴዎን እንዳደረግን ፈጽሞ አጠፋናቸው፤ ከተሞቹን ሁሉ ከወንዶችና ከሴቶች ከሕፃናቶችም ጋር አጠፋናቸው።
7 ፤ ከብቶቹን ሁሉ የከተሞቹንም ምርኮ ለእኛ በዘበዝን።
8 ፤ በዚያም ዘመን ከአርኖን ሸለቆ ጀምሮ እስከ አርሞንዔም ተራራ ድረስ ምድሪቱን በዮርዳኖስ ማዶ ከነበሩ ከሁለቱ ከአሞራውያን ነገሥታት እጅ ወሰድን፤
9 ፤ ሲዶናውያን አርሞንዔምን ሢርዮን ብለው ይጠሩታል፥ አሞራውያንም ሳኔር ብለው ይጠሩታል።
10 ፤ በሜዳውም ያሉትን ከተሞች ሁሉ፥ ገለዓድንም ሁሉ፥ በባሳንም ያሉትን የዐግን መንግሥት ከተሞች እስከ ሰልካና እስከ ኤድራይ ድረስ ባሳንን ሁሉ ወሰድን።
11 ፤ ከራፋይም ወገን የባሳን ንጉሥ ዐግ ብቻውን ቀርቶ ነበር፤ እነሆ፥ አልጋው የብረት አልጋ ነበረ፤ እርሱ በአሞን ልጆች አገር በነበረባት አለ፤ ርዝመቱ ዘጠኝ ክንድ ወርዱም አራት ክንድ በሰው ክንድ ልክ ነበረ።
12 ፤ ይህችንም ምድር በዚያን ዘመን ወረስን፤ በአርኖንም ሸለቆ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ የገለዓድን ተራራማ አገር እኩሌታ ከተሞቹንም ለሮቤልና ለጋድ ነገድ ሰጠኋቸው።
13 ፤ ከገለዓድም የቀረውን የዐግንም መንግሥት ባሳንን ሁሉ፥ የአርጎብንም ምድር ሁሉ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጠሁ፤ ያችም ባሳን ሁሉ የራፋይም አገር ተብላ ተቈጠረች።
14 ፤ የምናሴ ልጅ ኢያዕር እስከ ጌሹራውያንና እስከ ማዕካታውያን ዳርቻ ድረስ የአርጎብን ምድር ሁሉ ወሰደ፤ ይህችንም የባሳንን ምድር እስከ ዛሬ ድረስ በስሙ የኢያዕር መንደሮች ብሎ ጠራ።
15 ፤ ለማኪርም ገልዓድን ሰጠሁት።
16 ፤ ለሮቤል ነገድና ለጋድም ነገድ ከገለዓድ ጀምሮ እስከ አርኖን ሸለቆ ድረስ የሸለቆውን እኩሌታ ዳርቻውንም፥ እስከ አሞን ልጆች ዳርቻ እስከ ያቦቅ ወንዝ ድረስ፥
17 ፤ ከኪኔሬት እስከ ዓረባ ባሕር እርሱም የጨው ባሕር ድረስ ከፈስጋ ተራራ በታች ወደ ምሥራቅ ያለውን ዓረባ ዮርዳኖስንም ዳሩንም ሰጠኋቸው።
18 ፤ በዚያም ዘመን እንዲህ ብዬ አዘዝኋችሁ። አምላካችሁ እግዚአብሔር ይህችን ምድር ርስት አድርጎ ሰጥቶአችኋል፤ መሣሪያችሁን ይዛችሁ እናንተ አርበኞች ሁሉ በወንድሞቻችሁ በእስራኤል ልጆች ፊት ትሻገራላችሁ።
19 ፤ ነገር ግን እጅግ ከብቶች እንዳሉአችሁ አውቃለሁና ሴቶቻችሁና ልጆቻችሁ ከብቶቻችሁም በሰጠኋችሁ ከተሞች ይቀመጣሉ፤
20 ፤ ይኸውም እግዚአብሔር እናንተን እንዳሳረፈ፥ ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፍ ድረስ እነርሱም ደግሞ በዮርዳኖስ ማዶ አምላካችሁ እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ ነው፤ ከዚያም በኋላ እናንተ ሁሉ ወደ ሰጠኋችሁ ርስት ትመለሳላችሁ።
21 ፤ በዚያም ጊዜ ኢያሱን። አምላካችሁ እግዚአብሔር በእነዚህ በሁለቱ ነገሥት ያደረገውን ሁሉ ዓይኖችህ አይተዋል፤ እንዲሁ በምታልፍባቸው መንግሥታት ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ያደርጋል።
22 ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር እርሱ ስለ እናንተ ይዋጋልና አትፍራቸውም ብዬ አዘዝሁት።
23 ፤ በዚያም ዘመን እኔ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብዬ ለመንሁ።
24 ፤ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ታላቅነትህን የጸናችውንም እጅህን ለእኔ ለባሪያህ ማሳየት ጀምረሃል፤ በሰማይና በምድርም እንደ ሥራህ እንደ ኃይልህም ይሠራ ዘንድ የሚችል አምላክ ማን ነው?
25 ፤ እኔ ልሻገር በዮርዳኖስም ማዶ ያለችውን መልካሚቱን ምድር ያንም መልካሙን ተራራማውን አገር ሊባኖስንም ልይ።
26 ፤ እግዚአብሔር ግን በእናንተ ምክንያት ተቈጣኝ አልሰማኝምም፤ እግዚአብሔርም አለኝ። ይበቃሃል፤ በዚህ ነገር ደግመህ አትናገረኝ።
27 ፤ ይህን ዮርዳኖስን አትሻገርምና ወደ ፈስጋ ራስ ውጣ፤ ዓይንህንም ወደ ምዕራብ ወደ ሰሜንም ወደ ደቡብም ወደ ምሥራቅም አንሥተህ በዓይንህ ተመልከት።
28 ፤ ኢያሱ በዚህ ሕዝብ ፊት ይሻገራልና፥ አንተም የምታያትን ምድር እርሱ ያወርሳቸዋልና ኢያሱን እዘዘው፥ አደፋፍረውም፥ አጽናውም።
29 ፤ በቤተፌጎርም ፊት ለፊት በሸለቆው ውስጥ ተቀመጥን።