ምዕራፍ 32

ሰማያት ሆይ፥ አድምጡ፥ እኔም እናገራለሁ፤ ምድርም የአፌን ቃሎች ትስማ።
2 ፤ ትምህርቴ እንደ ዝናብ ትፈስሳለች፥ ነገሬ እንደ ጠል ትንጠባጠባለች፤ በልምላሜ ላይ እንደ ጤዛ፥ በሣርም ላይ እንደ ካፊያ።
3 ፤ የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁና፤ ለአምላካችን ታላቅነትን ስጡ።
4 ፤ እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፤ የታመነ አምላክ፥ ክፋትም የሌለበት፥ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው።
5 ፤ እነርሱ ረከሱ፤ ልጆቹም አይደሉም፤ ነውርም አለባቸው፤ ጠማማና ገልበጥባጣ ትውልድ ናቸው።
6 ፤ ደንቆሮ ብልሃተኛም ያልሆንህ ሕዝብ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር ይህንን ትመልሳለህ? የገዛህ አባትህ አይደለምን? የፈጠረህና ያጸናህ እርሱ ነው።
7 ፤ የዱሮውን ዘመን አስብ፥ የብዙ ትውልድንም ዓመታት አስተውል፤ አባትህን ጠይቅ፥ ያስታውቅህማል፤ ሽማግሌዎችህን ጠይቅ፥ ይነግሩህማል።
8 ፤ ልዑል ለአሕዛብ ርስታቸውን ባወረሰ ጊዜ፥ የአዳምን ልጆች በለየ ጊዜ፥ እንደ እስራኤል ልጆች ቍጥር የአሕዛብን ድንበር አቆመ።
9 ፤ የእግዚአብሔር እድል ፈንታ ሕዝቡ ነው፤ ያዕቆብም የርስቱ ገምድ ነው።
10 ፤ በምድረ በዳ በጥማት፥ የነፋስ ጩኸትም በሞላበት ውድማ አገኘው፤ ከበበው ተጠነቀቀለትም፤ እንደ ዓይን ብሌን ጠበቀው።
11 ፤ ንስር ጫጩቶቹን እንደሚያወጣ፥ በእነርሱም ላይ እንደሚሰፍፍ፥ ክንፎቹን ዘርግቶ ወሰዳቸው፥ በክንፎቹም አዘላቸው።
12 ፤ እግዚአብሔር ብቻውን መራው፤ ከእርሱም ጋር ሌላ አምላክ አልነበረም።
13 ፤ በምድር ከፍታ ላይ አወጣው፤ የእርሻውን ፍሬ በላ፤ ከዓለትም ድንጋይ በሚገኝ ማር፥ ከጭንጫውም ድንጋይ በሚገኝ ዘይት አጠባው፤
14 ፤ የላሙንም ቅቤ፥ የመንጋውም ወተት፥ ከጠቦት ስብ ጋር፥ የባሳንንም አውራ በግ፥ ፍየሉንም፥ ከስንዴ እሸት ጋር በላህ፤ ከወይኑም ደም ያለውን ጠጅ ጠጣህ።
15 ፤ ይሹሩን ወፈረ፥ ረገጠ፤ ወፈረ፥ ደነደነ፥ ሰባ፤ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ፤ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ።
16 ፤ በሌሎች አማልክት አስቀኑት፥ በርኵሰታቸውም አስቈጡት።
17 ፤ እግዚአብሔር ላልሆኑ አጋንንት፥ ለማያውቋቸውም አማልክት፥ በቅርብ ጊዜ ለተነሡ ለአዲሶች አባቶቻቸውም ላልፈሩአቸው አማልክት ሠዉ።
18 ፤ የወለደህን አምላክ ተውህ፥ ያሳደገህን እግዚአብሔርን ረሳህ።
19 ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ስላስቈጡት እግዚአብሔር አይቶ ጣላቸው።
20 ፤ እርሱም አለ። ፊቴን እሰውርባቸዋለሁ፤ ፍጻሜያቸው ምን እንደ ሆነ አያለሁ፤ ጠማማ ትውልድ፥ ያልታመኑም ልጆች ናቸው።
21 ፤ አምላክ ባልሆነው አስቀኑኝ፤ 3 ቍ.15፤ በዕብራይስጥ ይሹሩን የሚለውን ግዕዙ ያዕቆብ ይለዋል። በምናምንቴዎቻቸውም አስቈጡኝ፤ እኔም ሕዝብ ባልሆነው አስቀናቸዋለሁ፤ በማያስተውል ሕዝብ አስቈጣቸዋለሁ።
22 ፤ እሳት ከቍጣዬ ትነድዳለችና፥ እስከ ሲኦል ድረስ ታቃጥላለች፥ ምድርንም ከፍሬዋ ጋር ትበላለች፥ የተራሮችን መሠረት ታነድዳለች።
23 ፤ መከራን እጨምርባቸዋለሁ፤ በፍላጾቼም እወጋቸዋለሁ።
24 ፤ በራብ በንዳድ ይጠፋሉ፤ በንዳድና በመራራ ጥፋት ያልቃሉ፤ የአራዊትን ጥርስ፥ የምድርንም እባብ መርዝ እሰድድባቸዋለሁ።
25 ፤ ጕልማሳውን ከድንግል፥ ሕፃኑንም ከሽማግሌ ጋር፥ በሜዳ ሰይፍ፥ በቤትም ውስጥ ድንጋጤ ያጠፋቸዋል።
26 ፤ እበትናቸዋለሁ አልሁ፤ ከሰዎችም መካከል መታሰቢያቸውን አጠፋለሁ።
27 ፤ ነገር ግን ጠላቶቻቸው እንዳይታበዩ። እጃችን ከፍ ከፍ አለች እንጂ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ አላደረገም እንዳይሉ፥ ስለ ጠላቱ ቍጣ ፈራሁ።
28 ፤ ምክር ያጡ ሕዝብ ናቸው፥ ማስተዋልም የላቸውም።
29 ፤ አእምሮ ቢኖራቸው፥ ይህንን ያስተውሉ ነበር፥ ፍጻሜያቸውንም ያስቡ ነበር።
30 ፤ እርሱ አምላካቸው ካልሸጣቸው፥ እግዚአብሔርም አሳልፎ ካልሰጣቸው፥ አንድ ሰው እንዴት ሺህን ያሳድድ ነበር? ሁለቱሳ እንዴት አሥሩን ሺህ ያሸሹ ነበር?
31 ፤ አምላካችን እንደ አማልክቶቻቸው አይደለም፤ ጠላቶቻችንም ሰነፎች ናቸው።
32 ፤ ወይናቸው ከሰዶም ወይን፥ ከገሞራም እርሻ ነው፤ ፍሬያቸው ሐሞት ነው፤ ዘለላውም መራራ ነው።
33 ፤ የወይን ጠጃቸው የእባብ መርዝ፥ የእፉኝትም ሥራይ ነው።
34 ፤ ይህ በእኔ ዘንድ ተጠብቆ የለምን? በመዝገቤስ የታተመ አይደለምን?
35 ፤ የጥፋታቸው ቀን ቀርቦአልና፥ የሚመጣባቸውም ነገር ይፈጥናልና እግራቸው ሲሰናከል በቀልና ፍርድ የእኔ ነው።
36 ፤ ኃይላቸውም እንደ ደከመ፥ የተዘጋ የተለቀቀም እንደሌለ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳል፥ ስለ ባሪያዎቹም ያዝናል።
37 ፤ እርሱም ይላል። አማልክቶቻቸው የት ናቸው? ይታመኑባቸው የነበሩት አማልክት?
38 ፤ የመሥዋዕታቸውን ስብ የበሉ፥ የመጠጥ ቍርባናቸውንም የወይን ጠጅ የጠጡ? እነርሱ ይነሡ፥ ይርዱአችሁም፥ መጠጊያም ይሁኑላችሁ።
39 ፤ አሁንም እኔ ብቻዬን እኔ እንደ ሆንሁ፥ ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ እዩ፤ እኔ እገድላለሁ፥ አድንማለሁ፤ እኔ እመታለሁ፥ እፈውስማለሁ፤ ከእጄም የሚያድን የለም።
40 ፤ እጄን ወደ ሰማይ እዘረጋለሁና፥ እንዲህም እላለሁ። ለዘላለም እኔ ሕያው ነኝና
41 ፤ የሚንቦገቦግ ሰይፌን እስለዋለሁ፥ እጄም ፍርድን ትይዛለች፥ ጠላቶቼንም እበቀላለሁ፥ ለሚጠሉኝም ፍዳቸውን እከፍላለሁ።
42 ፤ ከተወጉት ከተማረኩትም ደም፥ ፍላጾቼን በደም አሰክራለሁ፤ ከጠላት አለቆችም ራስ ሰይፌ ሥጋ ይበላል።
43 ፤ የባሪያዎቹን ደም ይበቀላልና፥ ጠላቶቹንም ይበቀላቸዋልና፥ ምድሪቱንና ሕዝቡን ይክሳልና እናንተ አሕዛብ ሆይ፥ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ።
44 ፤ ሙሴም የነዌም ልጅ ኢያሱ የዚህችን መዝሙር ቃሎች ሁሉ በሕዝቡ ጆሮ ተናገሩ።
45 ፤ ሙሴም ይህን ቃል ሁሉ ለእስራኤል ሁሉ ተናግሮ ፈጸመ።
46 ፤ እርሱም እንዲህ አላቸው። የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዝዙበት ዛሬ የምመሰክርላችሁን ቃል ሁሉ በልባችሁ አኑሩት።
47 ፤ ይህ ነገር ሕይወታችሁ ነው እንጂ ለእናንተ ከንቱ አይደለምና፤ በዚህም ነገር ትወርሱአት ዘንድ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትገቡባት ምድር ረጅም ዘመን ትቀመጣላችሁ።
48 ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
49 ፤ ወደዚህ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ምድር በዓባሪም ተራራ ውስጥ ወዳለው ወደ ናባው ተራራ ውጣ፥ ለእስራኤልም ልጆች ርስት አድርጌ የምሰጣቸውን የከነዓንን ምድር እይ፤
50 ፤ ወንድምህም አሮን በሖር ተራራ እንደ ሞተ ወደ ወገኖቹም እንደ ተከማቸ፥ በወጣህበት ተራራ ሙት፥ ወደ ወገኖችህም ተከማች፤
51 ፤ በእስራኤል ልጆች መካከል በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ ባለው በመሪባ ውኃ ስለ በደላችሁኝ፥ በእስራኤልም ልጆች መካከል ስላልቀደሳችሁኝ፥
52 ፤ ምድሪቱን ፊት ለፊት ታያለህ እንጂ ወደዚያች እኔ ለእስራኤል ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር አትገባም።