ምዕራፍ 21

አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ በሚሰጥህ ምድር የተገደለ ሰው በሜዳ ወድቆ ቢገኝ፥
2 ፤ ገዳዩም ባይታወቅ፥ ሽማግሌዎችህና ፈራጆችህ ወጥተው በተገደለው ሰው ዙሪያ እስካሉት ከተሞች ድረስ በስፍር ይለኩ፤
3 ፤ ወደ ተገደለውም ሰው አቅራቢያ የሆነችው የከተማይቱ ሽማግሌዎች ለሥራ ያልደረሰችውን ቀንበርም ያልተጫነባትን ጊደር ይውሰዱ፤
4 ፤ የዚያችም ከተማ ሽማግሌዎች ጊደሪቱን ይዘው ፈሳሽ ውኃ ወዳለበት ወዳልታረሰና ዘርም ወዳልተዘራበት ሸለቆ ይሄዳሉ፤ በዚያም በሸለቆው ውስጥ የጊደሪቱን አንገት ይሰብራሉ።
5 ፤ የሌዊ ልጆች ካህናትም ይቀርባሉ፤ በፊቱ እንዲያገለግሉ፥ በስሙም እንዲባርኩ አምላክህ እግዚአብሔር መርጦአቸዋልና፥ በእነርሱም ቃል ክርክር ሁሉ ጉዳትም ሁሉ ይቈረጣልና፤
6 ፤ ወደ ተገደለው ሰው አቅራቢያ የሆነችው የከተማይቱ ሽማግሌዎች ሁሉ በሸለቆው ውስጥ አንገትዋ በተሰበረው ጊደር ላይ እጃቸውን ሲታጠቡ።
7 ፤ እጃችን ይህን ደም አላፈሰሰችም፥ ዓይናችንም አላየችም፤
8 ፤ አቤቱ፥ የተቤዠኸውን ሕዝብህን እስራኤልን ይቅር በል፤ በሕዝብህም በእስራኤል ላይ የንጹሑን ደም በደል አትቍጠር ብለው ይናገራሉ። ስለ ደሙም ይሰረይላቸዋል።
9 ፤ አንተም በእግዚአብሔር ዓይን የቀናውን ባደረግህ ጊዜ የንጹሑን ደም በደል ከመካከልህ ታርቃለህ።
10 ፤ ጠላቶችህን ልትወጋ በወጣህ ጊዜ፥ አምላክህም እግዚአብሔር በእጅህ አሳልፎ በሰጣቸው በማረክሃቸውም ጊዜ፥
11 ፤ በተማረኩት መካከል የተዋበች ሴት ብታይ፥ ብትመኛትም ሚስትም ልታደርጋት ብትወድድ፥ ወደ ቤትህ ታመጣታለህ፤
12 ፤ እርስዋም ራስዋን ትላጫለች፥ ጥፍርዋንም ትቈረጣለች፤
13 ፤ የተማረከችበትንም ልብስ ታወልቃለች፥ በቤትህም ተቀምጣ ስለ አባትዋና ስለ እናትዋ አንድ ወር ሙሉ ታለቅሳለች፤ ከዚያም በኋላ ትደርስባታለህ፥ ባልም ትሆናታለህ፥ እርስዋም ሚስት ትሆንልሃለች።
14 ፤ ከዚያም በኋላ በእርስዋ ደስ ባይልህ አርነት አውጥተህ ወደ ወደደችው ትሰድዳታለህ፤ በዋጋ ግን አትሸጣትም፤ እፍረት አድርገህባታልና እንደ ባሪያ አትቈጥራትም።
15 ፤ ለአንድ ሰው አንዲቱ የተወደደች አንዲቱም የተጠላች ሁለት ሚስቶች ቢኖሩት፥ ለእርሱም የተወደደችው ደግሞም የተጠላችው ልጆችን ቢወልዱ፥ በኵሩም ከተጠላችው ሚስት የተወለደው ልጅ ቢሆን፥
16 ፤ ለልጆቹ ከብቱን በሚያወርስበት ቀን ከተጠላችው ሚስት በተወለደው በበኵሩ ፊት ከተወደደችው ሚስት የተወለደውን ልጅ በኵር ያደርገው ዘንድ አይገባውም፤
17 ፤ ነገር ግን ከከብቱ ሁለት እጥፍ ለእርሱ በመስጠት ከተጠላችው ሚስት የተወለደው ልጅ በኵር እንደ ሆነ ያስታውቅ። የኃይሉ መጀመሪያ ነውና በኵርነቱ የእርሱ ነው።
18 ፤ ማንም ሰው ለአባቱ ቃልና ለእናቱ ቃል የማይታዘዝ ቢቀጡትም የማይሰማቸው እልከኛና ዓመፀኛ ልጅ ቢኖረው፥
19 ፤ አባቱና እናቱ ይዘው ወደ ከተማው ሽማግሌዎች ወደሚኖሩበትም ስፍራ በር ያምጡት፤
20 ፤ የከተማውንም ሽማግሌዎች። ይህ ልጃችን እልከኛና ዓመፀኛ ነው፥ ለቃላችንም አይታዘዝም ስስታምና ሰካራም ነው ይበሉአቸው።
21 ፤ የከተማውም ሰዎች ሁሉ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሩት፤ እንዲህም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታርቃለህ፥ እስራኤልም ሁሉ ሰምተው ይፈራሉ።
22 ፤ ማንም ሰው ለሞት የሚያበቃውን ኃጢአት ቢሠራ፥ እንዲሞትም ቢፈረድበት፥ በእንጨትም ላይ ብትሰቅለው፥
23 ፤ በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና ሬሳው በእንጨት ላይ አይደር፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ የሰጠህን ምድር እንዳታረክስ በእርግጥ በዚያው ቀን ቅበረው።