ምዕራፍ 7

አምላክህ እግዚአብሔር ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር ባመጣህ ጊዜ፥ ከፊትህም ብዙ አሕዛብን፥ ከአንተ የበለጡትን የበረቱትንም ሰባቱን አሕዛብ፥ ኬጢያዊውን ጌርጌሳዊውንም አሞራዊውንም ከነዓናዊውንም ፌርዛዊውንም ኤዊያዊውንም ኢያቡሳዊውንም ባወጣ ጊዜ፥
2 ፤ አምላክህ እግዚአብሔርም በእጅህ አሳልፎ በሰጣቸው በመታሃቸውም ጊዜ፥ ፈጽመህ አጥፋቸው፤ ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን አታድርግ፥ አትማራቸውም፤
3 ፤ ከእነርሱም ጋር አትጋባ፤ ሴት ልጅህን ለወንድ ልጁ አትስጥ፥ ሴት ልጁንም ለወንድ ልጅህ አትውሰድ።
4 ፤ እንዳይከተለኝ ሌሎችንም አማልክት እንዲያመልክ ልጅህን ያስታልና፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ ይነድድባችኋል፥ ፈጥኖም ያጠፋችኋል።
5 ፤ ነገር ግን እንዲህ አድርጉባቸው፤ መሠዊያቸውን አፍርሱ፥ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብሩ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቻቸውንም ቍረጡ፥ የተቀረጸውን ምስላቸውንም በእሳት አቃጥሉ።
6 ፤ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፤ በምድር ፊት ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መረጠህ።
7 ፤ እግዚአብሔርም የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ስለ በዛችሁ አይደለም፤ እናንተ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ጥቂቶች ነበራችሁና፤
8 ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ ወደዳችሁ ለአባቶቻችሁም የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ፥ ስለዚህ እግዚአብሔር በጽኑ እጅ አወጣችሁ፥ ከባርነትም ቤት ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ አዳናችሁ።
9 ፤ አንተም አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ፥ ለሚወድዱትም ትእዛዙንም ለሚጠብቁ ቃል ኪዳኑንና ምሕረቱን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ የታመነ አምላክ እንደ ሆነ እወቅ፤
10 ፤ የሚጠሉትን ለማጥፋት በፊታቸው ብድራት ይመልስባቸዋል፤ ለሚጠላው አይዘገይም፥ ነገር ግን በፊቱ ብድራት ይመልስበታል።
11 ፤ እንግዲህ ታደርጋት ዘንድ እኔ ዛሬ ለአንተ የማዝዛትን ትእዛዝና ሥርዓት ፍርድንም ጠብቅ።
12 ፤ እንዲህም ይሆናል፤ ይህችን ፍርድ ሰምተህ ብትጠብቃት ብታደርጋትም፥ አምላክህ እግዚአብሔር ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳንና ምሕረት ለአንተ ይጠብቅልሃል፤
13 ፤ ይወድድህማል፥ ይባርክህማል፥ ያበዛህማል፤ ይሰጥህም ዘንድ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር የሆድህን ፍሬ የመሬትህንም ፍሬ፥ እህልህን ወይንህንም ዘይትህንም፥ የከብትህንም ብዛት የበግህንም መንጋ ይባርክልሃል።
14 ፤ ከአሕዛብም ሁሉ ይልቅ የተባረክህ ትሆናለህ፤ በሰውህና በከብትህም ዘንድ ወንድ ቢሆን ወይም ሴት ብትሆን መካን አይሆንብህም።
15 ፤ እግዚአብሔርም ሕማምን ሁሉ ከአንተ ያርቃል፤ የምታውቀውንም ክፉውን የግብፅ በሽታ ሁሉ በአንተ ላይ አያደርስብህም፥ በጠላቶችህም ሁሉ ላይ ያመጣባቸዋል።
16 ፤ አምላክህም እግዚአብሔር በእጅህ አሳልፎ የሚጥላቸውን አሕዛብን ሁሉ ታጠፋቸዋለህ፤ ዓይንህም አታዝንላቸውም፤ ያም ወጥመድ ይሆንብሃልና አማልክቶቻቸውን አታምልካቸው።
17 ፤ በልብህም። እነዚህ አሕዛብ ከእኔ ይልቅ ይበዛሉና አወጣቸው ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ብትል፥ አትፍራቸው፤
18 ፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር በፈርዖንና በግብፅ ሁሉ ያደረገውን፥
19 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር፥ ዓይንህ እያየች፥ ታላቅን መቅሠፍት ምልክትንም ተአምራትንም የጸናችውን እጅ የተዘረጋውንም ክንድ አድርጎ እንዳወጣህ፥ አስብ፤ እንዲሁ አምላክህ እግዚአብሔር አንተ በምትፈራቸው በአሕዛብ ሁሉ ላይ ያደርጋል።
20 ፤ ደግሞም አምላክህ እግዚአብሔር የቀሩት ከፊትህም የተሸሸጉት እስኪጠፉ ድረስ ተርብ ይሰድድባቸዋል።
21 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር፥ ታላቅና የሚያስፈራ አምላክ፥ በመካከልህ ነውና ከእነርሱ የተነሣ አትደንግጥ።
22 ፤ አምላክህም እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ በጥቂት በጥቂቱ ከፊትህ ያወጣቸዋል፤ የምድረ በዳ አራዊት እንዳይበዙብህ አንድ ጊዜ ታጠፋቸው ዘንድ አይገባህም።
23 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ግን እነርሱን በእጅህ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፥ እስኪጠፉም ድረስ በታላቅ ድንጋጤ ያስደነግጣቸዋል።
24 ፤ ነገሥታቶቻቸውንም በእጅህ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፥ ስማቸውንም ከሰማይ በታች ታጠፋለህ፤ እስክታጠፋቸው ድረስ ማንም በፊትህ ይቆም ዘንድ አይችልም።
25 ፤ የተቀረጸውንም የአምላኮቻቸውን ምስል በእሳት ታቃጥላለህ፤ የተሠራባቸውን ብርና ወርቅ አትመኝ፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነውና እንዳትጠመድበት ከእርሱ ምንም አትውሰድ።
26 ፤ እንደ እርሱም ርጉም እንዳትሆን ርኩስን ነገር ወደ ቤትህ አታግባ፤ ርጉም ነውና ተጸየፈው፥ ጥላውም።