ምዕራፍ 24

ሰው ሴትን ወስዶ ቢያገባ፥ የእፍረት ነገር ስላገኘባት በእርሱ ዘንድ ሞገስ ባታገኝ፥ የፍችዋን ጽሕፈት ጽፎ በእጅዋ ይስጣት፥ ከቤቱም ይስደዳት።
2 ፤ ከቤቱም ከወጣች በኋላ ሌላ ወንድ ብታገባ፥
3 ፤ ሁለተኛውም ባል ቢጠላት፥ የፍችዋንም ጽሕፈት ጽፎ በእጅዋ ቢሰጣት፥ ከቤቱም ቢሰድዳት፥ ወይም ሚስት አድርጎ ያገባት ሁለተኛው ባልዋ ቢሞት፥
4 ፤ የሰደዳት የቀድሞ ባልዋ ከረከሰች በኋላ ደግሞ ያገባት ዘንድ አይገባውም፤ ያ በእግዚአብሔር የተጠላ ነው፤ አምላክህም እግዚአብሔር ርስት አድርጎ የሰጠህን ምድር አታርክስ።
5 ፤ አዲስ ሚስትም ያገባ ሰው ወደ ጦርነት አይሂድ፥ ነገርም አይጫኑበት፤ ነገር ግን አንድ ዓመት በቤቱ በፈቃዱ ይቀመጥ፥ የወሰዳትንም ሚስቱን ደስ ያሰኛት።
6 ፤ የሰውን ነፍስ እንደ መውሰድ ነውና ወፍጮ ወይም መጅ ስለ መያዣ ማንም አይውሰድ።
7 ፤ ማንም ሰው ከእስራኤል ልጆች ከወንድሞቹ አንዱን ሰርቆ እንደ ባሪያ ሲያደርግበት ወይም ሲሸጠው ቢገኝ፥ ያ ሌባ ይሙት፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታስወግዳለህ።
8 ፤ በለምጽ ደዌ ሌዋውያን ካህናት ያስተማሩህን ሁሉ ፈጽመህ እንድትጠብቅ እንድታደርግም ተጠንቀቅ፤ እኔ ያዘዝኋቸውን እንዲሁ ታደርግ ዘንድ ጠብቅ።
9 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ በመንገድ ሳላችሁ በማርያም ላይ ያደረገውን አስብ።
10 ፤ ለባልንጀራህ ባበደርኸው ጊዜ መያዣውን ልትወስድ ወደ ቤቱ አትግባ።
11 ፤ አንተ በውጭ ቁም ያበደርኸውም ሰው መያዣውን ያውጣልህ።
12 ፤ ያም ሰው ድሃ ቢሆን መያዣውን በአንተ ዘንድ አታሳድር።
13 ፤ ለብሶት እንዲተኛ እንዲባርክህም ፀሐይ ሳይገባ መያዣውን ፈጽመህ መልስለት፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ጽድቅ ይሆንልሃል
14 ፤ ድሀና ችግረኛ የሆነውን ምንደኛ፥ ከወንድሞችህ ወይም በምድርህ በአገርህ ደጅ ውስጥ ከሚቀመጡት መጻተኞች ቢሆን፥ አታስጨንቀው።
15 ፤ ድሀ ነውና፥ ነፍሱም ጠንክራ ትፈልገዋለችና ወደ እግዚአብሔር እንዳይጮኽብህ ኃጢአትም እንዳይሆንብህ ደመወዙን ፀሐይ ሳይገባ በቀኑ ስጠው።
16 ፤ አባቶች ስለ ልጆች አይገደሉ፥ ልጆችም ስለ አባቶች አይገደሉ፤ ነገር ግን ሁሉ እያንዳንዱ በኃጢአቱ ይገደል።
17 ፤ የመጻተኛውንና የድሀ አደጉን ፍርድ አታጣምምባቸው፤ የመበለቲቱን ልብስ ለመያዣ አትውሰድባት።
18 ፤ አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ፥ አምላክህም እግዚአብሔር ከዚያ እንዳዳነህ አስብ፤ ስለዚህ ይህን ነገር ታደርግ ዘንድ አዝዤሃለሁ።
19 ፤ የእርሻህን መከር ባጨድህ ጊዜ ነዶም ረስተህ በእርሻህ ብታስቀር፥ ትወስደው ዘንድ አትመለስ፤ አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ፥ ለመጻተኛና ለድሃ አደግ ለመበለትም ተወው።
20 ፤ የወይራህን ፍሬ ባረገፍህ ጊዜ ከቅርንጫፎቹ ላይ ማርገፉን ለማጣራት አትመለስ፤ ለመጻተኛና ለድሀ አደግ ለመበለትም ይሁን።
21 ፤ የወይንህን ፍሬ በቈረጥህ ጊዜ ቃርሚያውን አትልቀመው፤ ለመጻተኛና ለድሀ አደግ ለመበለትም ይሁን።
22 ፤ አንተም በግብፅ አገር ባሪያ እንደ ነበርህ አስብ፤ ስለዚህ ይህን ታደርግ ዘንድ አዝዤሃለሁ።