ምዕራፍ 2

እግዚአብሔርም እንዳለኝ ተመልሰን በኤርትራ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሄድን፤ የሴይርንም ተራራ ብዙ ቀን ዞርን።
2 ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረኝ።
3 ፤ ይህን ተራራ መዞር ይበቃችኋል፤ ተመልሳችሁ ወደ ሰሜን ሂዱ።
4 ፤ ሕዝቡንም እንዲህ ብለህ እዘዛቸው። በሴይር ላይ በተቀመጡት በወንድሞቻችሁ በዔሳው ልጆች አገር ታልፋላችሁ፥ እነርሱም ይፈሩአችኋል፤ እንግዲህ እጅግ ተጠንቀቁ።
5 ፤ የሴይርን ተራራ ለዔሳው ርስት አድርጌ ስለ ሰጠሁ እኔ ከምድራቸው የጫማ መርገጫ ታህል እንኳ አልሰጣችሁምና አትጣሉአቸው።
6 ፤ ከእነርሱ በገንዘብ ምግብ ገዝታችሁ ትበላላችሁ፤ ውኃም ደግሞ በገንዘብ ገዝታችሁ ትጠጣላችሁ።
7 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር የእጅህን ሥራ ሁሉ ባርኮልሃልና፤ በዚህ በታላቅ ምድረ በዳ መሄድህን አውቆአል፤ በዚህ አርባ ዓመት ውስጥ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነበረ፥ አንዳችም አላጣህም።
8 ፤ በሴይርም ከተቀመጡት ከወንድሞቻችን ከዔሳው ልጆች በዓረባ መንገድ ከኤላትና ከዔጽዮንጋብር አለፍን። ተመልሰንም በሞዓብ ምድረ በዳ መንገድ አለፍን።
9 ፤ እግዚአብሔርም አለኝ። እኔ ዔርን ለሎጥ ልጆች ርስት አድርጌ ስለ ሰጠሁ ከምድሩ ርስት አልሰጣችሁምና ሞዓብን አትጣላ በሰልፍም አትውጋቸው።
10 ፤ አስቀድሞ ታላቅና ብዙ ሕዝብ እንደ ዔናቅም ልጆች በቁመት የረዘሙ ኤሚማውያን በዚያ ይቀመጡ ነበር።
11 ፤ እነርሱም ደግሞ እንደ ዔናቅ ልጆች ራፋይም ይባሉ ነበር፤ ሞዓባውያን ግን ኤሚም ይሉአቸዋል።
12 ፤ ሖራውያንም ደግሞ አስቀድሞ በሴይር ላይ ተቀምጠው ነበር፥ የዔሳው ልጆች ግን አሳደዱአቸው፤ እግዚአብሔርም በሰጠው በርስቱ ምድር እስራኤል እንዳደረገ፥ ከፊታቸው አጠፉአቸው፥ በስፍራቸውም ተቀመጡ።
13 ፤ እግዚአብሔርም። ተነሡ የዘሬድንም ፈፋ ተሻገሩ አለ።
14 ፤ የዘሬድንም ፈፋ ተሻገርን። የዘሬድንም ፈፋ እስከ ተሻገርንበት ድረስ፥ እግዚአብሔር እንደ ማለባቸው የሰልፈኞች ትውልድ ሁሉ ከሰፈሩ መካከል እስከ ጠፉ ድረስ፥ ከቃዴስ በርኔ የተጓዝንበት ዘመን ሠላሳ ስምንት ዓመት ሆነ።
15 ፤ ከሰፈርም መካከል ተቈርጠው እስኪጠፉ ድረስ የእግዚአብሔር እጅ በላያቸው ነበረ።
16 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ሰልፈኞቹ ከጠፉ ከሕዝቡም መካከል ከሞቱ በኋላ፥
17 ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናገረኝ።
18 ፤ አንተ ዛሬ የሞዓብን ዳርቻ ዔርን ታልፋለህ፤
19 ፤ ለሎጥም ልጆች ርስት አድርጌ ስለ ሰጠሁ ከአሞን ልጆች ምድር ርስት አልሰጥህምና በአሞን ልጆች አቅራቢያ ስትደርስ አትጣላቸው አትውጋቸውም።
20 ፤ ያም ደግሞ የራፋይም ምድር ተብሎ ተቆጠረ፤ ራፋይምም አስቀድሞ በዚያ ተቀምጠው ነበር፤ አሞናውያን ግን ዘምዙማውያን ብለው ይጠሩአቸዋል።
21 ፤ ታላቅና ብዙም ሕዝብ እንደ ዔናቅም ልጆች ቁመታቸው የረዘመ ነበሩ፤ እግዚአብሔር ከፊታቸው አጠፋቸው፤ እነርሱንም አሳድደው በስፍራቸው ተቀመጡ።
22 ፤ ሖራውያንን ከፊታቸው አጥፍቶ በሴይር ለተቀመጡት ለዔሳው ልጆች እንዳደረገ እንዲሁ ለእነርሱ አደረገ፤ እነርሱንም አሳድደው በስፍራቸው እስከ ዛሬ ድረስ ተቀመጡ።
23 ፤ እስከ ጋዛም ድረስ በመንደሮች ተቀምጠው የነበሩትን ኤዋውያንን ከከፍቶር የወጡ ከፍቶራውያን አጠፉአቸው፥ በስፍራቸውም ተቀመጡ።
24 ፤ ደግሞም አለ። ተነሥታችሁ ሂዱ፥ የአርኖንንም ሸለቆ ተሻገሩ፤ እነሆ፥ አሞራዊውን የሐሴቦንን ንጉሥ ሴዎንን ምድሩንም በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁ፤ እርስዋን በመውረስ ጀምር፥ ከእርሱም ጋር ተዋጋ።
25 ፤ ከሰማይ በታች ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ ማስደንገጥህንና ማስፈራትህን እሰድድ ዘንድ ዛሬ እጀምራለሁ፤ ወሬህን በሰሙ ጊዜ በፊትህ ይንቀጠቀጣሉ፥ ድንጋጤም ይይዛቸዋል።
26 ፤ ከቅዴሞትም ምድረ በዳ የሰላምን ቃል ይነግሩት ዘንድ ወደ ሐሴቦን ንጉሥ ወደ ሴዎን እንዲህ ብዬ መልእክተኞችን ላክሁ። በአገርህ ላይ ልለፍ፤
27 ፤ በአውራ ጎዳና እሄዳለሁ፥ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አልተላለፍም።
28
29 ፤ የምበላውን ምግብ በገንዘብ ሽጥልኝ፥ የምጠጣውንም ውኃ በገንዘብ ስጠኝ፤ በሴይር የተቀመጡ የዔሳው ልጆች በዔርም የተቀመጡ ሞዓባውያን እንዳደረጉልኝ፥ አምላካችን እግዚአብሔር ወደሚሰጠን ምድር ዮርዳኖስን እስክሻገር ድረስ ብቻ በእግሬ ልለፍ።
30 ፤ የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎን ግን ያሳልፈን ዘንድ አልፈቀደም፤ እንደ ዛሬው ሁሉ በእጅህ አሳልፎ ይሰጠው ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መንፈሱን አደንድኖታልና፥ ልቡንም አጽንቶታልና።
31 ፤ እግዚአብሔርም። ሴዎንንና ምድሩን በእጅህ አሳልፌ መስጠት፥ እነሆ፥ ጀመርሁ፤ ምድሩን ትገዛት ዘንድ መውረስ ጀምር አለኝ።
32 ፤ ሴዎንም ሕዝቡም ሁሉ ሊጋጠሙን ወደ ያሀጽ ወጡ።
33 ፤ አምላካችንም እግዚአብሔር እርሱን አሳልፎ ሰጠን፤ እርሱንም ልጆቹንም ሕዝቡንም ሁሉ መታን።
34 ፤ በዚያን ጊዜም ከተሞቹን ሁሉ ወሰድን የተቀመጡባቸውንም ሰዎች ሁሉ ሴቶችንም ሕፃናቶችንም አጠፋን፤ አንዳችም አላስቀረንም፥
35 ፤ ከብቶቻቸውንና ከከተሞቻቸው ያገኘነውን ብዝበዛ ለራሳችን ወሰድን እንጂ።
36 ፤ በአርኖን ቈላ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር ከሸለቆውም ውስጥ ካለችው ከተማ ጀምረን እስከ ገለዓድ ድረስ ማናቸይቱም ከተማ አልጠነከረችብንም፤ አምላካችን እግዚአብሔር ሁሉን አሳልፎ ሰጠን።
37 ፤ ዳሩ ግን አምላካችን እግዚአብሔር ወደ ከለከለን ሁሉ፥ ወደ አሞን ልጆች ምድር በያቦቅም ወንዝ አጠገብ ወዳለው ስፍራ ሁሉ በተራራማውም አገር ወዳሉት ከተሞች አልደረስንም።