ምዕራፍ 22

የወንድምህ በሬ ወይም በግ ጠፍቶ ብታይ ቸል አትበል፤ ወደ ወንድምህ መልሰው።
2 ፤ ወንድምህም በአቅራቢያህ ባይሆን ወይም ባታውቀው ይዘህ ወደ ቤትህ ትገባለህ፤ ወንድምህ እስኪሻው ድረስ በአንተ ዘንድ ይቀመጣል፥ ለእርሱም ትመልሰዋለህ።
3 ፤ እንዲህም በአህያው ወይም በልብሱ ታደርጋለህ፤ እንዲህም በወንድምህ በጠፋበት ነገር ሁሉ ባገኘኸው ጊዜ ታደርጋለህ፤ ቸል ልትለው አይገባህም።
4 ፤ የወንድምህ አህያ ወይም በሬው በመንገድ ወድቆ ብታይ ከእርሱ ጋር ሆነህ አነሣሣው እንጂ ቸል አትበለው።
5 ፤ ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ፥ ወንድም የሴት ልብስ አይልበስ፤ ይህን የሚያደርግ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነውና።
6 ፤ በመንገድ ስትሄድ በዛፍ ወይም በመሬት ላይ እናቲቱ በጫጩቶችዋ ወይም በእንቍላሎችዋ ላይ ተኝታ ሳለች የወፍ ጎጆ ብታገኝ፥ እናቲቱን ከጫጩቶዋ ጋር አትውሰድ።
7 ፤ ነገር ግን መልካም ይሆንልህ ዘንድ ዕድሜህም ይረዝም ዘንድ እናቲቱን ስደድ፥ ጫጩቶችንም ለአንተ ውሰድ።
8 ፤ አዲስ ቤት በሠራህ ጊዜ ማንም ከእርሱ ወድቆ ደሙን በቤትህ ላይ እንዳታመጣ በጣራው ዙሪያ መከታ አድርግለት።
9 ፤ የዘራኸው ዘርና ከወይኑ የወጣው አንድ ሆነው እንዳይጠፉብህ በወይንህ ቦታ ላይ ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ።
10 ፤ በበሬና በአህያ በአንድነት አትረስ።
11 ፤ ከተልባ እግርና ከበግ ጠጕር በአንድነት የተሠራ ልብስ አትልበስ።
12 ፤ በምትለብሰው በልብስህ በአራቱ ማዕዘን ዘርፍ አድርግ።
13 ፤ ማናቸውም ሰው ሚስት ቢያገባ፥ ከደረሰባትም በኋላ ቢጠላት፥
14 ፤ የነውር ነገር አውርቶ። እኔ ይህችን ሴት ሚስት አድርጌ አገባኋት፥ በደርስሁባትም ጊዜ ድንግልናዋን አላገኘሁባትም ብሎ በክፉ ስም ቢያሳጣት፥
15 ፤ የብላቴናይቱ አባትና እናት የድንግልናዋን ምልክት ወስደው በበሩ በአደባባይ ወደ ተቀመጡ ወደ ከተማ ሽማግሌዎች ያምጡት፤
16 ፤ የብላቴናይቱም አባት ሽምግሌዎቹን። እኔ ለዚህ ሰው ልጄን ዳርሁለት እርሱም ጠላት፤
17 ፤ እነሆም። በልጅህ ድንግልና አላገኘሁባትም ብሎ የነውር ነገር አወራባት፤ የልጄም ምልክት ይኸው ይላቸዋል። በከተማም ሽማግሌዎች ፊት ልብሱን ይዘረጋሉ።
18 ፤ የዚያችም ከተማ ሽማግሌዎች ያንን ሰው ወስደው ይግረፉት፤
19 ፤ በእስራኤል ድንግል ላይ ክፉ ስም አምጥቶአልና መቶ የብር ሰቅል ያስከፍሉት፥ ለብላቴናይቱም አባት ይስጡት፤ እርስዋም ሚስት ትሁነው፥ በዕድሜውም ዘመን ሁሉ ሊፈታት አይገባውም።
20 ፤ ነገሩ ግን እውነት ቢሆን፥ በብላቴናይቱም ድንግልናዋ ባይገኝ፥
21 ፤ ብላቴናይቱን ወደ አባትዋ ቤት ደጅ ያውጡአት፥ በእስራኤልም ዘንድ የማይገባውን ነገር አድርጋለችና፥ በአባትዋም ቤት አመንዝራለችና የከተማዋ ሰዎች እስክትሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሩአት፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታስወግዳለህ።
22 ፤ ማናቸውም ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ተኝቶ ቢገኝ፥ አመንዝራውና አመንዝራይቱ ሁለታቸው ይሙቱ፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከእስራኤል ታስወግዳለህ።
23 ፤ ማናቸውም ሰው ድንግልና ያላትን ልጃገረድ ቢያጭ፥ ሌላ ሰውም በከተማ ውስጥ አግኝቶ ከእርስዋ ጋር ቢተኛ፥
24 ፤ ሁለቱን ወደዚያች ከተማ በር አውጡአቸው፤ ብላቴናይቱ በከተማ ውስጥ ሳለች አልጮኸችምና፥ ሰውዮውም የባልንጀራውን ሚስት አስነውሮአልና እስኪሞቱ ድረስ በድንጋይ ውገሩአቸው፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታስወግዳለህ።
25 ፤ ነገር ግን ሰው የታጨችውን ልጃገረድ በሜዳ ቢያገኛት፥ በግድ አሸንፎም ቢደርስባት፥ ያ የደረሰባት ሰው ብቻውን ይገደል።
26 ፤ በብላቴናይቱ ላይ ግን ምንም አታድርጉ በብላቴናይቱ ላይ ለሞት የሚያበቃ ኃጢአት የለባትም፤ ሰው በባልንጀራው ላይ ተነሥቶ እንደሚገድለው ይህ፤ ነገር ደግሞ እንደዚሁ ነውና፤
27 ፤ በሜዳ ባገኛት ጊዜ የታጨችው ልጃገረድ ጮኻለችና፥ የሚታደጋትም አልነበረምና።
28 ፤ ማናቸውም ሰው ድንግልና ያላትን ያልታጨች ልጃገረድ ቢያገኝ፥ ወስዶም ቢደርስባት፥ ቢያገኙትም፥
29 ፤ ያ የደረሰባት ሰው አምሳ የብር ሰቅል ለብላቴናይቱ አባት ይስጥ፤ አስነውሮአታልና ሚስት ትሁነው፤ በዕድሜውም ዘመን ሁሉ ሊፈታት አይገባውም።
30 ፤ ማናቸውም ሰው የአባቱን ሚስት አይውሰድ፥ የአባቱንም ልብስ ጫፍ አይግለጥ።